mandag 22. juli 2013

በህገ ወጥ የዘመቻ እስር የሚሊዮኖች ድምፅ አይታጠፍም!!!

 ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ለሶስት ወራት የሚቆይ ህዝባዊ ንቅናቄ በመጀመር በመላው አገሪቱ የሚገኙ አባላቶቹንና ደጋፊዎቹን
ማንቀሳቀሱ ይታወቃል፡፡ የሚልዮኖች ድምጽ ለነፃነት በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ አራት መሰረታዊ ጥያቄዎችንና
ወቅታዊ ጉዳዮችን ያነገበ ሲሆን እንደ ሁልጊዜውም ፓርቲው ሰላማዊነቱን በጠበቀ መልኩ በቁርጠኝነት ንቅናቄውን በታቀደለት መሰረት
እያስኬደው ይገኛል፡፡
አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ሀይል በሰላማዊ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠትና በተነሱ
ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር በርን ከመክፈት ይልቅ ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ ለጥያቄዎቹ አስተጋቢዎች የተለየ መልክ ለመፍጠር የሚያደርገው
ሩጫ እንደተጠበቀ ሆኖ በህገ መንግስቱ በግልጽ የተቀመጡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመሰብሰብና አቤቱታ የማቅረብ መብትን በአደባባይ
እየጨፈለቀና እነዚህ መብቶች ይከበሩ ዘንድ የሚጠይቁ አባላቶቻችንን ከህግ አግባብ ውጪ በገፍ እያሰረም ነው፡፡
በጎንደርና ደሴ ከተማ በ7/11/2005 ያደረግናቸው ሰላማዊ ሰልፎች ስርዓቱ ዘብ ቆሜለታለሁ እያለ በየዕለቱ ከሚያነበንበው ህገ-
መንግስት በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ እንደሚገኝ አይነተኛ ማሳያ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሊደረግ የታቀደውን ሰላማዊ ሰልፍ
እንዲያውቅ የተቋቋመ የመንግስት ባለስልጣን እወቅልኝ ላለው አካል ለሰልፉ ሰላማዊነት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ በደብዳቤ
ማሳወቅ አልያም ሰልፉን ለአንድ ሳምንት እንዲራዘም በቂና አሳማኝ ምክንያት በማቅረብ በደብዳቤ መጠየቅ ከአንድ ሃላፊነትና ህዝብን
የማስተዳደር ስልጣን ከወሰደ አካል የሚጠበቅ ቢሆንም በሁለቱ ከተሞች የሚገኙ ሃላፊዎች ግን ፈርመው ለተቀበሏቸው ደብዳቤዎች
ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡
ሰላማዊ ሰልፎቹን ለማሰናከል ሃላፊዎቹ የየአካባቢዎቹን ሚሊሻዎች፣ የደንነት ሰዎች፣ ታጣቂዎችና ፖሊሶች በመጠቀም አባላቶቻችንን
አስረዋል፣ አስፈራርተዋል፣ አዋክበዋል፡፡ ከአንድ የመንግስት አካል በማይጠበቅ መልኩም አመራሮቻችንን አግተዋል፣ የተለጠፉ የሰላማዊ
ሰልፍ ጥሪ ወረቀቶችን እንዲቀደዱ በማድረግና ህዝቡ በሰልፎቹ እንዳይገኝ በካድሬዎች አማካኝነት የቤት ለቤት ቅስቀሳ
ከማድረጋቸው በተጨማሪ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር በማድረግ ከየከተሞቹ አቅራቢያ ከሚገኙ ወረዳዎች ዜጎች ድምጻቸውን
ለማሰማት እንዳይመጡ እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡
በጥቂቱ ለመግለጽ የሞከርናቸውን መሰናክሎች በማለፍ በሁለቱ ከተሞችም ሕዝቡ በገፍ አደባባይ በመውጣት ፍጹም ሰላማዊነቱን
በጠበቀ መልኩ ጥያቄውን አስተጋብቶና ተቃውሞውን አሰምቶ ወደ መኖሪያ ቤቱ ተመልሷል፡፡ አንድነት ፓርቲም ለደሴና ለጎንደር ህዝብ
ያለውን ታላቅ አክብሮት በመግለጽ በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች በቀጣይ ፕሮግራሙ በሚያደርጋቸው የተቃውሞ ሰልፎች ለሚገኙ ዜጎች
አርአያነታቸው የጎላ እንደሚሆን እምነቱን ይገልጻል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አንድነት በያዘው እቅድ መሰረት የጸረ ሽብር አዋጁ በህገ መንግስቱ እውቅና የተቸራቸውን መብቶችን
የሚጨፈልቅና ከህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ መሰረዝ ይገባዋል የሚሉ ዜጎች ወደ ዋናው የፓርቲው በጽ/ቤት
በመምጣት የተቃውሞ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ የሚጠይቅ ‹‹ከሚሊዮኖች ለምን አንዱ አይሆኑም›› የሚል በራሪ ወረቀት በሁሉም የአዲስ
አበባ ወረዳዎች ለማሰራጨት የተጀመረውን እንቅስቃሴ መታወቂያቸውን ለማሳየት በማይፈቅዱ ደህንነቶች ነን ባዮችና በፖሊስ ጥምረት
በሕገወጥነት እየተደናቀፈ መገኘቱ አሳዝኖናል፡፡
ፖሊስ የአንድ ፓርቲ ወገንተኛ ሳይሆን ህዝብን ማገልገልና ሁሉንም በህግ መነጽር መመልከት የሚገባው አካል ቢሆንም ሚዛናዊነትን
ባልጠበቀ ሁኔታ ህገ መንገስታዊ መብታችንን በመጠየቅ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የምናቀርበውን አቤቱታ ለማደናቀፍ መሞከሩና
አባላቶቻችንን እግር በእግር እየተከታተለ ለእስር መዳረጉን በቸልታ ለመመልከት አንፈቅድም፡፡
በራሪ ወረቀቱን መበተን ከጀመርንበት ደቂቃ ጀምሮ አባላቶቻችን እየታሰሩና ፍርድ ቤት እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ፖሊስ ፍርድ ቤት
ባቀረባቸው ወጣቶች ላይም አንድነት የሚባል ፓርቲ መኖሩን አጣርቼ እስክመጣ የ10 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱና ፍርድ ቤቱም
የተጠየቀውን መፍቀዱ የምንገኝበት ሰዓት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ እንድንገነዘብ የሚያደርግ ነው፡፡
በየክፍለ ከተማው የሚገኙ የፖሊስ ኮማንደሮች ከህግ አግባብ ውጪ በመንቀሳቀስ አባላቶቻችንን ማሰራቸውና በአንዳንዶቹም ላይ
አካላዊ ድብደባ ማድረሳቸው ነጻ የፍትህ ስርዓትና ተጠያቂነት ቢኖር በወንጀል የሚያስጠይቃቸው በሆነ ነበር፡፡ አንድነት በአባላቶቹና  በእንቅስቃሴው ላይ የተከፈተውን ህገ ወጥ የፖሊስ ዘመቻ ለማስቆምና በደል ፈጻሚዎቹም በታሪክ፣ በህዝብና በህሊና ዳኝነት ይጠየቁ
ዘንድ ለማድረግና በድጋሚ የፍርድ ቤቶችን ነጻነት ለመፈተሸ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመምራት ተዘጋጅቷል፡፡
ፓርቲው የሚደረጉበትን ህገ ወጥ የአፈና ድርጊቶች በመቋቋም የጸረ ሽብር አዋጁ እንዲሰረዝ እያሰባሰበ በሚገኘው የህዝብ ድምጽ
እንደሚገፋበት በድጋሚ በማረጋገጥ ይህንኑ አላማ ከግብ ለማድረስ መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጡ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ስለ
ቁርጠኝነታቸውና ታማኝነታቸው ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ የሚሊዮኖች ድምፅም እስከነፃነት ድረስ ይቀጥላል፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት)
ሐምሌ 10 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ


Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar