torsdag 11. juli 2013

የቤተልሔም አበራ የሥነ-ምግባርን ቅጥር የመናድ ተልእኮ

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

big brother the chase
ትናንት ቅዳሜ 2-10-2005 ዓ.ም ፌስ ቡክ ላይ ተጥጄ በነበርኩበት ሰዓት አንዱ ጓደኛዬ አንድ ከቪዲዮ (ከትዕይንተ ኩነት) የተወሰደ ፎቶ (ምስለ ኩነት) ለጥፎ እዚያው ላይም አስተያየቱን ጽፎ ሌሎቹም ይጽፉ ዘንድ ጋበዘ፡፡ ነገር ግን ይህ ጓደኛዬ ስለጉዳዩ ትክክለኛ መረጃ አልነበረውም ነበርና በአስተያዬቱ ላይ ለሕዝብ በቀጥታ በሚታይ መድረክ ላይ ከወገብ በታች እርቃን መታየት ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት የወጣና መወገዝ እንዳለበት በ3 መስመር ጽፎ ነበር፡፡ እኔም ፎቶውን(ምስለ ኩነቱን) ዓይቼ በነገሩ ተደናግጬና ግራ ተጋብቼ ከስር (is she a crazy woman? I am sure she is a escapee from the Amanuel mental institution) ጤነኛ ነች ግን? እርግጠኛ ነኝ ከአማኑኤል የእዕምሮ ሕሙማን የሕክምና ማዕከል ያመለጠች ነች ብዬ ጻፍኩ፡፡ ለካ ነገሩ እንዲህ ቀላል አልነበረም ኖሯል ማታ ላይ በአንዱ የF.M ሬዲዮ (ነጋሪተ ወግ) የመዝናኛ ፕሮግራም(ምስናድ) ሳዳምጥ የተፈጸመው ጉዳይ ከዚህ የከፋ የሰማውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ሁለት ጆሮዎቹን ጭው የሚያደርግ የልጅቱን ቤተሰቦችና ዘመዶች በድቅድቅ ጨለማ እንደሚሄድ ሰው የጉምብስ የሚያስኬድ ያየንበትንና የሰማንበትን ዓይንና ጆሮ ለማመን የሚያዳግት ጉድ መፈጸሙን ተረዳሁ፡፡ወይ ወደላይ ብሎኝ አላረፍኩት የማቅለሽለሽ ስሜት ለሰዓታት ተናነቀኝ ከተኛሁ በኋላም እንደ መጥፎ ቅዥት ደጋግሞ ያባትተኝ ነበር፡፡ የማውቃቸው ሴቶች ሁሉ እሷን መስለው ታዩኝ፡፡ እኔን ይሄን ያህል የጎዳኝ ቤተሰቦቿን በተለይም ወላጆቿንማ እንዴት ያደርጋቸው ይሆን ብዬ ለእነሱ በጣም አዘንኩ፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው በDSTV. የሚታይ 8ኛ ዙር Big Brother Africa የሚባል reality show (የእውነት ትዕይንት) የመዝናኛ ፕሮግራም (ምስናድ) ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ከሄዱት ሁለት ወንድና ሴት ኢትዮጵያዊን ቤተልሔም አበራ በመባል የምትጠራዋ ዜጋ ያልተጠበቀ አይደለም ጨርሶ ያልታሰበ በባለፈው የውድድር ጊዜ ተሳትፋ የነበረችውን ኢትዮጵያዊት እሷ በመሳሟ ብቻ በእሷና በቤተሰቦቿ የደረሰባትን ችግር በመጥቀስ እንድትጠነቀቅ የሰጠቻትን ምክርና ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን በመተውና ይሄንንም በማድረጓ ከኢትዮጵያዊያን ሊደርስባት የሚችለውን መገለልና ጫና በመናቅና ከምንም ባለመቁጠር በብዙኃን መገናኛ ለሕዝብ በቀጥታ በሚተላለፉ ዝግጅት እጅግ አስደንጋጭ ነውረኛና ጸያፍ ድርጊት (ወሲብ) ከሴራሌዮናዊ ወንድ ጋር ፈጽማ ስለነበርና ይሄንንም መላው ዓለም እየተቀባበለ ጠላት እንደተለመደው ሲደሰትና ኢትዮጵያዊያንንም ለማሸማቀቅ ለማዋረድ ለማሳፈር የሀገራችንን ገጽታ ለማጉደፍ ሲጠቀምበት ወዳጅ ደግሞ አንገቱን ሲደፋበት እና ይህ ጸያፍና ነውረኛ ድርጊት በፍጹም ጨዋና ቁጥብ ባሕል ያለውን፣ ሃይማኖተኛ የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አይወክልም በማለት ሲከራከሩበት ዐቢይ የብዙኃን መገናኛ ርእስ ሆነ፡፡
እኔ በግሌ ከልጅቱ ተግባር ባልተናነሰ ያበገነኝና ያቆሰለኝ ማታ ሳደምጠው የነበረው የመዝናኛ ምስናድ አዘጋጆች ጉዳዩን ሚዛናዊ ያደረጉ መስሏቸው ይናገሩት የነበረው ነገር ነበር፡፡ ነገር ግን እንኳንና ልጅቱ የፈጸመችው ድርጊት በቀጥታ ሊተላለፍ እንደሚችል አስቀድማ እያወቀች፣ ተገዳ ወይም ተደፍራ ሳይሆን ወዳና ፈቅዳ እንዳደረገችው ታውቆና ይህን በማድረጓ በሀገርና በሕዝብ ላይ ያደረሰችውን ሀፍረት ውርደት መሸማቀቅና ሥብራት ያህል ሚዛን የሚያነሣ ምክንያት ይኖራት ይመስል ስልክ እየደወሉ ይሄንን ድርጊቷን በጥብቅ ያወግዙ ለነበሩ አድማጮች እንዲህ ከማለታችን በፊት የእሷንም ቃል ማድመጥ ይኖርብናል የምትለው ነገር ይኖራታል ብለን እንጠብቃለን መቼም ያለምንም ምክንያት ይሄንን ነገር ታደርጋለች ብለን አናስብም ወዘተ ማለታቸውና ሕዝብ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰማውን ስሜት ሲገልጹ የምስናዱ አዘጋጆች ከሆኑት አንዱ ድርጊቱን ያወገዙ የተቃወሙትንና መብቷ ነው ያሉትን ሰዎች የነሲብ ግምት ሲገልጽ እኩል በእኩል እንደሆነ አድርጎ ሲያወራ ሌላኛው አብሮት ያለው ደግሞ ድርጊቱን ያወገዙት እንደሚበዙ ይናገራል፡፡ እኔ ግን እርግጠኛ ነኝ እነኝህ አዘጋጆች ለሚዛናዊነት ባላቸው የተሳሳተ መረዳት ነገሩን ሚዛናዊ ያደረጉ መስሏቸው እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ አስከፊና ጸያፍ ጉዳይ ላይ የሕዝብ ስሜት እኩል በእኩል ይሆናል ብሎ መገመት የማይታሰብ ነው፡፡ የተባለው እርግጥ ሆኖ እኩል በእኩል ሆኖ ከተገኘ ግን ለዚህ ላለንበት የሞራል (የቅስም) ሥብራትና ልሽቀት የሥነምግባር ውድቀት “ሞተን ተቀብረናል በድናችን ነው የሚንቀሳቀሰው” የሚለው ቃል ራሱ የሚገልጸው አይመስለኝም ነገር ግን ይህ ይለመሆኑን በቀላል ትዝብት መረዳትና መገመት እንደሚቻለው የላይኛው አባባል ሐሰት እንደሆነ ማወቅ ይቻላል፡፡
ለምሳሌ በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን ለክብሩና ለነውር ግድ የለሽ የሆነውንና የማይገደውን ፀረ ግብረገብ የሆነውን ካልሆነው ጋር ብናነፃጽር የምናገኘው ውጤት እውነታውን ያስረዳናል፡፡ በመሆኑም ይሄንን ስሕተት በተደጋጋሚ ሲፈጽሙት አስተውላለሁና እንዲህ ዓይነት ተሳሳተ መረጃ ሊገምቱት ከሚችሉት በላይ ሕዝቡን ተስፋ የመቁረጥና በቀላሉ እጅ የመስጠት ችግር ውስጥ እንዲገባ የማድረግ አሉታዊ ውጤት አለውና እንዲህ እንዲሆን ደሞ ይፈልጋሉ ብየ ስለማልገምት እጅግ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ አይበለውና እኩል በእኩል ደረጃ የሚገለጽበት ደረጃ ወይም ዘመን የምንደርስ ከሆነም እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ሊስተናገዱ የሚገባቸው አሁን በቀረበበት ሁኔታ ሳይሆን ዳታው (ቁጥሩ) እንዲህ በእንዲህ መሆኑ የቱን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆናችንንና ልንሠራበት እንደሚገባ በሚያስገነዝብ በሚቀሰቅስ መልኩ እንጂ ጭራሽ በሚያደፋፍርና በሚያሳስት መልኩ መሆን አይኖርበትም፡፡ ይህንን ስል አፋቸውን ሞልተው መብቷ ነው የሚሉ ሰዎች ጨርሶ አይኖሩም እያልኩ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የመብት ምንነትን የማያውቁ ግለሰቦችና እነሱም በተመሳሳይ ቦታና ጊዜ ቢሆኑ ይህች ልጅ ያደረገችውን ከዚያም የከፋ ድርጊት የማድረግ ፍላጎትና አቋም ያላቸው የወደቀ ሰብእና የሞራል(የቅስም) ስብራት፣ የሥነ ምግባርና የግብረገብ ብልሽት ያለባቸው ግለሰቦች ይሄንን ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚጠራጠር ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡እንዲህ ዓይነት ትውልድ እንዲፈራ እንዲወጣ ሆን ተብሎ በጣም እየተሠራበት እንደቆየና ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩለት እንደቆየ በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡
መብቷነው ላሉ ቤቲያዊያን የምለው ሲጀመር አንድ ግለሰብ ሁሉንም ነገር የማድረግ መብትና ነፃነት ፈጽሞ የለውም በሰው ልጅ ታሪክ ይሄ ሆኖ አያውቅም፡፡ ደናቁርትና ማሰብ የተሳናቸው ግለሰቦች ሁሉ መብቴ ነው፣ መብቷ ነው፣ መብታቸው ነው ለማለት የትም መቸም ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ እንኳን አያደርጉም፡፡ አንድ ግለሰብ ያሰበውን ነገር የማድረግ መብትና ነፃነት የሚኖረው ያ ሊያደርገው ያሰበው ነገር የሰው ልጆችና ማኅበራዊ ፍጥረቶች እንደመሆናችን የጋራ ጥቅማችንን የማይጎዳ የማይፃረር የማይቃረን እስከሆነ ጊዜ ብቻና ብቻ ነው የየትኛውም የሕግ መጽሐፍና የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ከዚህ ጽንሰ ሐሳብ የወጡ አይደሉም፡፡ ይህች ልጅ እንኳንና በተለቀቁት ማስታወቂያዎች ሀገርን ወክላ እንደተሳተፈች ተገልጾ ቀርቶ ባይገለጽም እንኳን እኛ ኢትዮጵያዊያን (ሐበሾች) እንደ ሕዝብና እንደ ሀገር የጋራ ጥቅሞች አሉን፡፡ ከእነሱም ውስጥ ሀገር፣ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ክብር፣ ማንነት፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ወዘተ. እያልን ልንዘረዝራቸው እንችላለን፡፡ የምንሠራው ሥራ እነኝህን ነገሮች የሚጎዳ የሚጻረር ከሆነ ያንን ነገር ማድረግ መብታችን ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ከዚህ የአስተሳሰብ ሚዛን ወይም ደረጃ ወጥተን ማሰብና መተግበር ከሞከርን ከሰውነት ደረጃ ወርደን ወደ እንስሳነት ከእንስሳነትም ከብዙዎቹ በወረደ በዘቀጠ ባነሰ የአስተሳሰብ ደረጃና ክብር ላይ እንዳለን ማወቅ መረዳት ይኖርብናል፡፡
እዚህ ላይ ቤቲያዊያን አያይዘው የሚጠቅሱት ከድንቁርና የሚመነጭ አሳፋሪ አባባል አለ ‹‹ምን ነው? እሷ በግልጽ ስላደረገችው ነው እንዴ? ሁሉም ተደብቆ የሚፈጽመው ተግባር አይደለም እንዴ?›› የሚባል፡፡ የተደበቀውማ ተደብቋል የሚያውቀው የለም ይሄኔ እኮ ስንት የምናከብራቸው የምንኮራባቸው የምናደንቃቸው ሰዎቻችን ከዚህ በከፋ ነውር ላይ ውለው ይሆናል፡፡ነገር ግን ያደረጉት ተደብቀው በመሆኑ ሀፍረቱና ውርደቱ ከእነሱ አልፎ እንደ ሀገር ለኢትዮጵያ እንደ ሕዝብ ለሐበሻ አልሆነብንም፡፡ እንኳንና በእንደዚህ ዓይነት የመማገጥ ግንኙነት በሕግ በተመሠረተ ትዳር ያሉ ጠንዶች እንኳን በሥውር የምናደርገው አይደለም እንዴ ብለው በልጆቻቸው ወይም በሌሎች ፊት በግልጥ ዕየታዩ እናድርገው አይሉም፡፡
በድብቅ የምናደርገው አይደለም እንዴ! ተብሎ በግልጽ እናድርገው ማለት ይሄ ሌላ ምንም ሳይሆን ከበድ ያለ የአዕምሮ ጤና መቃወስ ችግር ነው፡፡ ሰው ደካማ ፍጡር እንደመሆኑና ጥንካሬውም አንዱ ከሌላው የማይመጣጠን እንደመሆኑ ከስሕተት(ከኃጢአት) የጸዳ ሊሆን አይችልም፡፡ስሕተት የምንለው ነገር በራሱ ክብደትና ቅለቱ የሚለያይ ቢሆንም፡፡ እናም ድክመት ከሰው ልጅ የማይጠፋ መሆኑ ቢታወቅም ለጋራ ሰላም፣ ለጥምረታችን ደኅንነት፣ ለማኅበራዊነታችን ጤንነት ሲባል እስከዛሬ ሲደረግ እንደነበረው ሁሉ የምግባር ድክመትና ብልሹነት(አመል) ያለብን ሰዎች መታረም ካልቻልን ነውራችንን በስውር በድብቅ ብናደርገው ኃላፊነት ከመወጣት ጋር የሚነጻጸር ተግባር እንደፈጸምን ይቆጠራል ጓዳ የማይችለው ጉድ የለምና፡፡ ከዚህ ወተን ካሰብንና ከሠራን ግን እንደ ጤነኛ ሰው በጤነኛ ዓይን መታየትና መስተናገድ አይኖርብንም፡፡ Big brother Africa reality show ተወዳዳሪዎቹ እንዲያደርጉት ከሚፈልገውና ከሚያደርስባቸው ጫና ባጠቃላይ ከዝግጅቱ ቅርጽ አንጻር ስናይ ተወዳዳሪዎቹ ሀገርን ወክለው እንዲሳተፉ ማስታወቅና ማድረግም አይኖርበትም ነበር ማድረግ ሳይኖርበት ይሄንን ማድረጉ የልጅቱ የሥነ ምግባር ብልሹነት እንዳለ ሆኖ ይህ ድርጊት የኢትዮጵያዊያንን ስም ለማጥፋት ለመስበር የሕዝቡን ሞራል (ንቃተ ወኔ) ለማኮላሸት ሆን ተብሎ እንደተደረገ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ሲጀመር ሀገርን በግለሰብ የመወከል ተግባር እጅግ እጅግ ከባድ ነገር ነው፡፡ምክንያቱም ተወካዮቹ የሚያደርጉት እያንዳንዱ ነገር ሁሉ የሀገርንና የሕዝቧን ባሕል ማንነትና አስተሳሰብ እንደገለጸ ወይም እየገለጸ እንደሆነ ይቆጠራልና፡፡ እንዲያዝ የተፈለገው ግንዛቤ ይሄ ሆኖ ውክልናው ከተደረገም ተዎካዮቹ እንዲያደርጉ የሚጠበቀውና የሚበረታታው የሚያንጸውም አዎንታዊ የሆኑ ነገሮችን እንጅ ጭራሽ የማያደርጉት የማያስቡት የነበረውን ሁሉ እንዲያደርጉ መገፋፋትና ማበረታታት አይኖርባቸውም፡፡ ይህ የእውነታን ትዕይንት ቅርጽ የሚለውጥ ድርጊት ነውና፡፡ ነገር ግን የዚህ ‹‹የመዝናኛ›› ዝግጅት አዘጋጆች ይሄንን እንደሚያደርጉ ቀደም ሲል ተሳትፈው የነበሩ ተወዳዳሪዎች አረጋግጠዋል፡፡Reality show (የእውነታ ትዕይንት) ተብሎ ሀገር በምግባረ ብልሹዎች እንድትወከል የማድረጉ ጽንሰ ሐሳብ በራሱ የሎጅክ (የአመክንዮ) ችግር አለበት፡፡ ምክንያቱም የሥነምግባር ብልሽት እንከን ያለባቸው ግለሰቦች ብዙውን ጨዋ የኅብረተሰብ ክፍል ሊወክሉ አይችሉምና፡፡ ይሄንን ባለመረዳት ወይም ለመረዳት ሳይፈለግ ቀርቶ ይህ ከተደረገ ግን ከጀርባው ሌላ ስውር ዓላማ እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡ የሆነውም ይሄው ነው በዚህች ልጅ አማካኝነት ከእንግዲህ የሀገራችን ኢትዮጵያ በብዙኃን መገነናኛ የተፈጸመ ርኩሰት በሚል ስሟ የውርደት መዝገብ ላይ ሠፍሯል፡፡ የሚገርመኝ ይህ የreality show (የእውነታ ትዕይንት) ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠራ የተፈቀደለት እንደሆነ ነው የምናየው ነገር ግን ነገሩ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን የሚጠቁም መሆኑ ነው፡፡ ይህ የሀገርንና የሕዝብን ቅስም የሠበረ የሀፍረትና የመሸማቀቅ ዱላውን በእያንዳንችን ጭንቅላት ላይ ያሳረፈ ጸያፍ ድርጊት ከተፈጸመና የወዳጅና ጠላት መሳለቂያ ከሆንን በኋላም የመንግሥት የብዙኃን መገናኛዎች አሁንም የBig Brother Africaን ማስታወቂያ እያስተላለፉ በመሆኑ፡፡ ይህ ሕዝብ ጨዋና ታጋሽ ስለሆነና ቁጣውንም መግለጽ የሚችልበት ዕድል ስለሌለ እንጂ ይህ ድርጊት የተፈጸመው በሌሎች ሀገሮች ላይ ቢሆን ኖሮ የDSTV. በሀገሪቱ ያለውን ተወካይና የBig Brother ተወካይ መሥሪያ ቤቶች ላይ አደጋ በደረሰ ነበር፡፡
በእርግጥ የከበረ ታሪክና ማንነት እንዳለው ከዓለማዊ(secular) እስከ መንፈሳዊ(spiritual) ያሉ ጥንታዊ የሥነጽሑፍ መረጃዎች የሚያረጋግጡት እውነታ በመሆኑ የዚህች ልጅና የመሰሎቿ(የቤቲያዊያን) ድርጊት የተመሰከረለትን ሕዝብና ሀገር የሚወክል አይሆንም፡፡ የምትወክለው ራሷንና እንዳለመታደል የድንቁርናም ነገር ሆኖ ሥልጣኔና ዘመናዊነትን እጅግ በተሳሳተ መንገድ የተረዱትን እንዴት እንደሚያስቡ ባይገባኝም ዘመናዊነትና ሥልጣኔ ማለት መባለግና ስድነት ሥነምግባርና ግብረ ገብነት አልባ መሆን ነው ብለው የሚያስቡትንና እንደዚህም የሆኑትን ከአምስት በመቶ በታች ያሉትን “ኢትዮጵያዊያንን” ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከ90 ሚሊዮን (ከእላፋት) ሕዝብ በላይ እንዳላት ይገመታል፡፡
ከዚህ ቁጥር በጠቀስኩት የጨነገፈ አስተሳሰብ የተመረዙት 15 በመቶ ሕዝብ በሚኖርበት በከተሞች ያሉ ጥቂት ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህች ልጅና ድርጊቷ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክልበት ምንም ሆኔታ የለም፡፡ ይህ ሁሉ እየታወቀ ኢትዮጵያን በዚህ ርኩስ ግብር ስሟ እንዲጠራና በውርደት መዝገብ እንዲሰፍር መደረጉ ታስቦበት ለክፋት አይደለም የሚለኝ ካለ የዋህ መሆኑን ልነግረው እወዳለሁ፡፡ እናት አባቶቻችን ለሀገራችን ክብር፣ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ ስም ሲሉ የደም መሥዋዕትነትም ቢሆን ለመክፈል አያመነቱም ነበር፡፡ ዛሬ እነ ቤቲያዊያን ደግሞ ለሀገር ክብር፣ ስም ወዘተ. ብለው አጥተው የማያጡትን ነገር እንኳን ቢሆን ለዚያች ቅጽበት ታግሰው ማሳለፍን እንደ መሥዋዕትነት ከቆጠርነው ቤቲያዊያን ይህችን ትንሽ ነገር እንኳን ለማድረግ ጽናትና ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው እንደማይፈልጉና ስለ ሀገር ብለው አላደርግም የሚሉት ነገር እንደሌለ በሐሳባቸውና በሥራቸው ግልጽ አድርገዋል፡፡ እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ትውልድ ተይዞ ነው ሩቅ የሚታለመው ?
በመጨረሻ ሌሎች እኅት ወንድሞቻችን በቀጣይ ጊዜያት በተመሳሳይ መድረኮች ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ለማስገንዘቢያነት ይረዳ ዘንድ ይህች ልጅ ይህንን ድርጊት በመፈጸሟ በግል ሕይወቷ ምን ሊገጥማት ይችላል የሚለውን እንመልከትና እናብቃ፡፡ ማኅበረሰባችን እንደምናውቀው ጥብቅና ክብርን የማዕዘን ድንጋዩ ያደረገ፡፡ ሃይማኖታዊ አሻራ የሰፈረበትና የታነጸ ባሕል ያለው ኅብረተሰብ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ይህች ልጅ ከባድ የሆነ የመገለል አደጋ ያጋጥማታል፡፡ የመገለሉ አደጋ ከእርሷም አልፎ ቤተሰቦቿ ላይም ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህንን ጸያፍ ድርጊት የሀገርና የሕዝብ ወኪልነቷን ለገንዘብ ስትል ለሕዝብ በቀጥታ በሚታይ መድረክ ፊት አድርጋለችና እስከ ተከፈላት ጊዜ ድረስ Blue film (የወሲብ ምትርኢት) እስከ መሥራት ድረስ አላደርግም የምትለው ነገር እንደማይኖር ሊያስገምታትና የሰውነት ክብር ሊያሰጣት ይችላል፡፡ ወላጆቿንም አሳዳጊ የበደላት በማሰኘት ለዘለፋ ትዳረጋለች፡፡ ምናልባትም አንዳንዴ ያልዘሩት ይበቅላል ይባላልና ይሄኔ ወላጆቿ በመልካም ሥነ ምግባር ለማሳደግ የደከሙ ሆነው ይሆናል፡፡ነገር ግን እንዲህ የነበሩ ቢሆኑም እንኳ ያለ ሥራቸው ለዘለፋ ዳረገቻቸው ማለት ነው ፡፡
ልጅቱ መምህርት እንደሆነች ይነገራል፡፡ የሚገርመውም ይሄው ነው መማር ሥነምግባርንም ለማነጽ፣ ሰብእናን ለመገንባት ይጠቅማል ተብሎ ይታሰባልና አሁን አሁን በየዩኒቨርስቲው የምናየው ነገር ይሄንን አባባል የሚሽር እየሆነ የመጣ ቢሆንምና ይህች እኅታችንንም መማሯ አርቃ ለማሰብና ለማገናዘብ የጠቀማት ባይሆንም፡፡ እናም የገለጸችውና ያሳየችው የሥነምግባር ግድፈትና ብልሽት ለተማሪዎች አርአያ ሊያደርጋት ስለማይችል ወይም በመጥፎ አርአያነት ስለሚያስቆጥራትና ከዚህም አንፃር የምታስተምርበት ት/ቤት በእሷ ምክንያት ተማሪ ሊያሳጣው ስለሚችል እንደሚያሰናብታት ወይም የሥራ ዋስትናዋን ሊያሳጣት እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
amsalu
አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ልጅቱ እንደተመኘችው አሸናፊ ሆና 300 ሺህ ዶላር ሽልማት ማሸነፍ ብትችል እንኳ እንዳሰበችው የአስጎብኝ ድርጅት ብትከፍት በዜጎች የሚወደድ፣ ተቀባይነት ያለው፣ እንደአስጎብኝ ድርጅት ኃላፊነት የሚሸከም እንደማይሆን የመጠርጠር የመገለል በአጠቃላይ ሥራዋን ልትሠራ የምትችልበትን ከባቢ ያለማግኘት ችግር ይገጥማታል ምክንያቱም ገንዘቡ የተገኘው ክብሯን ሸጣ፣ ማንነቷን አዋርዳ፣ ሰብእናዋን አርክሳ፣ ሕዝቧን አሳፍራ፣ ቤተሰብ ዘመዶቿን አሸማቃ፣ ታሪኳን እስከወዲያኛው አጠልሽታ፣ ጤናዋን ለአደጋ ዳርጋ፣ ኅሊናዋን አቆሽሻ፣ ሃይማኖቷን አስተሃቅራ ወይም አምላኳን አስቀይማ (ሃይማኖት ካላት) በመሆኑ፡፡ ስለሆነም ይህ ገንዘብ የተባረከ አይሆንም እንደአመጣጡ ሁሉ የጥፋት ይሆናል እንጅ፡፡ በሉ እግንዲህ ከዚህ ይሠውረን እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡እኅቴ ቀላሉን ያድርግልሽ ለንስሐ ያብቃሽ፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar