onsdag 30. juli 2014

በፖሊስ የተፈነከተችው ወይንሸት ሞላ እና አዚዛ መሐመድ ነገ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ

ከዳዊት ሰለሞን
ወይንሸት ሞላ ቀጭኗ የጥንካሬ ምልክት
addisweyeneshet molla
ከሁለት ሳምንት በፊት በአንዋር መስጊድ በተፈጸመ ጥቁር ሽብር እጇንና ጭንቅላቷን ተጎድታ እስር ቤት የተወረወረችውን ወይንሸት ሞላን የጠዋቱን ብርድ እየተጋፋን ልንጠይቃት ከኤልያስ ገብሩ ጋር አምርተን ነበር፡፡ከፎቶግራፍ ጋዜጠኛዋ አዚዛ መሐመድ ጋር አንድ ክፍል የተጋራችው ወይንሸት ከጉዳቱ በኋላ የማይንቀሳቀስ ቀኝ እጇን የለበሰችው ቱታ ጃኬት ውስጥ ከትታ ከአዚዛ ጋር ወደ እኛ መጣች፡፡
አዚዛ ጉዳት ያልደረሰባት በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ወይንሸትን የምትንከባከበው እርሷ ናት፡፡ጭንቅላቷን በተፈነከተች ወቅት የፈሰሰው ደሟ ጸጉሯን በማጠባበቁ ማላቀቁ ትልቅ ስራዋ ሆኖ መሰንበቱን አዚዛ አወጋችን፡፡እጇን በማሸትም ከፎቶግራፍ አንሺነት ሞያዋ በተጨማሪ ጥሩ የወጌሻ ብቃት እንዳላት ማወቋን በፈገግታ ታጅባ ነገረችን፡፡
‹‹አዚዛን ባላገኝ ኖሮ እስሩ በጣም አስቸጋሪ ይሆንብኝ ነበር፡፡ነገር ግን አሁን እሷን በማግኘቴ የጭንቅላቴም ሆነ የእጄ ህመም አይሰማኝም››የምትለው ደግሞ ወይንሸት ናት፡፡
ወይንሸት እጅግ በጣም ቀጭን ከመሆኗም በላይ ሴት ናት፡፡ወታደሮቹ ግን ሁለቱም አልታያቸውም፡፡ድፍረትን ከስጋ ውፍረትና ከወንድነት ጋር የምናቆራኝ ሰዎችም ወይንሸትን ስናይና ከአንደበቷ የሚፈልቁትን የውስጣዊ ጥንካሬ መገለጫ የሆኑ ቃላትን ስናደምጥ የመጀመሪያው አስተሳሰባችንን እንለውጣለን፡፡
‹‹እንዲህ አይነት ነገር በመፈጠሩ ምንም አልተሰማኝም፡፡ቁስሎቹ የፈጠሩብኝ ስቃይም ተራ ነገር ነው፡፡ይህ እንደሚሆን በፊትም አውቃለሁ፡፡››በማለትም ከሰውነቷ ገዝፎ የሚታየውን ጥንካሬዋን ታሳያለች፡፡
ነገ አዚዛና ወይንሸት ሜክሲኮ የሚገኘው ፍርድ ቤት ማለዳ ይቀርባሉ።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar