onsdag 23. juli 2014

የመንግሥትን ሥራ በማያመች ሁኔታ በመምራት የተጠረጠሩት የአቶ መላኩ ፈንታ የፍርድ ቤት ውሎ

10d10cfd99d2eea7d4355c5a85ddadfa_Lየቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆንና የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መርተዋል በሚል ተጠርጥረው ብቻቸውን በተከሰሱበት ክስ ላይ፣ ዓቃቤ ሕግ ከሐምሌ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የሙያ ምስክሮችን ማሰማት ጀመረ፡፡
በአቶ መላኩ ፈንታ ላይ ብቻ በክስ መዝገብ ቁጥር 141354 በሁለተኛ ክስነት የቀረበባቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ የሚያስረዱ የሙያ ምስክሮችን በመስማት ላይ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ሐምሌ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሰዓት በፊት አንድ የዓቃቤ ሕግ ምስክርን ሰምቶ አጠናቋል፡፡
ምስክሩ የሚሰጡት የምስክርነት ቃል ያማማቶ ኢትዮጵያ የተባለ አስመጪ ድርጅት ባለቤት አቶ አህመድ አብዱላሂ፣ ከ1996 እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ የተጨማሪ እሴት ታክስና የንግድ ሥራ ገቢ ግብር ኦዲት ተደርጎ ከተገኘ ከ48.4 ሚሊዮን ብር ጋር በተያያዘ ክስ ላይ ነው፡፡
ነጋዴው የተጠቀሰውን ገንዘብ እንዲከፍሉ የውሳኔ ማስታወቂያ ሲደርሳቸው፣ ልደታ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው የአነስተኛ ግብር ከፋዮች ጽሕፈት ቤት አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ያቀረቡትን አቤቱታ ያጣራው አቤቱታ አጣሪ ኮሚቴ የግብር ግምቱ ትክክል መሆኑን ያፀድቃል፡፡ ነጋዴው የተወሰነባቸውን ግብር 50 በመቶ በማስያዝ ለግብር ይግባኝ ጉባዔ ማቅረብ ሲገባቸው ቅሬታቸውን ለአቶ መላኩ ፈንታ ማቅረባቸውን፣ አቶ መላኩም በአዋጁ መሠረት ግለሰቡን ወደ ይግባኝ ጉባዔው መላክ ሲገባቸው፣ አዋጁን በተፃረረ መልኩ የነጋዴውን አቤቱታ ተቀብለው፣ በድጋሚ እንዲታይላቸው በማድረግ ቀድሞ ተወስኖባቸው የነበረው 48.4 ሚሊዮን ብር ወደ 34 ሚሊዮን ብር ዝቅ እንዲል ማስደረጋቸውን በሚመለከት፣ የሙያ ምስክሮቹ እንዲያስረዱለት የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ጭብጥ አስይዞ ምስክሩ መደመጥ ጀመሩ፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ምስክሩ ለምን እንደመጡ ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዱለት ያቀረበላቸውን ጥያቄ ተከትሎ ምስክሩ እንደተናገሩት፣ ሙደሲር ጁሀርና አሚናት የተባሉ ባልና ሚስት፣ የቁርጥ ግብር ከፋዮች (የቀን ገቢያቸው ታስቦ ግብር የሚከፍሉ) በመሆናቸው፣ የእነሱ ግብር ሲታሰብ የያማማቶ ማኅተም ያረፈበትና ከ700 ሺሕ ብር በላይ ግዢ የተፈጸመበት ደረሰኝ መገኘቱን ምስክሩ አስረድተዋል፡፡ በደረሰኙ (ፋክቱር) ላይ ሙሉ ስምና የድርጅቱ አድራሻ በአግባቡ ተጽፎ መሰጠት ሲገባው ስም ብቻ ያረፈበት ፋክቱር በመሆኑ፣ የያማማቶ ኢትዮጵያ የሒሳብ መዝገብ በገቢዎችና ጉምሩክ የኢንተለጀንስ ሠራተኞች ወደ ኦዲት ቢሮ እንዲመጣ መደረጉን ምስክሩ አክለዋል፡፡ ከ1996 እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የንግድ ትርፍ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ ምርመራ ሲደረግ፣ ያማማቶ ኢትዮጵያ ያልከፈለው በድምሩ ከ48.4 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር መገኘቱንና እንዲከፍል እንደተወሰነበት አስረድተዋል፡፡
የሉዲና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች አስመጪ የሆነው ያማማቶ ኢትዮጵያ በባለሥልጣኑ በተፈቀደለትና በተሰጠው ደረሰኝ መሸጥ እንደነበረበት የገለጹት ምስክሩ፣ እሱ ግን ያለደረሰኝ ሲሸጥ እንደነበር መስክረዋል፡፡ የትርፍ ገቢ ግብር ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደግሞ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፍል ግምት መወሰናቸውንና ለልደታ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ጽሕፈት ቤት ማስተላለፋቸውን ምስክሩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ያማማቶ ኢትዮጵያ ለጽሕፈት ቤቱ አቤቱታ ቢያቀርብም ውሳኔው እንደፀናበትም መስማታቸውን ምስክሩ አክለዋል፡፡
ኮሚቴ ተቋቁሞ ውሳኔው በድጋሚ እንዲታይ በስብሰባና በባለሥልጣኑ የኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላቸው በየነና የታክስ አማካሪው አቶ ማሞ አብዱ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ ምስክሩ የኦዲት ቡድኑ አለመስማማቱን አስረድተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ‹‹አዘዋል›› በማለት በቃል በመግለጽ አቶ በላቸውና አቶ ማሞ ጫና እንዳደረጉባቸውም ገልጸዋል፡፡ በኋላ በ1996 ዓ.ም. አቶ ሙደሲርና ወይዘሮ አሚና ግብይት የፈጸሙባቸው ፋክቱሮች በፎረንሲክ እንዲመረመሩ ተደርጎ፣ ‹‹ፋክቱሮቹ የያማማቶ ኢትዮጵያ አይደሉም›› በመባሉ፣ የአንድ ዓመት የ1996 ዓ.ም. ብቻ ሒሳብ ተቀንሶ ከ48 ሚሊዮን ብር ወደ 34 ሚሊዮን ብር ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል፡፡
ጠበቆች በመስቀለኛ ለምስክሩ ባቀረቧቸው ጥያቄዎች፣ ፋክቱሮቹ በፎረንሲክ የተመረመሩት የመጀመሪያ ኦዲት ተደርጎ የግምት ውሳኔ ከመናገሩ በፊት ወይም በኋላ መሆኑን እንዲያስረዱ ጠይቀዋቸው፣ የመጀመሪያ ኦዲት ሠርተው ውሳኔ ካስተላለፉ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኮሚቴ የተቋቋመው ለዚህ ብቻ ነው ወይ ተብለው ሲጠየቁም እርግጠኛ እንዳልሆኑና ስለኮሚቴው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ በመስቀለኛ ጥያቄና ምላሽ ወቅት ምስክሩ ድርጅቱ ፋክቱሩ የራሱ ሰነድ እንደሆነ ማመልከቱን ለእሳቸው ቢሮ ግን አለመግለጹን፣ አቤቱታ አጣሪው በጽሑፍ ጠይቆ በጽሑፍ እንደመለሰ፣ አራት ፋክቱር አግኝተው እንደመረመሩና ውጤቱም የያማማቶ አለመሆኑን እንዳረጋገጠ ገልጸዋል፡፡
ኮሚቴው ያቀረበውን ውሳኔ ለዋና ዳይሬክተሩ ማቅረብ መቻል አለመቻሉን የተጠየቁት ምስክሩ፣ ኮሚቴውን ያቋቋሙት ዋና ዳይሬክተሩ በመሆናቸው በግብር አዋጁ መሠረት ለእሳቸው ማቅረብ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ አቶ መላኩ ፈንታ ግብሩ ከተወሰነ በኋላ ያዘዙት ወይም የላኩት ደብዳቤ ስለመኖሩ ተጠይቀው፣ ምስክሩ ‹‹የለም›› ብለዋል፡፡
ግብሩ እንዴት እንደተሰበሰበ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ የገለጹት ምስክሩ፣ ስለአቶ መላኩም ‹‹የማውቀው ነገር የለም›› ብለዋል፡፡ የኦዲት ሥራ አጠራጣሪ ነገሮችን አጣርቶ ማቅረብ ወይም መሥራት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የፍርድ ቤቱ ሦስቱም ዳኞች የማጣሪያ ጥያቄ ለምስክሩ በማቅረብ፣ ግልጽ ያልሆኑ የምስክሩ ምላሾችን አጥርተዋል፡፡ የሐምሌ 14 ቀን የግማሽ ቀን ምስክርነትም በዚህ አጠናቀዋል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar