ወርቅነህ ገበየሁ ለምን ወደ ትራንስፖርት ሚኒስትርነት?
ሰሞኑንን ይፋ የሆነውን የአዲስ የሚኒስትሮችና የ”ከፍተኛ” ባለሥልጣናት ሹመት ተከትሎ ከውስጥም ከውጭም የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው። ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ሹመቱን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት ሪፖርተር “ምንጮቼ ነገሩኝ” በማለት አቶ በረከት ስምዖንን የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር የሚያደርጋቸው አዲስ ሹመት እንደሚሰጣቸው ዘግቦ ነበር። ይህንኑ ዜና ተከትሎ “ኢትዮጵያ በኦፊሴል በኤርትራ መመራት ጀመረች” በማለት ቅድመ አስተያየት የሰነዘሩ ጥቂት አልነበሩም።
ሚዲያውን መዳፋቸው ስር አኑረው የቆዩት አቶ በረከት ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትርነታቸው ተነስተው የጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም የፖሊሲና ጥናት አማካሪ ሚኒስትር ተደርገው መሾማቸው “በረከት አደጉ ወይስ ተገፉ?” የሚል ጥያቄ አስነስቷል።
ከመለስ ህልፈት በኋላ ኢህአዴግ ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ያሳዩት አቶ በረከት ከድርጅታቸው ይሁንታ ውጪ “አቶ ሃይለማርያም ጠ/ሚኒስትር ይሆናሉ። የሚቀረው የስርዓት ማሟላት ጉዳይ ነው” ማለታቸው የህወሃትና የኦህዴድ ሰዎችን ክፉኛ አበሳጭቶ እንደነበር የሚያስታውሱ አስተያየት ሰጪዎች “አቶ በረከት አማካሪ ሆነው ወደ ጠ/ሚኒስትር ቢሮ መዛወራቸው ከኢህአዴግ ባህሪ አንጻር የመገፋት ወይም ስራ አልባ የማድረግና ከቀጥተኛ ተሳታፊነት የመታቀብ ያህል ነው” ባይ ናቸው።
“በዜግነታቸው ብቻ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የመሳተፍ መብት የሌላቸው አቶ በረከት ሲፈነጩበት ከነበረው የኢህአዴግ ሚዲያ መሰናበታቸው በራሱ በርካታ ጉዳዮችን የሚያመላክት ነው” የሚሉት ምንጮች “የፖሊሲና የጥናት ጉዳዮች ከፍተኛ የቀለም እውቀትና ልምድ የሚጠይቅ ሃላፊነት ነው። አቶ በረከትም ሆነ አቶ ኩማ ለዚህ አይመጥኑም። ውሳኔው ማቀዝቀዣ ውስጥ የማስገባት ያህል ነው” ሲሉ አቶ በረከት ያላቸው የአደባባይ ሚና ማክተሙን ያወሳሉ።
በሌላ በኩል የተለየ አስተያየት የሚሰነዝሩ ክፍሎች እንደሚሉት “አቶ በረከት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስራ እለት እለት ሥርስራቸው ሆነው እንዲሰሩ የተሰጣቸው ስልጣን ነው። ይህ የሚያሳየው እሳቸው አሁንም ፈላጭ ቆራጭ ሆነው መቀጠላቸውን ነው” በማለት የሃሳብ ልዩነታቸውን ያስቀምጣሉ።
አቶ በረከትና አቶ ሃይለማርያም የቀረበ ግንኙነት እንደነበራቸው፣ አቶ መለስ በህይወት እያሉም ቢሆን ሶስቱ እንደማይለያዩ ያመለከቱት ክፍሎች፣ የህወሃት የበላይ አመራርና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር መሪ የሆኑት ዶ/ር ደብረጽዮን አዲስ በሚቋቋመው የደህንነት ሚኒስትር ውስጥ የሚሰይሙት ሚኒስትር፤ ሪፖርትር እንዳለው አቶ በረከት ካልሆኑና የህወሃት ሰው ከተሾመ “በትክክልም አቶ በረከት ወደ ማቀዝቀዣ ክፍል ገብተዋል ማለት ነው” ሲሉ ሁለት ጫፍ ያለው አስተያየት ሰንዝረዋል።
አቶ ኩማ አሁን ባለው ኦህዴድ ውስጥ አንጋፋና ታማኝ፣ በቅጣት ከሶስት ዓመት ማዕቀብ በኋላ ወደ መንግስት ሃላፊነት የተመለሱ፣ ኦህዴድን ማጥራት ሲፈለግ በትር የሚጨብጡ፣ በመሆናቸው ከንቲባነቱን ሲለቁ እንዳያፈገፍጉ አዲሱ ሃላፊነት እንደተሰጣቸው አብዛኞች ይስማማሉ። አቶ ኩማ ካላቸው ልምድና ዕውቀት አንጻር አቶ ሃይለማርያምን በፖሊሲ ጉዳዮችና በጥናት ረገድ ለማማከር የሚችሉ ሰው እንዳልሆኑ ስምምነት መኖሩን የሚጠቁሙ ጥቂት አይደሉም። ከዚህ አንጻር በዓለምቀፋዊ ዋና ከተማነት ከምትታወቀው አዲስአበባ ከንቲባነት ወደ አማካሪነት ኩማ ደመቅሳ “ሲሾሙ” እንደ ሥልጣን ሽረት ከተቆጠረ፤ የበረከት ስምዖን በተመሳሳይ መልኩ መታየት የማይችልበት ምክንያት ሊኖር እንደማይችል የሚከራከሩ አሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሥልጣን በምክትል ጠ/ሚ/ርነት ሲያድግና ኢህአዴግ በምርጫ የመሸነፍ ቅንጣት ችግር ሳይኖረው ኩማን ከከንቲባነት ሥልጣን ማንሳቱ የብቃት ማነስና አለመፈለግ እንደሆነ ተጨማሪ አስተያየቶች አሉ፡፡
ለሶስትና አራት ዓመት ህጻን “ከክልላችን ስለተባረርክ የትምህርት ገበታህ ላይ መቀመጥ አትችልም” የሚል ደብዳቤ የሚጽፉና በሙስና በከፍተኛ ደረጃ የሚታሙት የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ሽፈራው ሽጉጤ ወደ ትምህርት ሚኒስትርነት የተሻገሩት አቶ ሃይለማርያም ደቡብ ክልል ላይ ያለውን ሰንሰለት ለመበጣጠስ እንዲያመቻቸው እንደሆነ ይገመታል። ሃዋሳ ነዋሪ የሆኑ ለጎልጉል እንደገለጹት አቶ ሽፈራው የዘረጉት ድር መበጣጠስ እንዳለበት የታመነው አሁን አይደለም። በሚሊዮን የሚቆጠር የክልል በጀት እንደፈለጉ ከሚያስኬዱበትና ያለገደብ ሥልጣናቸውን ከሚያከናውኑበት የክልል ፕሬዚዳንትነት ወደ ሚኒስትርነት “መሾም”፤ የሥልጣን ሽረት ተብሎ ከመጠራት ውጪ ምንም ሊባል እንደማይችል በሽፈራው ሽጉጤ አመራር የተማረሩ ብቻ ሳይሆኑ ደጋፊዎቻቸውም ያመኑበት ጉዳይ ነው፡፡
የትምህርት ሚኒስቴርን መምራት ያቃታቸው አቶ ደመቀ በስራ ብዛት ሰበብ የምክትል ጠ/ሚኒስትርነታቸውን ወንበር ብቻ እንዲይዙ መደረጉን ያመለከቱት ክፍሎች “አቶ ሽፈራው በሹመቱ ደስተኛ እንዳልሆኑ ከሚቀርቧቸው ሰምተናል። ሃዋሳ በክልሉ መስተዳድር ውስጥ እሳቸው የሰገሰጓቸውም ስጋት ላይ ናቸው” ብለዋል፡፡ በቀጣይ ሃይለማርያም “ታማኛቸውን” በመሾም (“በማስመረጥ”) እውነተኛ የደኢህዴን ሊቀመንበርነታቸውን እንደሚያረጋግጡም ይጠበቃል፡፡
ደመቀ መኮንን በምክትል ጠ/ሚኒስትርነታቸው ብቻ እንዲቀጥሉ የተደረጉት ምን አልባትም አዲስ በሚቋቋመው የደህንነት ሚኒስቴር ውስጥ በአማራ ክልል ከነበራቸው “ልምድ” አኳያ ለኮታ ማሟያ ታስበው ነው በሚል ካድሬው በስፋት እንደሚያወራ እየተሰማ ነው። አቶ ደመቀ በአማራ ክልል የደህንነቱ መሪ እንደነበሩና በዚሁ በተግባራቸው “የተመሰገኑ ታማኝ” ለመሆን መብቃታቸውን የሚቀርቧቸው ይናገራሉ።
ወደ አዲስ አበባ የተዛወሩት ልጆቻቸውን በትምህርት ቤት እየሰደቧቸው በመቸገራቸው እንደነበር የሚያስታውሱት እኒህ ክፍሎች “አቶ ደመቀ የአማራው ክልል መሬት ተላልፎ ሲሰጥ አቶ አያሌው ጎበዜ አልፈርምም ሲሉ፣ እሳቸው መፈረማቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ‘ከሃዲ’ የሚል ስም ተሰጥቷቸዋል። ህጻናት ልጆቻቸውም ትምህርት ቤት መማር ያልቻሉት ለአባታቸው በተሰጠ ስም ትምህርት ቤት ውስጥ ጓደኞቻቸው ስለሚያበሽቋቸው ነው” በማለት አቶ ደመቀ ቀደም ሲል ጀምሮ ከደህንነቱ ጋር ያላቸው የሥራ ግንኙነት ታማኝ እንዳሰኛቸው አስታውቀዋል። ከዚሁ ውለታቸውና ልምዳቸው አንጻር በደህንነት መ/ቤት ውስጥ ይካተታሉ የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሰኔ 27 ቀን ለተሰየመው ፓርላማ በቀረበው ሹመት መነጋገሪያ ከሆኑት መካካል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ወርቅነህ ገበየሁ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው፣ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በተለያዩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች ችግር እንደተጣባው የተመሰከረለትን የትምህርት ሚኒስቴርን እንዲመሩ መመደባቸው፣ አንዲሁም የአቶ ደመቀ በ”ስልጣን በዛባቸው” ሰበብ የሚኒስትርነት ቦታቸውን መነጠቃቸው በቅድሚያ የሚጠቀሱ ናቸው።
የወርቅነህ ገበየሁ “ነገዎ” ሹመት
የፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ገበየሁ የትራንስፖርት ሚኒስትር ስለመደረጋቸው ከሚቀርቡት ምክንያቶች መካከል ቀደም ሲል ለረዥም ዓመታት ከደህንነቱና ከሽብር መከላለከል ግብረ ሃይል ጋር የነበራቸው ቁርኝት ከፍተኛ መሆኑ በግንባር ቀደም ይገለጻል። ለጎልጉልአስተያየት የሰጡ እንደሚሉት ኢህአዴግ የትራንስፖርቱን ዘርፍ በቅርብ መቆጣጠር ይፈልጋል።
በምርጫ 97 ወቅት ለታየው ህዝባዊ መነቃቃት የትራንስፖርቱ ዘርፍ፣ በተለይም የታክሲና የግል ማመላለሻዎች የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስተያየት ሰጪዎቹ ያስታውሳሉ። ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች እስከወዲያኛው እንዳይታሰቡ ለማድረግ ዘርፉን ከደህንነቱ ጋር በቅርብ ማጠላለፍ፣ ኢህአዴግ በከፍተኛ ደረጃ እየገነባሁ ነው የሚላቸውን መንገዶች፣ የስልክና የብሮድ ባንድ መስመሮች፣ የባቡር ትራንስፖርት በቅርብ ለመቆጣጠርና የቁጥጥሩ ሰንሰለት ውስጥ ለማስገባት አቶ ወርቅነህ ሁነኛ ሰው ሆነው መገኘታቸውን እነዚሁ ክፍሎች ይናገራሉ።
አዲሱ ቴሌን ጨምሮ የትራንስፖርት ዘርፉን ከደህንነቱ መዋቅር ጋር በቀላሉ ለማያያዝ ልምዳቸውና የመረቡ አባል ሆነው መቆየታቸው የትራንስፖርት ሚኒስትር ያደረጋቸው አቶ ወርቅነህ፣ የጄኔራልነት ማዕረጋቸው ከሳቸው ጋር ይቆይ ወይም ይነሳ የተገለጸ ነገር እንደሌለ የጠቆሙት ክፍሎች፣ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ የህወሃት አመራሮች አቶ ወርቅነህን በታማኝነት መድበው የተቀበሏቸው ሰው ስለመሆናቸው ጥርጥር የላቸውም።
አቶ ወርቅነህ ታማኝ ስለመሆናቸው፣ በዚሁ ታማኝነታቸው ስልጣናቸውን ሳይጠቀሙ በፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተርነት ለረዥም ጊዜ መቆታቸውን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው አቶ ወርቅነህ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሰባት ሚኒስትር መስሪያቤቶች ተውጣጥቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው የ”ደህንነት ኮር” ውስጥ አባል እንደነበሩ ይናገራሉ። ይህንን ኮር በአዲስ እየተዋቀረ ስለሆነ አቶ ወርቅነህ ወደ ትራንስፖርት ሚኒስትርነት የተዛወሩት ከደህንነቱ የኮር መዋቅር ውስጥ እንዲወጡ ስለተፈለገ መሆኑን ይገልጻሉ።
ዝርዝር ጉዳዩን ለማብራራት እንደሚቸገሩ የሚናገሩት እነዚህ ክፍሎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ እንዲዋቀር አዋጅ የታወጀለት የደህንነት መ/ቤት ሚኒስትርና የበላይ ሃላፊዎች ይፋ ሲሆኑ ነገሮች ይበልጥ እንደሚጠሩ ተናግረዋል። በኢህአዴግ ውስጥ ተፈጥሮ በነበረውና አሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ እንዳልጠራ የሚነገርለትን ልዩነት ተከትሎ የተሸናፊውን ወገኖች የማጥራት ስራ በተለያዩ ስልቶች እንደሚሰሩ የጠቆሙት እነዚህ ክፍሎች፣ የደህንነት ሚኒስትር ሲቋቋም የሚሾሙት ባለስልጣን ከቀድሞዎቹ መካከል እንደማይሆን ምልክት ማየታቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
የኢህአዴግ ንብረትና የንግድ ተቋም የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ከዚህ የሚከተለውን የአዲስ ሹመትና ተሿሚዎች ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሃሙስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሰላኝ የቀረቡ እጩዎችን ሹመት በአንድ ድምጸ ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።በዚህም መሰረት
አቶ ደመቀ መኮንን – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር
አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ወላሳ – የትምህርት ሚኒስትር
አቶ ሬድዋን ሁሴን ራህመቶ – የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር
አቶ አህመድ አብተው አስፋው – የኢንዱስትሪ ሚኒስትር
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ነገዎ – የትራንስፖርት ሚኒስትር
ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ መሸሻ – በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር
ወይዘሮ ደሚቱ ሃንቢሳ ቦንሳ – የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር
አቶ ጌታቸው አምባዬ በለው – የፍትህ ሚኒስትር
አቶ በከር ሻሌ ዱሌ – የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር
አቶ በለጠ ታፈረ ደስታ – የአካባቢ ጥበቃና የደን ሚኒስትር
አቶ መኮንን ማንያዘዋል እንደሻው – የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር
ሆነው የተሾሙ ሲሆን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ አማካኝነት ቃለ መሃላቸውን ፈጽመዋል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar