fredag 12. juli 2013

ዶ/ር ሰይድ ሐሰን ኢሳትን አስመልክቶ ያደረጉት ንግግር

July 12, 2013

በዋሽንግተን ዲ.ሲ. የኢሳት 3ኛ በዓልን አስደግፎ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ስብሰባ ላይ የቀረበ አጭር (ንድፍ/ግርድፍ) ነግግር

ከዶ/ር ሰይድ ሐሰን- Murray State University
ክቡራትና ክቡራን ወገኖች፤
በዚህ አጭር ንግግሬ 3 የተያያዙ ሐሳቦችን (ነጥቦችን) አንስቼ አቀርባለሁ።
ከዚህ በታች ያለው አጭር ንግግሬ ኢሳትን እንደ ነፃ ሚዲያ አድርጎ በማሰብ (assume) ነው። የእስካሁኑ የኢሳት የሥራ ጠባይም ይህንኑ ያመለክታል። የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸውን፤ ካገር ውጭም፤ ካገር ውስጥም ያሉትን አስተናግዷል። የመንግሥት ባለሥልጣናትንም እየጋበዘ ለማነጋገር ሞክሯል። አንዳዶቹ- ለምሳሌ እንደነ አቶ በረከት ሲሞን ያሉት የኢሳት ጋዜጠኛ ሲደውልላቸው በጆሮው ላይ ቢዘጉበትም!
ከመንግስት ቁጥጥር ነጻ የሆነ  የመገናኛ ዘዴ፤  ነፃ ሚዲያ/ፕረስ-  ለሀገርና ለሕዝብ ልማት በጣም አስፈላጊ ነው። በተለይ ባሁኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ነፃ ሚድያ እያስገኘ ያለው ጥቅም ብዙ ነው። የኢንፎርሜሽ ቴክሎጅን በሰፊው ተፎካካሪ ሀገሮችን ጥለው እንዲገሰግሱ እየረዳቸው ይገኛል። የሰውን  ባጠቃላይ ዓለምንም እየለወጠ ነው።Dr. Seid Hassan, Murray State University.
ለምሳሌ፤ ነፃና  ጠንካራ የመገናኛ ዘዴ፤ ነፃ ሚዲያ ተቋም፤ነጻ ፕረስ፤ የግል ቴሌቪዝንና ሬድዮ ጣቢያውች መኖር፤
ዲሞክራሲ እንዲስፋፋ (እንዲፋፋ) ይረዳል፤ እንዳውም፤ ዲሞክራሲ ያለ ነፃ ሚዳያ ሊኖር አይችልም። ሁለቱን ነጣጥሎ ማየትም አይቻልም!
ንግድ እንዲስፋፋ፤ የገባያ ፉክክር እንዲኖርና እንዲጠናከር ይረዳል። የገባያ ፉክክር ሲኖር ደግሞ ኢኮኖሚው ያድጋል፤ አገርም ትበለፅጋለች።
እውነት የበላይነት እንዲኖራት ይረዳል::
ቅርስንና ታሪክን ዘክሮና ዘግቦ ለውርስ የማስቀመጫ መሣሪያ ይሆናል።
ዜጎች ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለመፈለግ እንዲወያዩ፤ እንዲከራከሩ፤ ይፈቅዳል/ይረዳል። በዚህም የተነሳ ዜጎች ብልህና ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንዲወስዱም ይረዳል።  ዜጎች ለሕብረተሰባቸውና ለሀገራቸው እድገት ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።
ዜጎች በሀገራቸው ላይ የተፈጥሮ አደጋ፤ ተላላፊ በሽታ (ወረርሽኝ) ሲመጣ ባስቸኳይ ለሕብረተሰቡ መረጃዎችን ለማቅረብ፤ ሕብረተሰብም እንዲያውቃቸው ለማድረግ ይረዳል። ዜጎች እንድተባበሩም፤ የዜግነት ግዴታቸውን በፍጥነትና በጋራ እንዲወጡም  የመገናኛ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል።
የተጠፋፉ ዜጎችን፤ቤተሰቦችን፤ መተባበር የሚፈልጉ ሙያተኞችን ያገናኛል። በአካል መገናኘት ያልቻሉትን ሁሉ በቀላሉ ያገናኛል።
መንግሥት ሥራውን በትክክል እንዲሠራ ይረዳዋል; መንግሥት ለሕዝብ ተገዢ እንዲሆን ይረዳዋል። ዜጎች የመንግሥትን መጥፎም ሆነ መላካም ተግባሮች እንዲያዩ፤ እንዲገነዘቡና እንዲቆጣጠሩትም ይፈቅድላቸዋል፤ በአንፃሩም፤ አምባገነኖች ሕብረተሰቡን በተራ ውሼትና ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ሊያጠምቁና ሊበርዙ ሲፈልጉ መንገዱን ይዘጋባቸዋል። በዚህም የተነሳ ክፍተቶችንም ይሞላል።
ለነፃነት የሚደረገውን ትግል አቀጣጣይ መሳሪያ ሆኖ ያገልግላል። በጭንቅ ጊዜ (በጭንቅ ዘመን) የሕዝቡን አንድነት ሊያስተባብርና ለጋራ ትግሉ የመገናኛ  መድረክ ሆኖ ያገለግላል።
ፖለቲካዊና ህበረተሰባዊ ለውጦች እንዲመጡ/እንዲገኙ ይረዳል፤ አምባገነኖችን ከሥልጣን የማስወገጃ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል፤ የሕብረተሰቦችን፤ የዜጎችን ችሎታ ያዳብራል (ኢምፖወር ያደርጋል)።
ነፃ ሚዲያ ኢንፎርሜሽንን ስለሚያቀብል እውቀት እንዲስፋፋ ይረዳል። ባለፉት 20 ዓመታት እንደታየው፤ በርካታ ሀገሮች  አዲሱን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (ፈጠራ) ተጠቅመው ሕዛባቸው በሥልጣኔና ዕውቀት እንዲገሰግስ አድርጓል። ደቡብ ኮሪያን ልምሳሌ መጠቀስ ይበቃል።
የግል ቴሌቪዝንና ሬድዮ ጣቢያውች መኖር አማራጭን ይሰጣል። ድምፃቸው ለተዘጋቸው ሀሳባቸውን የመግለጫ መንገድ፤ እንደ እንባ ጠባቂ ሆኖም ሆኖ ያገለግላል።
የመረጃ ማዕከሎችን በመፍጠር ትልቅ ሚናን ይጫውታል። መረጃና የመረጃ ተቋም የጋራ ሀብት ነው። መረጃ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው። መረጃ  ኃይል ነው። መረጃ እውቀት ነው። እውቀትም የጋራ ሀብት ነው!
ከላይ የጠቀስኳቸው  የነፃ ፕረስ፤ የነፃ ሚዳያና የመረጃ ተቋም መገኛ የሚያስገኛቸው ከፊል ጥቅሞች ናቸው። እነዚህ ጥቅሞች  አንድ የጋራ የሆነ ጠባይ አላቸው። ይኸውም፤ ጥቅማቸው በአብዛኛው ለግል ሳይሆን ለጋራና ለሕዝብ ነው። በእንግሊዝኛው የPublic Goods ጠባይ ካላቸው መጠቀሚያዎች ይጠቃልላል ማለቴ ነው።   ይህ የጋራ ጠባያቸው፤ ከጥቅማቸው ጋር ተያይዞም  ቢያንስ አንድ  ሁለት ችግሮችን ያስከትላል።
1ኛው ችግር፡ ጠንካራ ሚዲያን ለማቋቋምና ቀጣይ በሆነ መንገድ ለማስኬድ የሚያስወጣው የገንዘብና የጉልበት ወጪው በጣም ብዙ መሆኑ ነው።
ለምሳሌ፤ እንደ ኢሳት ያለውን ተቋም ለማቋቋምና ለማስቀጠል ባጭሩ፤
ሀሳብን በማፍለቅ፤መሰረቱን ለመጣል፤የአየር ሞገዱን ለመምረጥ፤ ለማስተካከልና ለመሳሰሉት፤ ለሚደረገው ውይይት የሚጠፋው ጊዜና ገንዘብ፤
ለመግሥት ታክስና የመሥሪያ ፈቃድን ለማስገኘትና ለማደስ የሚወጣው እንግልትና የገንዘብ ወጪ፤
የሳተላይት ጣቢያን ለመከራየት የሚወጣው ገንዘብ፤
ቦታዎችን ለመከራየት፤ ክፍያውንም በጊዜው ለመክፈል የሚደረገው ወጪ፤
አስፈላጊ የሆኑትን የቴክኖሎጂ የማስተላለፊያ መሣሪያዎችን (broadcast equipment – master control switcher፤ satellite receivers, tape decks, and a transmitter፤ ካሜራዎችን፤ ኮምፒዩተሮችን፤ ሶፍትዌሮችን፤ ወ.ዘ.ተ.) ለመግዛት፤ አሮጌውችን ባዳዲሶቹ ለመቀየር በየጊዜው የሚወጣው ገንዘብ፤.
ሙያተኛ (ፕሮፌሽናል) ጋዜጠኞችን ለመቅተር፤ ለማሰልጠን፤ የሰለጠኑትንም በአግባቡ  ቀጥሮና ከፍሎ ለማሰራት፤ ሳይቋረጥ የሚደረገው ወጪ፤
መረጃን ለማግኘት የሚደረገው ክፍያ፤ ጋዜጠኞች ከቦታ ቦታ ሲጓዙ የሚደረገው ወጪና ክፍያ፤
የተሰበሰቡትን መረጃውች ሰብሰቦና ቀርፆ ለማስቀመጥ የሚደረገው ወጪ፤
ለፕሮግራሚንግ (programming) ለመሳሰሉት የሚደረገው ወጪ፤ ወ. ዘ. ተ.

እንደነዚህና የመሳሰሉትን ለመሸፈን፤ ወጪው ከባድ ስለሆነ፤
ሀ.            አንዱ መንገድ፤ መንግስት ዜጎች ላይ ታክስ ጭኖ ወጪውን አጠቃሎ በመሸፈን ተቋሙን ማስቀጠል ነው። ይህ ክስተት በአፍሪካ፤ በኤሽያና በደቡብ አሜሪካ በስፋት ይታያል።
ለ.            ሁለተኛው መንገድ፤ የሚዲያ ተቋሙ ከመንግሥት ካዝና ድጓሜ እንዲደረግለት በማድረግ፤ የቀረውን እራሱ ተቋሙ በንግድ (ቢዝነስ) የገቢ ምንጩን እንዲፈልግ ማድረግ ነው። ምናልባት እንደነ ቢ.ቢ.ሲ.ን ለምሳሌ ያህል መጥቀስ ይቻላል።
ሐ.           ሦስተኛው፤ የግል ያልሆኑ፤ ለሕበረተሰብ አግልግሎት የተቋቋሙ የሬዲዮና የቴለቪዥን ጣቢያዎች (የሚዲያ ተቋማት)፤  ከመንግሥት ድጎማ እየተደረገላቸው፤ አንዳንድ የገዘብ ማስገኛ መንገዶችን እየፈላለጉ (ለምሳሌ ለኩባንያዎች ማስታወቂያን በማሰማትና በመለጠፍ) ወጪያቸውን ሽፋን ሲያደርጉ፤  በተጨማሪም በየጊዜው ኩባንያዎችንና ግለሰቦችን በመለመን፤ የማይናቅ ወጫቸውን ይሸፍናሉ። በአሜሪካ NPR : National Public Radio ን እና PBS: Public Broadcasting Serviceን  እንደምሳሌመጥቀስ  ይቻላል።
መረሳት የሌለበት ነገር፤ ኢሳትን ልዩ የሚድደርገው፤ሙሉ በሙሉ የእናንተ-ለእናንተ -ለሕዝባችን መሆኑ ነው። ከዚህ ዝቅ ብዬ እንደማሳየውም፤ ኢሳት በግለሰቦች መዋጮ የሚደገፍ መሆኑም የበለጠ ክበድት ይሰጠዋል።
እንግዲህ እኛ፤ አልታደልንምና በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኢሳትን ሊረዳ ቀርቶ፤ ለማዳፈን በበርካታ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት ያባክናል።  ህወሀት/ኢሕአደግ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጨለማ ውስጥ አጉሮ ለዘላለም ለመግዛት ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም። በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብትን እያፈሰሰ የኢሣትን ሞገድ በጥለፍ ለማጥፋት/ለማዳፈን ያላደረገው ነገር የለም።  ይህንን ሲያደርግም፤ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ የፕሬስ ነፃነት የሚፈቅደውን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 29ኝን (ሐሳብንና አመለካከትን የመያዝና የመግለጽ መብት) እንደተለመደው  በመጣስ ነው።
እንደዚህ ባልው ሁኔታ፤ ያለን አማራጭ የነጻ ሚዲያ ጥቅሙን በማሳየት እናንተ ኪሳችሁን እንድትዳብሱ “መለመን” የግድ  ነው። እንደዚህ ያለው ልመና አስፈላጊም ነው፤ የተለመደም ነው። አገር ወዳዶችና ተለማኞችም ሳይሰለቹ በቋሚነት መልኩ መለገስ እንዳለባቸው ማስታወስም የግድ ይላል። አሁን ከፊታችሁ የቆኩትም ለዚሁ ነው።
2ኛው ችግር፤ እንደ ኢሳት ያሉት የመገናኛ ዘዴዎች የሚያሰራጩት ዜና እና መረጃዎች፤ ዜናዎች፤ መዝናኛ ዎች … ግደታቸውን ለተወጡትም፤ ላልተወጡትም በጋራ ይደርሳሉ። የወር መዋጮቻቸውን ባለማድረገ ግደታቸውን ያልተወጡትም፤ ግዴታቸውን የተወጡም፤ የከፈሉም፤ ያልከፈሉም፤ ኢሳትን የሚወዱም፤ የማይወዱም፤ ኢሳትን ይሰማሉ፤ጥቅሙንም ይጋራሉ። ግደታችውን ያልተወጡትን መርጦ እንዳይሰሙ፤ ስርጭቱን እንዳይጋሩ፤ እንዳይጠቀሙ ማድረግ አቻልም። የነፃ ተጠቃሚዎችን (በእንግሊዝናው፤free riders ተብለው የሚዘረፉትን ማለቴ ነው ) ማግለል አይቻልም። ችግሩም በእንግሊዝኛው “Free-Rider Problem” ይባላል።  ይህ ችግር  በእንግሊዝኛው ከ“nonexcludability” criteria of a public good ችግር ጋር ይጠቃልለላል።
በዚህም የተነሳ፤ እያንዳንዱ ሰው፤ በግለሰብ ደረጃ፤ አንድ ጊዜ ተቋሙ ከተመሰረተ በኋላ፤ “ለዚህ ሀብትነቱ የጋራ ለሆነ፤ ጥቅሙ የጋራ ለሆነ፤ ጉዳዩ  የጋራ ለሆነ፤ የኔ ብቻ ላልሆነ…. ሌላው ይክፈለው እንጂ እኔ አልከፍልም፤ አላዋጣም” ሊል ይችላል! አልፎም፤  “ይህን የመሰለ “ግዳንግድ” ተቋም ከኔ ኪስ የምትፈልቀው መዋጮ ጋኑን ለመሙላት ለሚደረገው የውኃ ጋጋታ አንዲት ጠብታ ስለሆነች ማዋጣቴ ጉዳትንም፤ ጥቅምንም አያመጣም” የሚል ከንቱ አስተሳሰብን ያስከትላል። ይህ ጉዳይ በእንግሊዝኛው “Drop-In-The-Bucket Problem” ይባላል።  ከዚያም አልፎ “ኢሳትን ከማዳመጥ የሚከለክለኝ፤  ማናባቱ ነው! እምቢ፤ አሻፈርኝ፤ አልከፍልም” የሚል መጥፎ አስታሰብንም ሊያስከትል ይችላል!
እንደምታውቁት እንደዚህ ያለው ችግርና አስተሳሰብ “የፉክክር በር (ወይም ባለቤት የሌለው በር)  ሳይዘጋ ያድርና አደጋው ለሁላችንም  ይደርሳል!”  ከሚለው የአያቶቻችን ቁም-ነገራዊ  አስተሳሰብ ጋር ይያያዛል።
መልእክቴን ግልፅ ያደረግኩ ይመስለኛል፤ ኢሳትን እያንዳንዳችን በግል ተነሳሽነት ካልደገፍነው ኢሳት ሊኖር አይችልም! የኢትዮጵያ አይንና ጆሮ፤ የነጻነት ነፀብራቅ … እንዳይዳከም፤ እንዳይደፈን፤ መብራታችን ሆኖ እንዲቀጥል ከፈለግን፤ ቀጣይ በሆነ መንገድ መርዳት አለብን! ለሌላ የምንተወው ጉዳይ አይደለም!
በነገራችን ላይ ይህ ከላይ የነሳሁት ችግር በመገናኛ ዘዴ (ሚዲያ) ብቻ የተወነ አይደለም።
ጎበዝ፤ እኔን  የሚደንቀኝ፡-
ኢሳትን ለማቋቋም ለማስቀጠል በርካታ ገንዘብ እንደሚያስወጣ እያወቁ፤ ከላይ የጠቀስኩትን ችግርና ፈተና እያወቁ፤ በቀላሉ መውደቅን፤ መክሰርና እንደሚያስከትል እያወቁ ኢሳትን ያቋቋሙት ግልሰቦችና ቡድኖች  (እንደሰማሁት ከሆነም፤ አንዳንዶቹ የቤት ካርታዎቻቸውን ተያዥ በማድረግም ጭምር) እንዴት ደፍረው ይህንን ትልቅ ጉዞ፤ ይህንን ችሮታ፤ ጀመሩት? ነው።
በኔ አስተያየት፤ ኢሳትን የመሠረቱት/የጀመሩት (ይቅርታ፤ እኔ አንደኛው አልነበርኩም!) ሊከበሩ፤ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።
እነዚህ የዲሞክራት ሀይሎች በሕብረተሰቡ (በተለይ በዲያስፖራው) ላይ ያላቸውንም እምነት ያሳያል። የነፃ ሚድያ ጥቅሙንም ከማናችንም በላይ የተገነዘቡ ይመስለኛል! ለነጽነት፤ ለፍትሕ፤ ለዲሞክራሲ ያላቸውን ጥማት ያሳያል። የመንፈስ ጥንካሬያችውንም ያሳያል።  ተበታትኖ ከመጮህ ይልቅ ተቋምን ፈጥሮ የመታገልን ጥቅም የተገነዘቡ፤ ያወቁ ይመስለኛል! በዘላቂነት ውድ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል እንደተነሱም ያሳያል። እነዚህ ሥራዎቻቸውና እምነታቸው እኔን ማርኮኛል! ኢሳትን በማቋቋም እዚህ ድረስ በማድረሳቸው ትልቁን ሸክም አውርደውልንናል። ምስጋና ይገባቸዋል!
ከላይ የጠቀስኩትን ለማጠናከር ያህል፤ እስቲ ኢሳት በዚች አጭር የለጋ  እድሜው  ከሸፈናቸው ትላልቅ ጉዳዮችና ከተጫወተው ታሪካዊ ሚናዎች  አንዳንዶቹን  ልጥቀስ፤
የሙስሊሞች የድምፃችን ይሰማ፤ የመብታችን ይከበር ጥያቄን አስመልከቶ ያደረገው ሰፊ ሽፋንና የተጫወተው ሚና፤
ከጉራፈርዳ እና ከቤንሻንጉል-ጉምዝ የተፈናቀሉትን የብዙ ዜጎች የእሮሮ ድምጾች፤ የህወሃትን የዘር የማጥራት (Ethnic Cleansing) ወንጀል  ሰፊ ሽፋን በመስጠትና በማጋለጥ የተጫወተው ሚና፤
በዋልድባ ገዳም መነኮሳት ላይ ህወሀት የደረሰውን በደል፤ እንግልትና መፈናቀል፤ የዘር ማጥራት ወንጀል፤ የመነኮሳቱን እሪታን በማስተጋባት በተካታታይ ያደረገው ሽፋን፤
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በክረስትና ሀይማኖት ጉዳይ ውስጥ ያደርገውንና እያደረገ ያልውን ጣልቃ-ገብነት በማጋለጥ የተጫወተው ሚናና ሰፊ ሽፋን፤
ለመብታቸው መከበር በሚታገሉ ዜጎቻችን፤ ጋዜጠኞቻችን፤ ወ.ዘ.ተ. እደረሰ ያለውን  እስርና አፈና በማጋለጥ ያደረገው ሚና፤
የአቶ መለስ ሕልፈትን በሚመለከት ማንም ሳይቀድመው ያደረገው የዜና ዘገባና በህወሃት ላይ ያደረሰው ክስረትና ውርደት፤
መንግሥትን የከዱ ግለሰቦችን- ለምሳሌ፤ የኢት/ ቴሌኮሙኒኬሽን በሙስና መዘፈቅ፤አድሎአዊና የጎሰኝነት የተሞላበት አስተደደርን በሚሚለከት፤  በብረታብረትን የቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን ተብየው ውስጥ፤ በኢትዮጵያ የጦርና መከላከያ መሥሪያ ቤት የሚደረገውን (እንደነ አቶ ተስፋየ አጽብሀ ያሉና ሌሎችን ማስታወስ ይበቃል)  እንግዶችን በእንግድነት በማቅረብ፤ በሰፊው እንደ፤ ደኩመንታሪ የሚሆን መረጃን በተከታታይ ማቅረቡ፤
ባጠቃላይ በሀገሪቱ ሰፍኖ ያለውን በደልና አድሎአዊ አስተዳደር ፤በተለይ የአንድ ጎሳ የባላይነት የሰፈነበት የሆነበትን ጉድ በተጨባጭና በመረጃ በተከታታይ ማቅረቡ፤በሚሊዮን የሚቆጠር አድምጭ እንዲሰማው ማድረጉ፤
የሶማሊው የክልል ፕሬዚደንት አቶ አብዲ ሞሃመድ ኦመር ከሶማሊ ጎሳ መሪዎች ጋር ያደረገውን ቅሌታዊ ውይይት፤ ከህወሃት ጋር ያደረገን መርዛዊ የፀረ አማራ ንግግርና  የፀረ-ኢትዮጵያዊ የሶማሊ ዜጋ በደልን፤ በሶማሊ አስተዳደር የሰፈነውን ሙስና  ወጣት አብዱላሂ ሁሴንን በእንግድነት በማቅረብ ያቀረበው ዘገባ/ቅሌት፤
ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የህበረተሰባዊ ተራድዖ መሬዎች፤ የሀሳባቸው መግለጫ መደረክ በመሆን የተጫወተውና እየተጫወተው ያለው ሚና፤
በሀገሪቱ ተንሰርፍቶ ያለውን ሙስና በማጋለጥና በመዘከር ያደረገውና የሚያደረገው አስተዋፅዖ፤
በኔ አስተያየት፤ ከላይ የጠቀስኳቸው የኢሳት ተግባሮች በዋጋ የሚተመኑ አይደሉም! እርሰዎም ያውቁታል፤ ኢሳትን እያዳመጡም አድንቀዋል! ሌሎች የከፈሉም ሰምተውታል፤ አድንቀዋልም! ለመሆኑ ድርሻዎን በትክክል ተውጥተዋል? ጥቅሙን ካወቁ፤ ከዚህ በላይ ያሰፈርኳቸው ችግሮችና ቁምነገሮች የገቡዎት ከሆነ ማለቴ ነው!
መደምደሚያ፤
እንግዲህ እኛ፤ አልታደልንምና በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኢሳትን ሊረዳ ቀርቶ፤ ለማዳፈን በበርካታ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት ያባክናል።  ህወሀት/ኢሕአደግ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጨለማ ውስጥ አጉሮ ለዘላለም ለመግዛት ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም። በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብትን እያፈሰሰ የኢሣትን ሞገድ በጥለፍ ለማጥፋት/ለማዳፈን ያላደረገው ነገር የለም።  ይህንን ሲያደርግም፤ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ የፕሬስ ነፃነት የሚፈቅደውን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 29ኝን (ሐሳብንና አመለካከትን የመያዝና የመግለጽ መብት) እንደተለመደው  በመጣስ ነው።
እንደዚህ ባልው ሁኔታ፤ ያለን አማራጭ የነጻ ሚዲያ ጥቅሙን በማሳየት እናንተ ኪሳችሁን እንድትዳብሱ “መለመን” የግድ  ነው። እንደዚህ ያለው ልመና አስፈላጊም ነው፤ የተለመደም ነው። አገር ወዳዶችና ተለማኞችም ሳይሰለቹ በቋሚነት መልኩ መለገስ እንዳለባቸው ማስታወስም የግድ ይላል። አሁን ከፊታችሁ የቆኩትም ለዚሁ ነው።
ወያኔ/ኢሕአደግ  እንደ ኢሳት ያሉ ተቋማትን እንደጦር የሚፈራቸውም ያለምክንያት አይደለም፡፡ መላው ዓለም ለኢኮኖሚውና ለኅብረተሰባዊ ዕድገቱ እየተጠቀመበትና የኤኮኖሚ፤ የፖለቲካዊና የሕብረተሰባዊ እድገቱን በፈጠነ መልክ እያስኬደ ባለበት በዚህ የሥልጣኔ ግስጋሴ ዘመን፤ ወያኔ/ኢሕአደግ  የሬዲዮ፤ የሳተላይት ቲቪ ስርጭቶችን፤ የኢንተርኔት፤ የእስካፕና ሌላውን ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴ መዝጋቱ፤ ለመዝጋት መጣሩ፤ መበሰሱ፤ ኅብረተሰቡ በጨለማ ውስጥ እንዲጓዝ ማደረጉ፤ የትምህርት ተቋሟት ጥራት መቀነሱ፤ በጣም የሚያስፍር ነው። በሥላጣን ላይ ያሉት ቡድኖችና ግለሰቦች የቱን ያህል፤ወደኋል የቀሩ መሆናችውን ያሳያል። እነዚህን የረከሱ ኋላ ቀሮች እንድንታገላቸው የሚያስችለን እንደ ኢሳት ያሉ ተቋማትን፤ የመረጃ ማዕከላትን  በመመሥረትና በቋሚነት በመደገፍ ብቻ ነው።
በኔ አስተያየት ለመጀምሪያ ጊዜ የዲያስፖራው ሕብረተሰብ የሠራው ውጤታማ ሥራ ኢሳትን ማቋቋሙ ነው። ኢሳት በጨለማ ውስጥ እየማቀቀ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ  የነፃነት ችላጭል ሰጥቶታል። ወደፊትም ይህ የመገናኛ ዘዴ የበለጠ እንድንተባበር፤ ለነጻነታችን የምናደርገው ትግላችን  እንዲስምር፤ የሕዝባችን አንድነት እንዲጠነክር የሚረዳን፤ እንዳውም ህወሀት በቆፈረልንና እየቆፈረልን ባለው ጉድጓድ እንዳንገባ፤ እንዳንተላለቅ መገናኛና መወያያ፤ የመፍትሄ መፈለጊያ መደርካችን፤ መሳሪያችን ይሆናል ብዬ አጥብቄ አምናለሁ። የመልካም ዜጎች ትልቁ ሚና እና ትልቁ እርዳታ መሆን ያለበት እንደ ኢሳት ያሉ ተቋማትን መፍጠርና ማስቀጠል ነው።
ኢሳት እንዲቀጥል፤ እንዲያድግ፤ ቋሚ ሆኖ እንዲያገለግለን  እያንዳንዳችን፤ ሁላችንም –  ማንም ሳይነግረን፤ ማንንም ሳንጠብቅ፤ ማንም ሳይለምነን፤ በባለቤትነት፤ በግል ተነሳሽነትና ሀላፊነት በተሞላው መንገድ፤ በቋሚነት ድርሻችንን መወጣት አለብን ብዬ አምናለሁ። እያንዳንዳችን ኢሳትን ለመጠበቅ ዘብ መቆምም አለብን።
ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar