onsdag 10. juli 2013

የኢትዮጵያ ፀረ ሽብር አዋጅ መሻሻል ለምን?

July 10, 2013

አዘጋጅ Zone 9
በሚኪያስ በቀለ
Any law that uplifts human personality is just. Any law that degrades human personality is unjust. One has not only a legal but a moral responsibility to obey just laws. Conversely, one has a moral responsibility to disobey unjust laws… for an unjust law is no law at all.
Dr. Martin Luther King
የመንግሥት ወይስ የሕዝብ ሕግ?
በኢትዮጵያ ውስጥ የፀረ ሽብር አዋጅ የወጣው በ2001 ዓ.ም ላይ ሲሆን የአዋጁ ረቂቅ የተለያዩ የአለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ደርጅቶች እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አዋጁ የዜጎችን የሰብኣዊ መብቶች አደጋ ውስጥ ስለሚከት መስተካከል እንደሚኖርበት ድምፃቸውን አሰምተው ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥት ትችቶቹን ከቋፍ ሳይከት አዋጁን በ2001ዓ.ም ከ547 የፓርላማ አባላቶቿ ውስጥ 378ቱ በተገኙበት በ268 የአዎንታ ድምጽ፣ በ91 ተቃውሞ እና በ1 ድምፀ ተአቅቦ የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ኅብረተሰቡን ከአደጋ ለመጠበቅ በሚል አወዛጋቢውን ሕግ አውጥቶ ማስፈጸም ጀምሯል፡፡
Zone9 young Ethiopian bloggers
አዋጁ በወጣበት ቀን “ባለራዕዩ” የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴት መለስ ዜናዌ የአዋጁን ትክክለኛነት (Ligitimacy) ለፓርላማው ሲያብራሩ “… አዋጁን ስናረቀቅ ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ እና ከአውሮፓ አገራት ጥሩ ጥሩውን ቃል በቃል….ለምሳሌ በነዚህ ሃገራት ባለው ሕግ አሸባሪ ብሎ የመፈረጅ ሥልጣን የሕግ አስፈፃሚው ሲሆን እኛ ግን የሕግ አውጪው ሥልጣን እንዲሆን አድርገናል…” ብለው ነበር፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር በዓለማችን የሕግ የበላይነት ከሰፈነባቸው አገራት የፀረ ሽብር አዋጁን “ቃል በቃል” መገልበጣቸው ሕጉን ትክክለኛ ሊያስብለው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሠራ የተፈጥሮ ሕግ (Universal law) እንደመኖሩ አንድ ሕግ ሲወጣ ሀገሪቷ ካላት ሁኔታ እና በሕጉ ከሚተዳደሩት ማኅበረሰቦች አንፃር መሆን እንዳለበት (Capable of being complied with) በማወቅ ይሁን ባለማወቅ ጠ/ሚኒስትሩ የዘነጉት መሠረታዊ የሕግ አወጣጥ መርሕ ነው፡፡ የሰው ልጅ የመኖር (የሕ.መ.አ.15*) እና ከማንኛውን የአካል አደጋዎች የመጠበቅ (የሕ.መ.አ.16*) በዓለማችን ላይ ሁሉ ዕኩል የሚሠሩ የተፈጥሯያዊ መብቶች አሉት፡፡ ነገር ግን እነዚህን መብቶች ለመጣስ በየሃገራቱ ብቻ አይደለም በየኅብረተሰቡ የተለያዩ አደጋዎች እንደመኖራቸው መብቶቹን ለማስጠበቅ የሚወጡት ሕጎች (እንደ ፀረ ሽብር ሕግ) ከቦታ ቦታ እና ከጊዜ ጊዜ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የተለያዩ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ሕግ ሲረቀቅ የሌላ ሀገሮች ተመሳሳይ ሕግጋት (raison d’etre) መመልከት ተገቢ ቢሆንም በሕጉ የሚተዳደረውን ማኅበረሰብ ጥያቄ መመለስ ዋነኛው አላማው ነው፡፡ (Law must deliberately meet one of the prevalent ‘needs’ of the society) የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ የራሱ የሆነ የአስተሳሰብ እና የአኗኗር ዘይቤ አለው፡፡ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ፣ እንግሊዝ ወይም አውሮፓ ዕኩል ለሽብር ጥቃት የተጋለጡ አገሮች አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ የፀረ ሽብር አዋጅም ኢትዮጵያን ከሽብር አደጋዎች ለመጠበቅ እንዲያስችል ተደርጎ መረቀቀ ይኖርበታል እንጂ ከሌላ ሀገር ሕጎች ላይ ቃል በቃል መገልበጥ የለበትም፡፡
የሰብኣዊ መብት የሚያስከፍል የሽብር ጥቃት በኢትዮጵያ?
የሰብዓዊ መብት መንግሥት በመልካም ፍቃዱ አይሰጠንም፣ የሰው ልጆች ሆነን ስለተፈጠርን ብቻ የምናገኘውና በቀለም፣ በዘር፣ በሀብት እና በመሳሰሉት ሳንለያይ ያለምንም አድሎ የምንጠቀመው በነጻ በእግዚያብሄር አማሳል ስለተፈጠርን ብቻ የሚኖረን መብት ነው፡፡ መንግሥት መብቱን ባይሰጠንም የመጠበቅ ኃላፊነቱ ግን የሱ፤ የሀገር (የመንግሥት) ኃላፊነት እንጂ የግለሰቡ (የእኛ) ኃላፊነትም አይደለም፡፡ የሰብኣዊ መብትን የመጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት ነው ስንል መብቶቻችን እንዳይገፈፉ በሕግ አግባብ የመጠበቅ፣ መብቶቻችን ሲገፈፉ አግባብ ባለው የፍርድ አካሄድ የማስጠበቅ እና ሕግ የተላለፈውን መቅጣት አለበት እንደ ማለት ነው፡፡ ችግሩ የሰብኣዊ መብቶቻችን የማስጠበቅ ኃላፊነቱ የመንግሥት እንደመሆኑ መብቶቻችንንም ለመጣስ የመጀመሪያው እራሱ መንግሥት ነው፡፡
ይሄም የሥልጣን ፍቅር ያሰከረው፣ ሥልጣን እና/ወይም መሣሪያ ከሕዝብ የሚበልጥ መስሎ የሚታየው መንግሥት ላይ በብዛት ይታያል፡፡ መንግሥት የሰብኣዊ መብቶች ሊጥስ ከሚችልባቸው አጋጣሚዎች ዋነኛው የኅብረሰቡን ጥቅም (Public interest) ለማስጠበቅ የተወሰኑ ግለሰቦች የሰብኣዊ መብት መጣስ ይኖርባታል በሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያው የፀረ ሽብር አዋጁም የብዙኃኑን ሠላም ለማስጠበቅ በሚል የግለሰቦችን ሰብኣዊ መብት እየጣሰ መፈፀም ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን የተላየዩ ሰብኣዊ መብቶችን የሚያስጥስ የሽብር አደጋዎች በኢትዮጵያ ውሰጥ የሉም፡፡ ይልቁንም ከአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ በዊኪሊኪስ ድረ ገጽ አማካኝነት ሾልኮ የወጣው መረጃ (Ref. No. #06ADDISABABA2708) ተፈፀሙ ከተባሉት የሽብር ጥቃቶች በጳጉሜ 1 ቀን 1998 ዓ.ም ተፈፀመ የተባለው ሦስት የቦንብ ጥቃት እራሱ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደፈፀማቸው እና ኤርትራንና ኦነግን ተጠያቂ እንዳደረገ ይገልጻል፡፡
የሌለን ሽብር መፍጠር ይልሃል ይህ ነው፡፡ ስለዚህ የሽብር ጥቃት በማያሰጋበት እና “አሸባሪ” በሌለባት ኢትዮጵያ የተለያዩ የሰብኣዊ መብቶችን እየገፈፉ የፀረ ሽብር አዋጅን ማስፈፀም ከአደጋ የሚጠብቀው ሕዝቡን ወይስ መንግሥትን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በመጀመሪያ የፀረ ሽብር አዋጁ በሕገ መንግሥት ውስጥ ከተካተቱት የሰብኣዊ መብቶች ውስጥ የትኛዎቹን ይጥሳል? የሚለውን መመለስ ያስፈልጋና ጥቂቶቹን እንሆ፡፡
ከፍተኛ ጥንቃቄ (Due Deligence) ለሰላማዊ ሰልፍ
የሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲታሰብ ንብረቶችን ማጥፋት፣ በፖሊስ ላይ ጥቃት መፈፀም እና የመሳሰሉት ወንጀል ከመሆናቸው ባሻገር ሠላማዊ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ይሸረሽሩታል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተግባራት ወንጀል ቢሆኑም ሽብር አይደሉም፡፡ ይልቁንም “ማንኛውንም ሰው ወይም ቡድን የፖለቲካ፣ ሃይማኖታዊ፣ ወይም የአይዲዎሎጂ ዓላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር… የሕዝብ አገልግሎት ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ፣ የያዘ፣ በቁጥጥር ስር ያደረገ፣ ያቋረጠ፣ ወይም ያበላሸ እንደሆነ…” የሽብር ድርጊት እንደተፈፀመ የፀረ ሽብር አዋጁ ይደነግጋል (የፀ.ሽ.አ.አ.3(6)*) ነገር ግን የሕዝብ አገልግሎት ማቋረጥ ኅብረተሰቡን ምን ዓይነት አሳሳቢ አደጋ፤ ለዛውም እንደ ሽብር የሚቆጠር አደጋ ውስጥ እንደሚጥል ግልጽ አይደለም፡፡ ደግሞም የሠላማያዊ ሰልፍ ሲደረግ በመቶዎች፣ በሺሕዎች ወይም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ በወጣበት የትራንስፖርት እና የመሳሰሉት የሕዝብ አገልግሎቶች ሊያቋርጥ ይችላል፡፡ የቴሌኮሙኒኪሽን፣ የመብራት ኃይል፣ የውኃና ፍሳሽ ወይም ሌላ የመንግሥት ሠራተኞች ተቃውሞ ኖሯቸው ከሥራ የመቅረት አድማ ቢያደርጉ የሕዝብ አገልግሎት ሊቋረጥ ይችላል፡፡ በዚህ ዓይነት የሠላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉት ሆኑ የሥራ መቆም አድማ ያደረጉት የሽብር ድርጊት ፈፀሙ ሊባል ነው? የሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት (የሕ.መ.አ.30(1)*) በተዘዋዋሪ ተገፈፈ ማለት ይሄ ነው፡፡ ለዚህም ነው የተለያዩ ባለሙያዎች እና ድርጅቶች አዋጁ የሽብር ድርጊቶችን ሲያብራራ አደናጋሪ (vague) እና ሰፊ (broad) ስለሆነ መሻሻል ይገባዋል እያሉ የሚጮሁት፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰፊ ክፍተት መተው በፍ/ቤቶች የተለያዩ ትርጉሞች እንዲሰጡት ከማድረጉ ባሻገር የፍትሕ ሚኒስቴር የፈለገውን ሰው እና/ወይም ድርጅት በሽብር ወንጀል ከሶ ችሎት ለመገተር መንገዱን ክፍት ያደረገዋል፡፡
የመረጃ ነጻነት እንደዋዛ
ታዋቅው የሕግ ሊቅ እና ፈላስፋ Seneca የሰው ልጅ ከተፈጥፎ ጋር በነጻነት ያለማንም ጣልቃ ገብነት መኖር ይኖርበታል ይላል፡፡
Man is a sprit and his ultimate goal is the perfection of his reason in that sprit. Because man is a rational animal, his ideal state is realized when he has fulfilled the purpose for which he was born. And what is it that reason demands of him? Something very easy – that he live in accordance with his own nature.
Man is a rational animal! የሰው ልጅ የሚያገናዝብ እንስሳ ነው፡፡ የሚያግናዛበው በአካባቢው ከሚያገኛቸው እውነታዎች አንፃር ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ስለፈለገው ነገር ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ከፈለው መረጃ ላይ፡፡ ያገኘውን መረጃ አገናዝቦ የፈለገው አቋም የመያዝ መብትም አለው፡፡ መንግሥትን ጨምሮ ማንም ሰው ይህንን ዕወቅ ይህንን አትወቅ እንዲለው አይፈልግም፡፡ የማወቅ፣ የማገናዘብ፣ አቋም የመያዝ ብቻ አይደለም አቋሙን ለፈለገው ሰው ያለምንም ፍርሐት የማሳወቅ መብት አለው፡፡ ምክንያቱም ሰው ነውና፡፡
መንግሥትን ከራሱ አማካሪዎች ይልቅ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የነጻው ፕሬስ ካልተቸው ሁሌም ትክክል ነኝ ማለቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ትክክል መሆን ሥልጣን ላይ ለመቆየት ብቸኛው አማራጭ ነውና፡፡ እንኳን በዚህ ፓርላማው፤ የአንድ ፓርቲ ግለሰቦች በሞሉበት ሀገር እና የጦፈ ክርክር ባለበት ፓርላማም የኅብረተሰቡ እና የፕሬስ ትችት ለመንግሥት የሥራ ወሳኝ ነው፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 6 እንዲህ ይለናል፡፡ “…የሽብር ድርጊት እንዲፈፅሙ ወይም ለመፈፀም እንዲዘጋጁ ወይም በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያበረታቸው ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ የሚገፋፋቸው እንደሆነ አድርገው ይረዱታል ተብሎ ሊገመት የሚችል መልዕክት ሆን ብሎ ወይም በግዴለሽነት ያተመ ወይም ያሳተመ እንደሆነ….” ሽብርተኝነትን ማበረታታት ስለሆነ ከ10 እስከ 20 ዓመት ያስቀጣል፡፡ የሽብር ድርጊትን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የሚያበረታታ መልዕክት ምንድነው? ለሚለው አዋጁ ለሽብር ድርጊት ይገፋፋል ተብሎ የሚገመት መልዕክት ነው ብሎ ይመልሳል፡፡ ማን ነው አንድን መልዕክት ለሽብር ይገፋፋል የሚለውን ግምት የሚሰጠው? መንግሥት ወይስ ማን? ከሽብር ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው መልዕክት ሲያስተላልፍ ማለት ሲቻል ሽብር ይገፋፋል ተብሎ የሚገመት መልዕክት ነው ብሎ እስከ 20 ዓመት እስር መቅጣት ለምን አስፈለገ? በዚህ ዓይነት አቃቢ ሕግ ሽብርን ያበረታታል ብሎ ካሰበ ማንኛውንም የመንግሥት ትችት የሽብር ድርጊትን አበረታታ ብሎ ሊከሰው ነው ማለት ይሆናል፡፡ ለዛውም የሽብር ድርጊት በሚያወዛግብ ሁኔታ በተብራራበት የሕግ ማዕቀፍ፡፡
ማበረታታት (Encouragement) ከሚል ማነሳሳት (Incitement) በሚል ጠንካራ እና ሕጋዊ መርሕ መተካት ይቻል ነበር፡፡ ማነሳሳት (Incitement) የወንጀል ሕጋችን ሲያብራራው “ሌላውን ሰው በመጎትጎት፣ ተስፋ በመስጠት፣ በገንዘብ፣ በስጦታ፣ በማስፈራራት ወይም በማናቸውም ሌላ ዘዴ አንድ ወንጀል እንዲያደርግ ያግባባ እንደሆነ…” አነሳሹ የሚቀጣው ወንጀሉ ቢያንስ ተሞክሮ (Attempt) እንደሆነ” (የወ.ሕ.አ.36(1)*) ነው ይላል፡፡ ሌሎች ወንጀሎችን ማነሳሳት እንደዚህ ባለው ጠባብ ሕግ ለዛውም የተባለው ወንጀል ዝግጅትን (Preparation) አልፎ ወንጀሉ ቢያንስ ከተሞከረ ብቻ (Attempt ላይ ከደረሰ) እያስቀጣ ሽብርን ያህል ለኅብረተሰቡ አደገኛ የሆነ ወንጀል “ሽብርን ያበረታታል ተብሎ ስለታሰበ” ብቻ እስከ 20 ዓመት ማስቀጣቱ አግባብ አይደለም፡፡
ይህ ሲባል የነጻው ፕሬስ የሕትመት መልዕክቶች በሙሉ ሽብርን አይቀሰቅሱም እና አያስቀጡም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የሚያስቀጣው መልዕክት ከሚያደርስው የአደጋ አጣዳፊነት (Imminent) እና ወሳኝነት (Neccessity) አንፃር መመርመር ይኖርበታል፡፡ አደገኛ መልዕክትን መተርጎም ለፍ/ቤቶች ብቻ ሳይሆን ጠበብ ባለ የሕግ ማዕቀፍ መካተቱ ለሀገሪቷ የሚጠቅሙትን መልዕክቶች በተቃራኒው አደገኛ ናቸው ብሎ ከመቅጣት ይሰውራልና ቢታሰብበት አይከፋም፡፡ ከዓለማችን የተሰባሰቡ የሕግ ሊቆች እና ከተባበሩት መንግሥታት የተሾሙ ባለሙያዎች በተገኙበት በተረቀቀው የጁሃንስፐርጉ መርሕ ላይ ለኅብረተሰቡ አደጋ የሚያጋልጡ መልዕክቶች ማስቀጣት ያለባቸው ሦስት ሁኔታዎችን (Pre conditions) ሲያሟሉ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ “መልዕክቱ አፋጣኝ አደጋን ለማድረስ የተሳበ ከሆነ (Immenint)፣ መልዕክቱ አደጋውን ማድረሱ እርግጥ ከኖነ (Probable) እና በመልዕክቱ እና በሚደርስው አደጋ መካከል የተቀራረበ ግንኙነት ካለው (Cause and Effect)” ናቸው፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁ ግን እነዚህን መዘርዝሮች ማሟላት አይደለም አንዱንም አያካትትም፡፡ እነ ውብሸት ታዬ፣ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ እና የመሳሰሉት ነገ ጠባ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ ለኅብረተሰቡ መረጃን በማድረስ፣ በመንግሥት ላይ ትችት በማቅረብ የሚሠሩ ታታሪ ጋዜጠኞች ናቸው ብለው የዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ሲሸልሟቸው የደከሙላት ኢትዮጵያ ግን የሽብር ድርጊትን አበረታታቹኋል ብላ ማረሚያ ቤት የላከቻቸው፡፡ አራሚዎቹን ወደ ማረሚያ፡፡ ይህ አካሄድ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 የተገለፀውን የአመለካከት እና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት ከመጣሱ ባሻገር ኅብረተሰቡ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ያለውን አመኔታ እንዲያጣ ምክንያት ሆኗል፡፡
በሃያማኖት ጣልቃ ገብነትን መቃወም እንደ ሽብር
መንግሥት ሕዝቡን ለመቆጣጠር እና ያለምንም ስጋት ሥልጣን ላይ ለመቆየት ካሉት አማራጮች ውስጥ ዋነኛው በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ በሃይማኖቱ አይደራደርም፣ የሃይማኖች አባቶች ትክክል ነው ያሉት የእግዚአብሔር/የአላህ ቃል ነውና ለቃሉ መገዛት ግድ ይሆናል፡፡ ፈጣሪ የሾመውን ፈጣሪ ያውርደው እንዲሉ፡፡ በጣልያን በ15ኛው ክፍለ ዘመን የተወለደው የሕግ ሰው Nicolo Machiavelli ለመሳፍንት መመሪያ በጻፈው The Prince በተሰኘው መጽሐፉ መንግሥት በሃይማኖት ሕዝቡን እንዴት መቆጣጠር እንደሚችል ሲገልጽ፤
…touching which all difficulties are prior to getting possession, because they are acquired either by capacity or good fortune, and they can be held without either; for they are sustained by the ancient ordinances of religion, which are so all−powerful,èandèofèsuchèaècharacterè thatè theèprincipalitiesèmayèbeè held no matter how their princes behave and live.
ይላል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም በችሎታ (Capacity) ወይም በተወዳጅነት (good fortune) ኅብረተሰቡን መቆጣጠር ስለማይችል፤ ከፋፍለህ ግዛ (Divide and rule) ከሚለው የማካቬሊ መርሕ በተጨማሪ በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ጣልቃ መግባቱ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ነገር ግን የሙስሊሙ ኅብረተሰብ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሃይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ (የ.ሕ.መ.አ.11*) መሆን አለባቸው በሚል ሰፊ ተቃውሞ ለማድረግ በቅርቡ ወኔውን አግኝቷል፡፡ መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ እየገባ ነው፣ የአሕባሽ አስተምህሮት ማስፋፋት ይቁም በሚል በመንግሥት ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሠላማዊ የሆነ ተቃውሞ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ነገር ግን መንግሥት በተግላቢሽ የሃይማኖታዊ መንግሥት የማቋቋም ድብቅ አጀንዳ እንጂ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የላቸውም በሚል ከ500,000 በላይ የሙስሊሙን ኅብረተሰብ የአዎንታ ፊርማ አግኝቶ የተቋቋመውን የኮሚቴ አባላት በፀረ ሽብር አዋጁ ከስሶ ጉዳዩ በፍ/ቤት በመታየት ላይ ያገኛል፡፡ የክርክሩ ውጤት (ውሳኔ) የሚተላለፈው በገለልተኛ ፍ/ቤት ይሁን በሕግ አስፈፃሚው አካል ቀጭን ትዕዛዝ (የፍ/ቤቶችን ገለልተኝነት ሳልገጽ ማለፍ አግባብ ስለማይሆን) ግልጽ ባይሆንም ከሕጉ አንጻር ነጻ የመውጣት ዕድል ቢኖራቸውም ካለው ነባራዊ ሁኔታ እና ከበፊት ተሞክሮዎች ጥፋተኛ ሊባሉ የሚችሉበት አጋጣሚ የሰፋ ነው፡፡
ለአደጋ የተጋረጠው የፍርድ አካሄድ (Due process of law)
የፀረ ሽብር ሕጉ ለመስፈጸም ማስረጃ ለማሰብሰብ በሚደረጉ ተግባሮች፣ በፍርድ ቤት በሚኖረው አካሄድ፣ እና በማረፊያ ቤቶች የተከሳሾች እና ከጉዳዩ ተያያዥነት አላቸው ብሎ ፖሊስ የጠረጠራቸውን ግለሰቦች የሰብዓዊ መብት እንደሚጣስ ልብ ይሏል፡፡
የወንጀል ተከሳሾች “ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍ/ቤት….የመሰማት” ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው (የሕ.መ.አ.20(1)*)፡፡ ነገር ግን በፀረ ሽብር አዋጁ የሚከሰሱ ተጠርጣሪዎች ከወንጀል ስነ ስርዓት ሕጉ 14 ቀን በመጨመር የጊዜ ቀጠሮ ትንሹ 28 ቀን እንደሆን ከመደንጉ ባሻገር ይህ ጊዜ እስከ 4 ወራት ሊዘልቅ እንደሚችል ይደነግጋል (የፀ.ሽ.ሕ.አ. 20(3)*)፡፡
ሌላው የፀረ ሽብር አዋጁ የሚጥሰው የግለሰብን የነጻንት መብት ሲሆን (Right to privacy) “በሽብርተኝነት የተጠረጠረን ሰው የስልክ፣ ፋክስ፣ የሬድዮ፣ የኤሊክትሮኒክስ፣ የፖስታ እና የመሳሰሉትን ግንኙነቶች ለመጥለፍ ወይም ለመከታተል…. ጠለፋውን ለማስፈፀም ወደ ማንኛውም ቤት ውስጥ በሚስጥር የመግባት… “መብትን ለፖሊስ እና ለደኅንነት መብቱን ይሰጣል (የፀ.ሽ.አ.አ.14(1)*)፡፡ በዚህ የተገኙትንም ማስረጃዎች በሚስጥር መጠበቅ እንዳለባቸውት ይደነግጋል (የፀ.ሽ.አ.አ.14(2)*)፡፡ ይህም የግል ሕይወት የመከበር እና የመጠበቅ የሰብኣዊ መብትን (የሕ.መ.አ.26) በግልጽ ከመጣሱ ባሻገር የተያዙት ማስረጃዎች በሚስጥር ሲጠበቁ አይታዩም፡፡ አኬልማዳ፣ ጀሀዳዊ ሃረካት እና የመሳሰሉት የኢቲቪ ዶክመንተሬዎች ማስረጃዎቹ በሚስጥር ከመያዝ ይልቅ ቀድሞ ተከሳሾችን ባደባባይ ለመወንጀል ጥቅም ላይ እንደዋሉ ያረጋግጣል፡፡ ይህም ወደ ሚቀጥለው የሰብኣዊ መብት ጥሰት ያሸጋግረናል፡፡
ማንኛውም ተከሳሽ በፍርድ ቤት ቀርቦ እና ማስረጃ ተሰምቶ ጥፋተኛ እስከሚባል እንደ ነጻ ግለሰብ መቆጠር (presumption of innocence until proven guilt) እንደሚኖርበት ሕገ መንግሥታችን ቢደነግግም (የሕ.መ.አ.20(3)*) በቴሌቪዥን ዶክመንተሪዎች እና የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ጭምር ተከሳሾች የሽብር ድርጊትን በመፈፀም ዙሪያ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል በሚል መግለጫዎች ሲሰጡ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የሙስሊሞች ጉዳይ ‹‹መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ›› ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጋ እና የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ የጅሃዳዊ ሃረካት በሚለው የዶክመንተሪ ፊልም የደንበኞቻችን ስም ጠፍቷል በሚል የ8 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያን በፍ/ቤት ለመጠየቅ የፍትሐ ብሐር ክስ እንደጀመሩ በቅርቡ ሰምተናል፡፡ ክርክሩ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን እንደተከሳሽ ማካተቱ የሕግ የበላይነትን ያሳየናልና በርቱ ብያለሁ፡፡
የሚስጥሪያዊነት ስነ ምግባር በሽብር ምርመራ…
የተለያዩ ባለሙያዎች ከሥራ ዘርፋቸው አንፃር የሚጠበቁባቸው የሥነ ምግባር ኃላፊነቶች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ምስጥራዊነት (Confidentiality) ነው፡፡ ነገር ግን አዋጁ የባለሙያዎቹን ሥነ-ምግባር ወደ ጎን በመተው፤ ለሽብር እንኳን የባለሙያ ሥነ-ምግባር የሰብኣዊ መብትም ይጣሳል ይለናል፡፡ አዋጁ በማስረጃ አሰባሰብ አካሄዱ “…[ፖሊስ] ለምርመራው የሚረዳው መሆኑን በሚገባ የሚያምንበት መረጃ ወይም ማስረጃ ከማናቸውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ ባለሥልጣናት፣ ባንክ፣ የግል ድርጅት ወይም ግለሰብ እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይችላል፡፡ መረጃ ወይም ማስረጃ የተጠየቀው ወገን መረጃውን ወይም ማስረጃውን የመስጠት ግዴታ አለበት” ይላል (የ.ፀ.ሽ.አ.አ.22*)፡፡ በዚህም ምክንያት ጠበቃ ደንበኛው የሕግ ወኪሌ ብሎ ያማከረውን፣ ሐኪም ታማማሚው ለሕክምና እንዲረዳው ብሎ የተናገረውን ሚስጥር ብቻ ሳይሆን የንስሐ አባት ይፀዩልኝ ዘንድ ብሎ የተነገራቸውን ጉድ ጭምር ለደኅንነት ወይም ለፖሊስ አንድም ሳይደብቁ የመናገር ግዴታ ይጥላባቸዋል፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁ፡፡
ለኢ-ፍትሐዊ ሕግ አንገዛም!!!
በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ትክክለኛ (Right) እና ፍትሐዊ (Just) ያልሆነ ሕግ ከመጀመሪያው አስገዳጅነት የለውም ይለናል፡፡ ሕብረተሰቡም ይህንን ሕግ የመቃወም ሕጋዊ ብቻ አይደለም የሞራልም ተጠያቂነት አለበት፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ሕግ ሲወጣ የኅብረሰቡን አመለካከት እና ጥያቄ ግምት ውስጥ ካልከተተ ሕጉ የመንግሥት እንጂ የሕዝብ አይሆንም፡፡
የመንግሥት ሕግ ደግሞ በጀርመኑ ናትዚ ጊዜ ያለውን ከፍተኛ ተግዳሮት አይተናል፡፡ የጀርመን ፕሮፌሰር Fuller ኢፍትሐዊ ውሳኔዎች የሚፈጠሩት በፍርድ ቤቶች ችግር ሳይሆን በዋነኛነት በሕግ አውጪዎቹ ድክመት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ሕጎች ይላሉ ፕሮፌሰር ፉለር Morality of duty ብቻ ሳይሆን Morality of Aspiration ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም ማለት አንድ ሕግ በኅብረሰቡ ዘንድ ሊያስተዳድረን ይገባል የሚል እምነት ከሌላቸው በግዴታ ብቻ በሕጉ መገዛታቸው በቂ አይደለም፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት እና አንዱ ከሌላው ጋር ያላቸውን ቁርኝትና እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡፡
The morality of aspiration…is the morality of the Good Life, of excellence, of the fullest realization of human powers…Where the morality of aspiration starts at the top of human achievement, the morality of duty starts at the bottom. It lays down the basic rules without which an ordered society is impossible, or without which an ordered society directed toward certain specific goals must fail of its mark.
ኢትዮጵያ ለሽብር ጥቃት ያን ያህል የሚያሰጋ ደረጃ ላይ እንደሌለች ሁላችንም የምናውቀው ኩነት ነው፡፡ በሱማሊያ ጦርነት መሳተፏ ከአልሻባብ ለሚሰነዘር ጥቃት ያጋልጣታል የሚል ስጋት ቢኖርም በአሁኑ ጊዜ ግን አሸባሪ ተብለው እየተፈረጁ የምናየው የሀገር ውስጥ ግለሰቦችን እና/ወይም ቡድኖችን እንጂ ከሱማሊያ የሚመጡትን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ምንም ጭቆና ቢደርስበት ከነበረው የረዥም ጊዜ የአስተሳሰብ ደረጃ (Moral standard) በዓለም አቀፍ ደረጃ የሽብር ድርጊት ተብለው የሚወሰዱትን እንደ አጥፍቶ ማጥፋት፣ የንፁሐንን ዜጋ ሕይወት ለመደራደሪያነት የማቅረብ ዓይነት ተግባራትን እንዳማይፈፅም እሙን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተራበበት ጊዜ እንኳን አመፅ/ሽብር አላስነሳም፡፡ ስለዚህ ለሽብር ጥቃት ርቃ የምትገኝውን ሀገር ሰፊ ክፍተት ባለው የፀረ ሽብር አዋጅ አፍኖ መያዝ ሥልጣንን መጠበቅ እንጂ ኅብረተሰቡን ከአደጋ ለመከላከል አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡ የራሴ ብሎ ሊገዛበት (Morality of Aspiration) ያልፈቀደው ሕግ በፓርላማ ስለፀደቀ ብቻ አስገዳጅነት ቢኖረው (Morality of duty) የፍትሕ ስርዓቱን ኅብረተሰቡ መተባበር አይደለም ጭራሽ እምነት እንዲያጣበት ይዳርገዋል፡፡
የሠላማዊ ሰልፍ እና የፕሬስ ነፃነቶችን ኅብረሰቡን ከአደጋ ለመጠበቅ በሚል በሰፊው መጣስ በተቃራኒው የኅብረተሰቡን የተፈጥሯዊ መብት እየጣሱ ኅብረተሰቡን አደጋ ውሰጥ መጣል ስለሚሆን ተግዶሮቱ ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለውም ትውልድ ነው፡፡ የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት መቃወም እና እስላማዊ መንግሥት ማቋቋም ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸውና የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ድምፅ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ድምፃችን ይሰማ፡፡ የተከሳሽን የሰብኣዊ መብቶች መጣስ እና የፍርድ ቤት አካሄዶችን ያለአግባብ ማጣመም እንደ ደርግ ያለምንም የፍርድ አካሄድ ግለሰቦችን ባደባባይ ከመቅጣት ስለማይተናነስ የሽብር ተጠራጣሪዎች ሕገ መንግሥታዊ መብት ይከበር፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁ ኢትዮጵያን “ከሽብር ጥቃቶች” ለመከላከል ታስቦ በልኳ የተሰፋ የሕግ ማዕቀፍ ስላልሆነ ብዙ ጥፋት ከማጥፋቱ በፊት በጊዜ መሻሻል እንደሚኖርበት ይህ ጽሑፍ የሚመለከታቸውን ሁሉ ያሳስባል፡፡
ታዋቂው የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጠስ በ70 ዓመቱ “ወጣቱን ያልሆነ አስተምህሮት በመስጠት” እና “በመንግሥት የበላይነትና አስተሳሰብ ባለመገዛት” በቀረበበት ክስ ከሳሾቹን ተቃውሞ ለችሎቱ ከሰው ሕግ በላይ ከሆነው ከተፈጥሯዊ ሕግ ጋር ለሚጣረስ ኢ-ፍትሐዊ ሕግ እንደማይገዛ በመግለጽ ያቀረበውን መከላከያ ፕላቶ Apology በሚለው ጽሑፉ ያሰፈረውን በመግለጽ ጽሑፌን ላጠቃልል፡፡ ሠላም እና ነጻነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ!!!
Socrates refuted the accusations made by his opponents. Justifying his teaching of philosophy and his consistency in continuing same work, he importantly said that it was good to obey the law and the order of a commander so long as they are just. But if the command was illegal or the laws unjust, then no man shall obey the order or the laws. From this argument he had also developed the principle that the command of god is more pious and just and as a result it is above and beyond any other human laws. Hence, it is wise to obey god’s command than human laws when they are in conflict. He believed that he was commanded by god to teach people philosophy, to question and convince them whenever he got the chance.
—-
* የምህፃረ ቃላት መፍቻ፡-
ሕ.መ – የኢፌድሪ ሕገመንግሥት አዋጅ ቁጥር 1/1987፣
የፀ.ሽ.አ – የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001፣
የወ.ሕ – የ1997ቱ የወንጀል ሕግ
አ. – አንቀጽ
—–
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው mikiyaslaw@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar