July 19, 2013
ከኢየሩሳሌም አርአያ
ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከአቶ ገ/ዋህድ፣ አቶ ነጋና ምህረተአብ ጋር በመመሳጠር በሶስት መርከብ ስሚንቶ አስጭነው አገር ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል መፈፀማቸውን ምንጮች አጋለጡ። በተከለከለ ፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ አገር ቤት የገባው ስሚንቶ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ትርፍ አዜብና ግብረአበሮቻቸው እንደዛቁበት ያረጋገጡት ምንጮቹ፣ አያይዘውም ጉዳዩ በደህንነት ሹም አቶ ጌታቸው አሰፋ እጅ እንደገባ አስታውቀዋል። በሕገወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ በመመደብና አስፈላጊውን ትእዛዝ በመስጠት እንዲሁም የጥቅም ተካፋይ በመሆን ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት አዜብ መስፍን ከዚህ ድርጊታቸው በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ከስሚንቶው ጋር በተያያዘ ተመስርቶ የነበረውን ክስ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን የጠቆሙት ምንጮች፣ ይህና ሌሎች ተያያዥ የወንጀል ድርጊቶችን የሚያስረዱ ማስረጃዎች በአቶ ጌታቸው እጅ እንደገቡ አረጋግጠዋል። አቶ ነጋ ገ/እግዚያብሄር በኮንትሮባንድ ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ አገር ውስጥ ያስገቧቸው የህክምና መሳሪያዎች ተይዘው ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ ክሱ እንዲቋረጥ ያደረጉት አዜብ መሆናቸውን የገለፁት ምንጮቹ፣ በተለያዩ ጊዜያት የገቡና የነጋ ገ/እግዚያብሄር ንብረት የሆኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ያለቀረጥ እንዲገቡ በማድረግ አዜብ መተባበራቸውን አያይዘው ገልፀዋል። ጉዳዩም «ክስ በማቋረጥ..» በሚል በሰነድ ተደግፎና ከሌሎች መሰል ድርጊቶች ጋር ተያይዞ በታሳሪዎች ላይ ክስ የቀረበ ቢሆንም፣ ዋናው ተዋናይ ግን አዜብ ሳይጠየቁ መቅረታቸው አነጋጋሪ መሆኑን ምንጮቹ አልሸሸጉም። ከስሚንቶው ጋር በተያያዘ አስተያየት የጠየኳቸው ታዋቂ የሆኑ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ ፥ « መንግስት ስለ ፍራንኮ ቫሉታ ሕግ አውጥቷል፤ ይህን በመተላለፍ ሶስት መርከብ ስሚንቶን የሚያክል ነገር በታሳሪዎቹ ብቻ ሊፈፀም አይችልም፤ ከዚህ ሕገወጥ ድርጊት በስተጀርባ ትልቅና ቁልፍ ስልጣን ያለው ሰው እጁ እንዳለበት ግልፅ ነው።» ብለዋል።
በተያያዘም ስለ ነጋ ገ/እግዚያብሄርና ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ የጀርባ ታሪክ በተመለከተ ምንጮቹ ተከታዩን መረጃ አስቀምጠዋል፤ “ ሕወሐት/ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ የአቶ ነጋ ስራ የመኪና ድለላና ኮረዶችን ከባለስልጣናት ጋር የማገናኘት የድለላ ተግባር ላይ ተሰማርቶ እንደነበረ ይገልፃሉ። በተለይ ሴቶችን እየመረጠ ለበርካታ የገዢው ሹማምንት ለወሲብ ከማቅረብ ጎን ለጎን የሕወሐት ቁልፍ ባለስልጣናትን በእጁ የማስገባት አጋጣሚ ፈጥሮለታል ፥ ይላሉ ምንጮቹ። ከባዶ ተነስቶ ሚሊየነር የሆነበት ምስጢሩ አዜብ መስፍን መሆናቸውን ያሰምሩበታል። ለዚህም «ነፃ ትሬዲንግ፣ ባሰፋና…» ሌሎች ከፍተኛ የቢዝነስ ተቋማቱና በሕገወጥ የዘረፋ ተግባር በድፍረት ተሰማርቶ መቆየቱን ከሞላ ጎደል ይጠቅሳሉ። በባለስልጣናቱ ተረማምዶ ከአዜብ ጋር በፈጠረው <ልዩ ቁርኝት> የተገኘ ሃብት እንደሆነ ይገልፃሉ። ከአዜብ ጋር በማሌዢያና ለንደን የፈፀሟቸው አስነዋሪ ተግባራት የሚያሳዩ የምስል ማስረጃዎች በደህንነት ሃላፊው እጅ እንደገቡ የጠቆሙት ምንጮቹ፣ የሁለቱን ግንኙነት በተመለከተ አብዛኛው የሕወሐት አመራር ጠንቅቆ እንደሚያውቀው አስታውቀዋል። አቶ ነጋ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ማመን ተስኗቸው ከማንገራገራቸው ባሻገር፥ «..ለአዜብ ስልክ እንድደውል ፍቀዱልኝ?» በማለት መማፀናቸውንና ደህንነቶቹ እንዳልተቀበሏቸው ምንጮቹ አመልክተዋል። በሌላም በኩል ከአዜብ ጋር ተመሳሳይ <ግንኙነት> ያላቸው ሌሎች ሁለት ባለሃብቶች፥ አንዱ 40 ሚሊዮን የፈጀ ባለስድስት ፎቅ የቢዝነስ ተቋም (ቦሌ ከሜጋ አጠገብ) አዜብ በለገሱት ገንዘብ እንዲገነባ ሲደረግ፣ ከዚህ ግለሰብ ጋር በተደጋጋሚ በዱባይ በውቂያኖስ ላይ በተገነባውና የቱጃሩ አልወሊድ ቢንጣለል ንብረት በሆነው “ኪንግደም” ባለ4 ኮከብ እጅግ ዘመናዊ ሆቴል እንደተገናኙ፣ እንዲሁም ሌላኛው የአንድ ቢሊየን ብር ባለሃብት ሆኖ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ አዜብ ማድረጋቸውን ምንጮቹ አጋልጠዋል።
የአቶ ገ/ዋህድ ማንነት በተመለከተ ምንጮቹ ይህን ይላሉ፤ « ገ/ዋህድ የኢሰፓ አባል ሆኖ በአስመራ እስከ 1982ዓ.ም ያገለግል ነበር። በዚሁ አመት መጨረሻ በራማ በኩል አድርጎ ሕወሐትን ተቀላቀለ። በወቅቱ በመቀሌ እንዲቋቋም በተደረገውና የቀድሞ የደርግ ከፍተኛ መኮንኖች (ምርኮኛ) የተካተቱበት <ኢዴመአን> የተባለ ድርጅት መስራች አባል ነበር – ገ/ዋህድ። በ1983 ዓ.ም የሁለት ሳምንት ወታደራዊ ስልጠና ወይም በድርጅቱ አጠራር “ተአለም” ከወሰደ በኋላ በአጋጣሚ ፓርቲው መላ አገሪቱን እንደተቆጣጠረ ምንጮቹ ያመለክታሉ። በሲቪል ሰርቪስ አልፎ ደቡብን ከጀርባ እንዲመሩ ከተመደቡት አቶ ቢተው በላይ ጋር በአዋሳ ተመደበ። በ1993ዓ.ም በተፈጠረው የፓርቲው መሰንጠቅ አመቺ አጋጣሚ የተፈጠረለት ገ/ዋህድ የክልሉን ፕ/ት አቶ አባተ ኪሾን፣ ቢተው በላይና ሌሎችም እንዲታሰሩ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫወተ። ለዚህ ታማኝነቱ የላቀ ቦታ በመለስ ማግኘት እንደቻለና ከዛ በኋላ በየቀኑ ከአዜብና መለስ ጋር በስልክ ይገናኝ እንደነበረ በፈለገው ጊዜ ቤተመንግስት ይገባና ይወጣ እንደነበረ ምንጮቹ አረጋግጠዋል። በአዜብ መልካም ፈቃድ በጉምሩክ ወሳኝ ስልጣን እንዲጨብጥ መደረጉንም አክለው ገልፀዋል። ከአዜብና ሸሪኮቻቸው ጋር በመነጋገርና በመመሳጠር ስሚንቶና ሌሎች ቁሳቁሶች በህገወጥ መንገድ ቀረጥ ሳይከፈልባቸው አገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ ከፍተኛ ሚና የተጫወተው ገ/ዋህድ፣ በሚሊዮን የሚገመት ሃብት ከዘረፋው እንዳተረፈም ተመልክቷል። ባለቤቱ ኮ/ል ሃይማኖትም እንዲሁ አዜብ በሚመሩት የሴቶችና ፀረ-ኤድስ ተቋም በምክትል ሃላፊነት እንዲመደቡና በየአመቱ ከአሜሪካ ብቻ እስከ 240 ሚሊዮን ዶላር በእርዳታ መልክ የሚገኘውን ገንዘብ በግልፅ በመዝረፍ ተባባሪ ሆነው መቆየታቸውን ምንጮቹ አስታውቀዋል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar