ዛሬ ከቀኑ 8፡00 በአራዳ ምድብ ችሎት ሐብታሙ አያሌው ዳንኤል ሺበሺና የሺዋስ አሰፋ እንደሚቀርቡ በመነገሩ ብዛት ያላቸው ሰዎች ቀደም ብለው በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ተገኝተው ነበር፡፡ፖሊስ በፍርድ ቤቱ የተሰጠውን የቀጠሮ ሰዓት አክብሮ እስረኞቹን ማቅረብ በመቻሉ ላይ ብዙዎች ስጋት የነበራቸው ቢሆንም አልተሳሳቱም፡፡
መደበኛው የስራ ሰዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ከፍተኛ ታጣቂ ሃይል የፍርድ ቤቱን ቅጥረ ግቢ ተቆጣጠረው ከደቂቃዎች በኋላም አንድ ማንነቱን ቀደም ብለን ለማወቅ ያልቻልነው ቀጠን ያለ ወጣት እጆቹን ታስሮ ወደ ችሎት ገባ፡፡በኋላ ላይ ማረጋገጥ እንደቻልኩት ወጣቱ ዘላለም የሚባል ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ መርሀ ግብር ተማሪ ነበር፡፡ፖሊስ በተመሳሳይ መልኩ እነ ሐብታሙን በያዘበት ዕለት በቁጥጥር ስር መዋሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በመለጠቅም ዳንኤል ሺበሺ ሁለት እጆቹ በካቴና ታስረው ነጠላ ጫማ ፣ጥቁር ሱሪና ቱታ ጃኬት ተላብሶ ወደ ውስጥ ዘለቀ፡፡
ከጺሙ ማደግ በስተቀር ዳንኤል ፊትና አካል ላይ ምንም አይነት ለውጥ አይታይም፡፡ስሙን እየጠሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ አድናቆታቸውን ለሚገልጹለት ሰዎች ጥርሱን ብልጭ እያደረገ አጸፌታውን ከመመለስ ውጪ ምንም አልተናገረም፡፡
ከጺሙ ማደግ በስተቀር ዳንኤል ፊትና አካል ላይ ምንም አይነት ለውጥ አይታይም፡፡ስሙን እየጠሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ አድናቆታቸውን ለሚገልጹለት ሰዎች ጥርሱን ብልጭ እያደረገ አጸፌታውን ከመመለስ ውጪ ምንም አልተናገረም፡፡
የዳንኤልን ችሎት ለመከታተል ጋዜጠኞችና ቤተሰቦቹ ጥያቄ አቅርበው አይቻልም የሚል ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም ጉዳዩን የተመለከቱት ሴት ዳኛ ቤተሰቡ እንዲገባ በማዘዛቸው ባለቤቱ ችሎቱን ተከታትላለች፡፡
የዳንኤል ጉዳይ እየታየ በነበረበት ሰዓት የሺዋስ አሰፋን የያዘችው መኪና ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ደረሰች፡፡ለደቂቃዎች ያህልም የሺዋስ በመኪናው ውስጥ እንዲቆይ ተደረገ፡፡ዳንኤልና ዘላለም እንደጨረሱና ግቢውን እንዲለቁ ከተደረጉ በኋላ የሺዋስ እንዲገባ ተደረገ፡፡ሙሉ ነጣ ያለ ቱታ ያጠለቀው የሺዋስ ግቢው ውስጥ እንደገባ ደመቅ ያለ ጭብጨባና በርታ የሚሉ መልእክቶች ጎረፉለት፡፡ፖሊሶች በጭብጨባውና በመልእክቶቹ ደስተኞች አለመሆናቸውን ቢገልጹም ከውስጥ ፈንቅለው የሚወጡ ስሜቶችን በቁጣና ማስፈራሪያ ሊያስቆሙ እንደማይችሉ የተረዱ ይመስሉ ነበር፡፡
የሺዋስ እንደሁልገዜው ዘና ያለና የተረጋጋ ነው፡፡ፈገግታውን በመርጨትና ሰላምታ በመለገስ የታሰሩ እጆቹን እያወዛዘወዘ ችሎት ገባ፡፡የሺዋስ የውስጥ ጉዳዩን ከውኖ እንደጨረሰም በተመሳሳይ የወዳጆቹና የትግል አጋሮቹ ጭብጨባና አድናቆት ታጅቦ ግቢውን ለቀቀ፡፡
በመጨረሻም ሐብታሙ አያሌው ወደ ውስጥ እንዲገባ ተደረገ፣ ሐብታሙ እግሮቹ ግቢውን እንደረገጡ ተሰብስበው ለጠበቁት ሰዎች ጥልቅ ፈገግታውን በመለገስ ሰላምታ አቅርቧል፡፡‹‹እንወድሃለን፣አይዞን››የሚሉ ቃላት ከደማቅ ጭብጨባ ጋር በግቢው አስተጋቡ፣ አጃቢዎቹም ፈጠን እንዲል እየወተወቱት ችሎት አስገቡት፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar