søndag 17. august 2014

የአንድነት ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አምስት አባላት ከፕሬዚዳንቱ ጋር አልተግባቡም

UDJአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ከአሥራ አምስቱ ሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል አምስቱ ከፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ጋር ባለመግባባታቸው ከካቢኔ ራሳቸውን አገለሉ፡፡
ራሳቸውን ከሥራ አስፈጻሚነት ያገለሉት አባላት የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክሌ በቀለ፣ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በላይ ፍቃዱ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ፣ የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ሥዩምና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዳዊት አስራዱ ናቸው፡፡
አቶ ዳንኤል ተፈራ፣ ‹‹እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው በአጠቃላይ ከፕሬዚዳንቱ አመራር ጋር በተያያዘ ጉዳይ ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹በትግሉ በሚሰጡት አመራር ልዩነት አለን፡፡ ፕሬዚዳንቱ እየሰጡት ያሉት አመራር ወደፊት ያራምዳል ብለን አናምንም፡፡ በአመራራቸው ሳናምን ደግሞ መቀጠል አንችልም፡፡ ለዚህ ነው ራሳችንን ያገለልነው፤›› በማለት ያብራሩት አቶ ዳንኤል፣ ‹‹ከብሔራዊ ምክር ቤት አባልነትና ከፓርቲው አባልነት ራሳችንን አላገለልንም፡፡ በቀጣይም ኢንጂነሩ ለካቢኔ አባላትን የሚያመጡዋቸውን ሰዎች እንደግፋለን፤›› ብለዋል፡፡
የፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው በበኩላቸው፣ ‹‹አንድነት የሚመራው በተቋም ነውና የሰዎች መልቀቅና መውጣት እንደ ትልቅ ነገር መታየት የለበትም፤›› ብለው፣ ‹‹ፓርቲው የሚከተለው የሊበራል ርዕዮተ ዓለም ግለሰቦች ለሥራ አስፈጻሚነት መመረጥና መውጣትን የሚያጐናፅፍ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር ጉዳዩ እንዲታይ ነው የምፈልገው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
የተፈጠሩትን አለመግባባቶችና ልዩነቶች በውይይት ለመፍታት ተሞክሮ ነበር ወይ በሚል ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ኢንጂነር ግዛቸው ሲመልሱ፣ ‹‹ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ውይይት አልተካሄደም፤›› በማለት፣ ‹‹ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ከውህደቱ በፊት ንቁ እንደነበርና ላለፉት ሁለትና ሦስት ወራት አዲስ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ሥራ አስፈጻሚና ምክር ቤት ለመመሥረት በነበረው ሒደት ምንም ዓይነት ልዩነት የተፈጠረበትና የተወያዩበት ሁኔታ አልነበረም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን ፕሬዚዳንቱ ይህን ቢሉም አቶ ዳንኤል ግን ውይይቶች መኖራቸውን አስታውሰው፣ ‹‹በአጠቃላይ የአካሄድ ሥልቱ ላይ ልዩነቶች አሉን፡፡ እነዚህ ልዩነቶች እንዲፈቱ ደግሞ በሊቀመንበሩ በኩል ቁርጠኝነት ያጣን ስለመሰለን ነው ይህን ውሳኔ የወሰንነው፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢንጂነር ግዛቸው ‹‹ጉዳያቸውን ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅርበናል ያሉት ነገር ትክክል ከሆነ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይወስናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕይታ ካላቸው ሥራ አስፈጻሚው ጋር አቅርበው ተወያይተን ነው መወሰን ያለብን፤›› ብለዋል፡፡ የዲሞክራሲ ባህል የሚሳተው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በቅርቡ የተጀመረውን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከአንድነት ፓርቲ ጋር ሊያደርገው የነበረውን ውህደት በተመለከተ ይህ አሁን የተላለፈው ውሳኔ ጥላውን አያጠላበትም ወይ የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበላቸው አቶ ዳንኤልም ሆነ ኢንጂነር ግዛቸው ምንም ተፅዕኖ እንደማይኖረው ገልጸው፣ ምርጫ ቦርድ የመኢአድን ምልዓተ ጉባዔ የማጣራት ጉዳይ አጠናቆ ፈቃድ በሚሰጥበት ወቅት የሚከናወን እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና የአንድነት ፓርቱ የተወሰኑ አባላት በማኅበራዊ ድረ ገጽ በተለይም በፌስቡክ ባደረጓቸው ጭቅጭቆች በመሀላቸው ክፍተት እንደተፈጠረ አመላካች ቢመስልም፣ ከኢንጂነር ግዛቸው ጋር ካልተግባቡት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ዳንኤል የፌስቡክ ጉሽሚያው እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar