søndag 24. august 2014

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሀብታቸውን በግልጽ እንዲለዩ የዓለም ባንክ አሳሰበ

Ethiopian Electric Power Corporationየቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት ተከፍሎ የተፈጠሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ሀብታቸውን በግልጽ ለይተውና ተካፍለው የየራሳቸውን የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ የዓለም ባንክ ማሳሰቡን ምንጮች ገለጹ፡፡
የዓለም ባንክ ማሳሰቢያውን የሰጠበት ምክንያት ለአገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት (Grid) ማጠናከሪያና ማስፋፊያ የሰጠው ብድር በአግባቡ ሥራ ላይ እየዋለ መሆኑን ለማረጋገጥ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
እ.ኤ.አ. በግንቦት 2012 የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት ማጠናከሪያ ፕሮጀክት የ200 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል፡፡
በስምምነቱ መሠረት የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የፕሮጀክቱ ፈጻሚ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ መሆን የጀመረው እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 2013 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ሥራው ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን ለሁለት በመክፈል ራሳቸውን የቻሉ ሁለት ተቋማትን ፈጥሯል፡፡ የተፈጠሩት ሁለት ተቋማት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኢንጂነር አዜብ አስናቀ የሚመራ ሲሆን፣ ኃላፊነቱም የኃይል ማመንጫ ግንባታዎችን እንዲሁም የመስመር ዝርጋታዎችን የተመለከተ ነው፡፡ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል ሥርጭትንና ጥገናን የተመለከተ ኃላፊነት ተሰጥቶት ማኔጅመንቱም በሁለት ዓመት ኮንትራት ለህንድ ኩባንያ ባለፈው ዓመት መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት መከፈሉ የኃላፊነት መዛባትን ያስከትላል የሚል ሥጋት የገባው የዓለም ባንክ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር ወዲያውኑ ውይይት ማድረጉን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
የተደረገው አዲስ አወቃቀር የፕሮጀክት ትግበራውን ያስተጓጉላል፣ ተጨማሪ ወጪ ያስከትላል፣ በፕሮጀክቱ ከሚሳተፉ ኮንትራክተሮች ጋር ግጭት ይፈጥራል በሚል በቀረበ ሐሳብ መሠረት ቀድሞ በተፈረመው የብድር ስምምነት ውስጥ የሚካተት የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ፕሮጀክቱ መቀጠሉን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ እስኪፈረም ድረስ መጠነኛ የሥራ መጓተት መፈጠሩን ለመረዳት ቢቻልም፣ አሁንም ቢሆን በሚፈለገው ፍጥነት ፕሮጀክቱ እየሄደ አለመሆኑን ምንጮች ያስረዳሉ፡፡
ለአብነት ያህልም የዓለም ባንክ ለፕሮጀክቱ ከፈቀደው 200 ሚሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ፣ ፕሮጀክቱ በተጀመረ በአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ውስጥ የተጠቀመው ዘጠኝ በመቶውን ብቻ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
ሁኔታው ያሳሰበው የዓለም ባንክ ከሁለት ሳምንት በፊት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች ጋር ፕሮጀክቱን በመገምገም ማሳሰቢያዎችን መስጠቱን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
የኢትዮጵያ አሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ግልጽ የሆነ የሀብት ክፍፍል አድርገው ባለመለያየታቸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፋይናንስ አማካሪ ድርጅት በመቅጠር ሀብታቸውን እንዲለያዩና ግልጽ የሆነ የየራሳቸው የሒሳብ መዝገብ እንዲፈጥሩ ማሳሰቡን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቱን ተግባራዊ በሚያደርግበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ትብብርን የሚሹ ጉዳዮች የሚኖሩ በመሆናቸው እነዚህ ትብብር የሚሹ አካባቢዎች በግልጽ እንዲለዩ ባንኩ ማሳሰቡ ታውቋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀን ለማግኘት የተደረገው ጥረት መሳካት አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዋየር ቢዝነስ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ቢትወደድ ገብረ አሊፍ ሥራው በአግባቡ እየተሠራ መሆኑንና በጥሩ ደረጃ ላይም እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡
‹‹ሥራውን ተከፋፍለናል፡፡ ሥራውን ስንከፋፈል ሁሉም ወደሚመለከተው ይሄዳል፡፡ ነገር ግን አብሮ የመሥራትና የመተባበር ጉዳይ የሚቀር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሥራ ተከፋፈልን እንጂ ፍቺ አይደለም የፈጸምነው፡፡ እንዲህ ብንረዳው ይሻላል፤›› ብለዋል፡፡
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከመፍረሱ በፊት ከሰጣቸው ብድሮች መካከል ለየኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት የሚውል ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ይገኝበታል፡፡ ነገር ግን ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ጊዜ በመግባባት እየተከናወነ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar