lørdag 16. august 2014

የሎሚ መጽሔት አሳታሚ ጋዜጠኛ ግዛው ታዬ በ50ሺህ ብር ዋስ ተለቀቀ

በሃገር ቤት ዛሬ ታትሞ የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደዘገበው ፍትህ ሚኒስቴር የወንጀል ክስ ከተመሠረተባቸው 6 የሚዲያ ተቋማት መካከል የሎሚ መጽሔት አሣታሚና ባለቤት በትናንትናው እለት ፍ/ቤት ቀርበው በ50ሺህ ብር ዋስ የተለቀቁ ሲሆን የፋክትና የ“አዲስ ጉዳይ” አሣታሚዎች ባለፈው ረቡዕና ሃሙስ ባለቤቶች በሌሉበት ክሣቸው ቀርቧል፡፡
ፎቶ - ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ
ፎቶ – ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ

የ“ሎሚ” መፅሄት አሳታሚና ባለቤት አቶ ግዛው ታዬ፤ ክሱ የደረሰኝ ከ3 ቀን በፊት በመሆኑ ከህግ ባለሙያ ጋር ተማክሬ እንድቀርብ ጊዜ ይሰጠኝ ሲሉ በፍ/ቤቱ ያመለከቱ ሲሆን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ክሱ ከደረሳቸው ጊዜ ጀምሮ ያለው ቀን ለመዘጋጀት በቂ ስለሆነ ፍ/ቤቱ በቀጥታ ክሱን መስማት ይጀምር ሲል ተከራክሯል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ሲያደምጥ የቆየው ችሎቱ፤ ሐምሌ 30 ወጪ የተደረገው የፍ/ቤቱ መጥሪያ ነሐሴ 6 ለተከሳሹ እንዲደርሳቸው መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ገልፆ ተከሳሹ የቀረበባቸውን ክስ በበቂ መከላከል እንዲችሉ ከህግ ባለሙያቸው ጋር ተማክረው ነሐሴ 14 እንዲቀርቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
የሎሚ መጽሔት ሰኔ 6 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው እትም ላይ “በአለም በጨቋኝነቷ አቻ የማይገኝላት የሚዲያ ምህዳር በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በቀረበው ጽሑፍ፤ ከ2007 ዓ.ም ምርጫ በፊት አዋጪ የሚሆነው በአመጽ በመደራጀት የሃይል ተግባር መፈፀም ሊበረታታ እንደሚገባ በመጥቀስ ለአመጽ የሚያነሳሱ ጽሑፎችን አትመው በማውጣት በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ መሰናዳት ተከሰዋል ይላል – የአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር፡፡
በመፅሄቱ ላይ በሁለተኛነት የቀረበው ክስ የካቲት 2 ቀን 2006 ዓ.ም ታትሞ በወጣው የ“ሎሚ እትም ላይ “የአሸባሪነት ፈርጦች” በሚል ጽሑፍ፤ በሽብር ህግ ተከሰው የተቀጡ ተከሳሾች በህዝብ የሚወደዱና ለገዢ ፓርቲ ተቀናቃኝ በመሆናቸው ብቻ በግፍ የተቀጡ ንፁሀን እንደሆኑ የሚያስመስል ሀሰተኛ ወሬ አትሞ በማውጣት በሃሰት ወሬዎች ህዝብን የማነሳሳት ወንጀል መፈፀማቸውን ያመለክታል፡፡ የፍትህ ሚኒስቴር አቃቤ ህግ በሚዲያ ተቋማቱ ላይ ከነሐሴ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ክስ ማቅረብ የጀመረ ሲሆን ባለፈው ረቡዕ የ“ፋክት” መጽሔት፣ ሃሙስ የ“አዲስ ጉዳይ” መጽሔት እንዲሁም በትናንትናው እለት የ“ሎሚ” መጽሔት አሣታሚና ባለቤት ላይ የተመሠረተው ክስ ለፍ/ቤቱ ቀርቧል፡፡ በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይም ነሐሴ 20 ክስ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡
በ“ፋክት” መጽሔት አሣታሚና ባለቤት ላይ የቀረቡት ሁለት ክሶች ሲሆኑ የመጀመሪያው በተለያዩ ዕትሞች “የከተማ አብዮት”፣ “የፈራ ይመለስ”፣ “የቁልቁለት መንገድ”፣ “የግፉአን እድሜ ምን ያህል ይረዝማል” እንዲሁም “የፍትህ እጦት አመጽ ይጣራል” በሚል በታተሙ ጽሑፎች፣ ተከሣሾቹ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በአመጽ ለማፍረስ አመጽ የሚያነሳሱ ጽሑፎችን ለህዝብ እንዲደርስ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ቅስቀሳ ያካሄዱ በመሆኑ በፈፀሙት መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ መሰናዳት ወንጀል መከሰሳቸው ተመልክቷል፡፡
ሁለተኛ ክስ “ሽብርተኝነትና የቀለም አብዮት፣ የኢህአዴግ ስጋት ወይስ የምርጫ መጨፍለቅ ቅድመ ዝግጅት” እና “ዘመቻ የሰላማዊ ትግል ግባት” በሚል ርዕስ ስር በፃፋቸው ጽሑፎች ሀሰተኛ ዘገባ አትሞ በማሠራጨት በስርአቱ ላይ ህዝቡ እምነት እንዲያጣ የሚያደርግ የሀሰት ወሬዎችን በማውራት ህዝብን በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸው ተጠቁሟል፡፡ 1ኛ ተከሳሽ የሆኑት የ “ፋክት” አሳታሚ ፋጡማ ኑርዬ ይማም ፍ/ቤት ያልቀረቡ ሲሆን ፖሊስም “ለተከሳሽ በስልክ ነግሬያቸዋለሁ፤ ነገር ግን በአካል ላገኛቸው አልቻልኩም፤ ይዞ ለመቅረብ ቀጠሮ ይሰጠኝ” ሲል ባመለከተው መሠረት ፍ/ቤቱ ተከሳሿን ፖሊስ በቀጠሮው እለት ይዞ እንዲቀርብ በማዘዝ ክሱን ለመስማት ለነሐሴ 12 ቀጠሮ ይዟል፡፡
ከትላንት በስቲያ በዋለው ችሎት፤ “የአዲስ ጉዳይ” መጽሔት አሣታሚ በሆነው ሮዝ አሳታሚዎች ኃ/የተ.የግ.ማህበርና በስራ አስኪያጁ እንዳልካቸው ተስፋዬ አርጉ ላይ ክስ የቀረበ ሲሆን በሁለት የተለያዩ ህትመቶች ላይ የተስተናገዱ ጽሑፎች በወንጀል ፍሬነት ተጠቅሰዋል፡፡
ተከሣሹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተሣትፈውበታል የተባለው ወንጀል “እንደማይመለከትህ ስታስብ” በሚለው ጽሑፍ “ህዝበ ሙስሊሙን ለማነሳሳት የአመጽ ቅስቀሳ በማድረግ” እንዲሁም “በኦሮሚያ ጊዜ ጠብቀው የሚፈነዱ ቦንቦች” በሚል ርዕስ ስር በተስተናገደ ጽሑፍ በ “ኦሮሚያ የሚገኙ ወጣቶች በህገ መንግስታዊ ስርአቱ ላይ እንዲያምፁ በማነሳሳት” የሚል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
ተከሣሽ በእለቱ ባለመቅረባቸው ፍ/ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ በጋዜጣ ተጠርተው እንዲቀርቡ፣ ያዘዘ ሲሆን ካልቀረቡ ጉዳያቸው በሌሉበት ይታያል ሲል ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ መዝገቡን ለነሐሴ 18 ቀጥሯል፡፡
በመንግስት የወንጀል ክስ የቀረበባቸው ቀሪዎቹ የግል የሚዲያ ተቋማት የ “እንቁ”፣ የ “ጃኖ” መጽሔትና የ “አፍሮ ታይምስ” ጋዜጣ አሣታሚዎች፤ የተመሠረተባቸው ክስ በፖሊስ በኩል የደረሳቸው ሲሆን ሶስቱም ለነሐሴ 20 ፍ/ቤት እንዲቀርቡ መቀጠራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ“ጃኖ” መጽሔት አሣታሚ አስናቀ ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ስራዎች ኃላ/የተ/የግ/ማህበርና ባለቤቱ አስናቀ ልባዊ፤ ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው ዕትም “ህዝቡ አንገቱን ደፍቶ የሚኖረው ለምንድነው?” በሚል ርዕስ በተስተናገደው ጽሑፍ፤ መንግስት በዜጐች ላይ በደል እየፈፀመባቸው በማስመሰል ህዝብ በመንግስት ላይ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲኖረው የሚያደርግ የሃሰት ወሬ በማሰራጨት ህዝብን በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸው ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ በ “እንቁ” መጽሔት አሣታሚ አለማየሁ ህትመትና ማስታወቂያ ኃላ/የተ/የግ ማህበርና ባለቤቱ አለማየሁ ማህተመ ወርቅ ገብረአጋይስት ላይ በመጋቢት 2006 ዓ.ም እና በሚያዚያ 2006 ዓ.ም ታትመው በወጡ ሁለት መጽሔቶች ላይ የሃሰት ወሬዎችን አትሞ በማውጣት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
በመጋቢት ወር በወጣው ዕትም፤ “በሐረር ከተማ ከአንድ መቶ በላይ ሱቆች ወደሙ፤ የክልሉ መንግስት ሆን ብሎ ነው ያቃጠለው (ነዋሪዎች)” በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፍ “የክልሉ መንግስት ሆነ ብሎ ያደረገው ነው” በሚል ህዝቡ በክልሉ መንግስት ላይ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲኖረው የሚያደርግ የሃሰት ወሬ በማቅረብ እንዲሁም በሚያዚያ ወር ዓ.ም ለህትመት በበቃው መጽሔት፤ “የሠራዊቱ አልጋዎች” በሚል ርዕስ የመከላከያ ሠራዊቱ ለህገ መንግስቱና ለኢትዮጵያ ህዝብ የቆመ እንዳልሆነ በማስመሰል፣ ህዝቡ ሠራዊቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረው የሚያደርግ ሃሰተኛ ወሬ በማሠራጨት ህዝብን በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸው ታውቋል፡፡
ዘወትር አርብና ማክሰኞ ታትሞ ይወጣ በነበረው “አፍሮ ታይምስ” ጋዜጣ አሣታሚ ግዛውና ቶማስ ኢንተርቴይመንት የፕሬስ ስራዎች ኃላ/የተ/የግ ማህበርና ባለቤቱ ቶማስ አያሌው ተካልኝ ላይ የቀረበው ክስ ደግሞ ሚያዚያ 21 እና 22 ቀን 2006 ዓ.ም በወጡት ዕትሞች ላይ “ልዩ ኃይሎችና መከላከያ ሰራዊት ተፋጠዋል” በሚል ርዕስ ስር ባስነበበው ጽሑፍ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በህዝቡ ዘንድ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርግ ሃሰተኛ ወሬዎችን በመንዛትና ህዝብን በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸው ተመልክቷል፡፡
ምንጭ አዲስ አድማስ ጋዜጣ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar