onsdag 30. juli 2014

በጋምቤላ በመዥንገርና በደገኞች መካከል ግጭት ተፈጠረ

-17 ሰዎች መገደላቸው የተሰማ ቢሆንም መንግሥት ሕይወት አልጠፋም አለ
በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መዥንገር ዞን የሪ በተሰኘ ቦታ ላይ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በተከሰተ ግጭት 17 ሰዎች መገደላቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡
284903EE-7935-4928-8B1C-D65A9A50A515_mw1024_s_nመንግሥት ግን በግጭቱ ጥቂት ሰዎች ቢፈናቀሉም የአንድም ሰው ሕይወት እንዳልጠፋ ገልጿል፡፡
የዓይን እማኞች ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ የዞኑ ቀደምት ነዋሪዎች የሆኑት የመዥንገር ብሔር አባላት በአካባቢው ሠፍረው የሚገኙትን በአብዛኛው የአማራና የትግራይ ተወላጆች የሆኑትንና ‹‹ደገኛ›› ወይም ‹‹ሐበሻ›› በመባል የሚታወቁትን ነዋሪዎች ‹‹ከአካባቢው ይውጡልን›› በማለት ቅሬታ ማቅረባቸው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተለመደ ሆኗል፡፡
የሪ በተሰኘው ቦታ ላይ በቡና ልማት ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ የነበሩት ደገኞች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ግን ለየት ያለና የፖለቲካ ድጋፍ ያለው እንደሚመስል ምንጮች አመልክተዋል፡፡
ነባር ነዋሪዎች መሣሪያ ታጥቀው እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፣ ግጭቱ የተከሰተው ነባር ነዋሪዎች በገዛ ፈቃዳቸው መሬታቸው ላይ ደገኞቹ ቡና እንዲያለሙ ሰጥተው፣ ቡናው ሙሉ በሙሉ ከለማ በኋላ ደገኞቹ ያለ ምንም ዓይነት ካሳ እንዲለቁ በመጠየቃቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የቡና መሬቱን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባልሆኑ ሰዎች ላይ በተወሰደው ዕርምጃ 17 ሰዎች መሞታቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ አስከሬኖቹን በወቅቱ ለማንሳት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ በክልሉም ሆነ በፌዴራል መንግሥቱ በኩል ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ የማደባበስ ነገር እንደሚስተዋል የጠቆሙት ምንጮች፣ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ጊዜያዊ መፍትሔ ብቻ በመስጠት ሳይገታ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በጥልቀት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ሪፖርተር የጋምቤላ ክልል ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ጥረት ያደረገ ሲሆን፣ ግጭቱ ስለመከሰቱ ባይክዱም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አበበ ወርቁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በነባር ነዋሪዎችና በደገኞቹ መካከል የተፈጠረው ግጭት ከባድ የሚባል አይደለም፡፡
ግጭቱ ጥቂት ደገኞችን ማፈናቀሉን የጠቆሙት አቶ አበበ፣ የፌዴራል መንግሥት በቦታው በመገኘት ግጭቱን በቁጥጥር ሥር ካዋለው በኋላ የተፈናቀሉትም ቢሆኑ ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ መደረጉን አመልክተዋል፡፡ ሪፖርተር 17 ሰዎች ስለመሞታቸው ጥቆማ እንደደረሰው የተገለጸላቸው አቶ አበበ፣ መረጃው ከእውነት የራቀ እንደሆነና የአንድም ሰው ሕይወት እንዳልጠፋ አስተባብለዋል፡፡
ግጭቱ እንዲፈጠር ያደረጉት የራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ያላቸው የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደሆኑ መታወቁን ያመለከቱት አቶ አበበ፣ የአካባቢው አመራር ተገምግሞ እጃቸው እንዳለበት በተረጋገጠ አባላት ላይ ዕርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል፡፡
በነባር ነዋሪዎችና በደገኞች መካከል ለሦስት ቀናት ውይይት ከተደረገ በኋላ የጋራ መግባባት መፈጠሩን የጠቆሙት አቶ አበበ፣ አሁን በአካባቢው ሰላም ሙሉ በሙሉ መስፈኑንና ነዋሪዎችም ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለሳቸውን አመልክተዋል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar