አንድነት ፓርቲ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት በ48 ሰዓታት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር መቆየታቸው ሕገወጥ ነው ሲል ላቀረበው ክስ በአራዳ የሚገኘው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ ፍርድ ቤት ስለመቅረባቸው ማስረጃ ማቅረቡን በመግለጽ ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ብይን ሰጠ፡፡
የተያዙበት መንገድ ሕገወጥ ነው ለሚለው ቅሬታ በመደበኛው ክርክር ሊካተት እንደሚገባም ፍርድ ቤቱ በይኗል፡፡
የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ 2ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ይህን ብይን ቢሰጥም፣ የአንድነት ፓርቲ ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ ክርክሩ የፍትሐ ብሔር እንደመሆኑ መጠን ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበው መከራከር ሲኖርባቸው፣ ፖሊስ ብቻውን ቀርቦ ማስረዳቱ አግባብነት እንደሌለው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ጠበቃው በተጨማሪም የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የአቶ ሀብተሙ አያሌው ቤተሰቦች የተጠርጣሪው የፌስቡክ አካውንት ከታሰሩም በኋላ ጥቅም ላይ እየዋለ (active) መሆኑን እንደገለጹለቸው የጠቆሙ ሲሆን፣ በቁጥጥር ሥር ያዋለው የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነትና የፌዴራል ፖሊስ ጥምር የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የይለፍ ቃል ስለመውሰዱ ወይም አለመውሰዱ ግን አለመታወቁን አስረድተዋል፡፡
አንድነት ፓርቲ ከአቶ ሀብታሙ አያሌው በተጨማሪ የፓርቲው የምክር ቤት አባል አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የዓረና ለትግራይ ሉዓላዊነት ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ የሺዋስ አሰፋ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውና በ48 ሰዓታት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው ሕገወጥ ነው ሲል ሐምሌ 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ያቀረበው ክስ ላይ፣ ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. መልስ የሰጠው ግብረ ኃይሉ ፍርድ ቤት ማቅረቡን በመግለጽ መከራከሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱም ለሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ለብይን ሲቀጥር ግብረ ኃይሉ ፍርድ ቤት ስለማቅረቡ ማስረጃ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ በእሱ ላይ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ የፍርድ ቤቱ ብይን የግብረ ኃይሉ ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ማቅረቡንና የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ እንደተሰጠው በጽሑፍ ያቀረበው ማስረጃ አሳማኝ ሆኖ እንዳገኘው የሚገልጽ ነው፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar