–ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ተጠቁሟል
የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ 50,000 ብር ጉቦ ጠይቀው 10,000 ብር ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡
እንደ ኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ምክትል ዋና ቃዲው፣ በሥራ ኃላፊነታቸውና ግዴታቸው ማድረግ የሚገባቸውን አላደረጉም፡፡ በመሆኑም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት አስበው የግል ተበዳይ ናቸው የተባሉት ወ/ሮ ሮዛ መሐመድ ጁሃር፣ የጋብቻ ሰነዳቸው የሸሪዓ ስለመሆኑ ተመስክሮ እንዲሰጣቸው ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ማመልከታቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ማስረጃውን ሊሰጣቸው ባለመቻሉ ግለሰቧ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ማቅረባቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡ ምክትል ዋና ቃዲው ጉዳዩን ለመጨረስ 50,000 ብር ጠይቀው፣ ከግለሰቧ ጋር ከተስማሙ በኋላ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከምሽቱ 11፡00 ሰዓት፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15 ልዩ ቦታው አስኮ ነዳጅ ማደያ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ፣ ከግለሰቧ 10,000 ብር ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ክሱ በዝርዝር ያስረዳል፡፡
ተጠርጣሪው ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የዋስትና መብታቸው ታልፎ፣ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩና ሐምሌ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
በክሱ ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ሕግ ቁጥር 408(2) ከሰባት እስከ 15 ዓመታት በእስራት ሊያስቀጣ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar