ከዕለት ወደ ዕለት ችግሩ እየተባባሰ የቀጠለው የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭት አገልግሎት የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ተጠቃሚዎች እየተናገሩ ነው፡፡
ከኃይል ማመንጫው በቀጥታ አገልግሎትቱን በማግኘት እየሠሩ ከሚገኙት ጥቂት ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች በስተቀር፣ ሁሉም በሚባል ሁኔታ በቀን ከሁለት እስከ አምስት ጊዜያት ኤሌክትሪክ ኃይል የማይቋረጥበት መለስተኛ፣ አነስተኛና ጥቃቅን ድርጅቶች እንደሌሉ ሁሉም በተመሳሳይ ቋንቋ ‹‹የኤሌክትሪክ ኃይል የለም›› በማለት እየተናገሩ ነው፡፡
ከአሥር ወራት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የተቋረጠባቸው ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኙት አነስተኛ ከተሞች ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚል ለሁለት ከተከፈለው ፒያሳ ደጐል አደባባይ ከሚገኘው የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት አካባቢ ጀምሮ፣ በመላው አዲስ አበባ እስከ አንድ ወር ድረስ የኃይል መቋረጥ የሚገጥማቸው ነዋሪዎች ወዴት ሄደው አቤት እንደሚሉ ግራ መጋባታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በአነስተኛ ኢንዱስትሪ ሥራ ላይ የተሰማራው የንግዱ ማኅበረሰብ ለሚሰጠው አገልግሎት፣ ደንበኞቹን በአግባቡ ቀጥሮ የሚሠራውን ሥራ በጊዜና ባለበት ሰዓት ለማስረከብ ፈተና እንደሆነበት ለመግለጽ ‹‹መብራት ካልተቋረጠብኝ በዚህ ቀን አደርሳለሁ፡፡ ለማንኛውም እዚህ ድረስ ለፍተው እንዳይመለሱ ስልክ ደውለው ይጠይቁኝ፤›› በማለት የእሱ ጥፋት እንዳልሆነ እንዲገነዘቡት የሚማፀንበት ጊዜ ላይ እንዳለ ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ ለሁለት ተከፍሎ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ዘርፍ በዋናነት የተረከበው የህንዱ ኩባንያ፣ ኢትዮጵያውያን በምክትል ሥራ አስፈጻሚነት መሾሙንና ቀደም ብሎ የነበረውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በአዲስ የመተካት ሥራ እየሠራ መሆኑ በመግለጹ፣ የተሻለ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገው እንደነበር የሚናገሩት ሁሉም ተጠቃሚዎች፣ ‹‹ትሻልን ፈትቼ ትብስን አገባሁ›› እንዲሉ አገልግሎቱ እንኳን ሊሻሻል ባለበት መቀጠል አለመቻሉ እንዳሳዘናቸው እየተናገሩ ነው፡፡
ሌላ መሄጃ ስለሌላቸው ፒያሳ በሚገኘው የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቢሮ ሲመላለሱ አንዴ ካሳንቺስ፣ ሌላ ጊዜ መካኒሳ፣ አራት ኪሎ፣ ቄራና ኮተቤ ሄደው እንዲያመለክቱ በተላላኪ ወይም በማይመለከተው ሠራተኛ እንደሚነገራቸው የሚገልጹት የመሥሪያ ቤቱ ደንበኞች፣ የሌሊቱን ጨለማና ምግብ ማብሰሉን በሻማ፣ በላምባና በእንጨት ለመጠቀም የተገደዱ ቢሆንም፣ ሥራዎችን ከኤሌክትሪክ ኃይል ውጪ መሥራት ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ኪሳራ እየተጋለጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ለሁሉም የመንግሥት አካላት አስቸኳይ ደብዳቤ በመላክ ችግራቸውን ለማሳወቅ ቢሞክሩም፣ በተለይ ላለፉት አምስትና ስድስት ወራት ምንም ምላሽ እንዳላገኙ የሚናገሩት የድርጅቱ ደንበኞች፣ አሁን አሁን እንኳን በደብዳቤ በአካል ተገኝተው ባመለከቱበት መሥሪያ ቤት አግባብ ያለው ምላሽ ስላልተሰጣቸው ተስፋ መቁረጣቸውን አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ሁሉንም ዜጐች የማስተዳደር፣ መብታቸውን ማክበርና የሚፈልጉትን የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት ገልጸው፣ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራው ከአቅሙ በላይ ሆኖበት ከሆነ መንግሥት ጠይቆ አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርግለት እንደሚገባ የሚናገሩት ደንበኞቹ፣ ኢትዮጵያውያኑ ‹‹የበለጠ ዕውቀት እያለን እንዴት በውጭ ዜጐች እንታዘዛለን?›› ማለታቸው እንዳሰጋቸው አንዳንዶቹን ሲያነጋግሯቸው ‹‹ገብታችሁ አነጋግሩት›› የሚል ምላሽ እንደሚሰጧቸውና ይኼ ችግር የኃይል እጥረት ሳይሆን ቀናነት ማጣትና የማኩረፍ ሁኔታ ሳይሆን እንደማይቀር ደንበኞቹ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ችግር በአንድ ቦታ ብቻ ራሱን ችሎት የቆመ አለመሆኑን የሚጠቁሙት ደንበኞች፣ ኃይል በተቋረጠ ቁጥር የውኃና የስልክ አገልግሎትም እንደሚቋረጥ አስረድተዋል፡፡ ችግሩ መልከ ብዙ በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞች የሚያነሱትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በሚመለከት የሚመለከተው ኃላፊ ምላሽ እንዲሰጥ ሪፖርተር ሰኔ 27 ቀን 2006 ዓ.ም. በደብዳቤ ማብራሪያ ጠይቆ ‹‹በአካል ተገኝታችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ›› የሚል ምላሽ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ኃላፊዎቹ በአካል ለመነጋገር ፈቃደኛ በመሆናቸው ምክንያት የሪፖርተር ዘጋቢዎች ፒያሳ ደጐል አደባባይ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ቪ.ኬ ካሬ ቢሮ ሲገኙ፣ ደብዳቤው ለሥርጭት ዋና ኦፕሬሽን ኃላፊ ስለተመራ ሄደው እንዲጠይቁ ተነገራቸው፡፡ የሥርጭት ዋና ኦፕሬሽን ኃላፊ ሚስተር ዲፓክ ማቱርና ደግሞ ለሥርጭት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቢትወደድ ገብረአሊፍ መመራቱን በመናገራቸው፣ እሳቸውን ለማግኘት በተደጋጋሚ በቢሮአቸው በመገኘት ማብራሪያ ለማግኘት ቢሞከርም ‹‹የሉም፣ አሁን ወጡና ስብሰባ ላይ ናቸው፤›› በሚሉ ምክንያቶች የድርጅቱን አስተያየት ማካተት አልቻለም፡፡
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar