torsdag 20. juni 2013

የአባይ ጉዳይ የዛፍ ላይ እንቅልፍ የሆነባት ግብጽ እና ለስልጣን ጸብ ጫሪው ህውሃት!

nile dam
የአባይ ጉዳይ ለግብጽ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው። ዛፍ ላይ ሆነህ እንቅልፍ ይወስድሃል? ሸለብ እንኳን ያደርግሻል ዛፍ ላይ ሆነሽ? እነደዚያ ነው የአባይ ጉዳይ ለግብጽ። ይኽ እንቅልፍ ማጣት እና ስጋት ዛሬ የጀመረ አይደለም። ባጭሩ ልተርክ። ሪቻርድ ፓንክረስት በግብጽ የተገኙ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ ክርስቶስ ከመወለዱ ከ3 ሺ አመቶች በፊት ጀመሮ የግብጽ ነጋዴዎች በእግራቸው የአባይን ወንዝ ዳርቻ ተከትለው እንዲሁም በቀይ ባህር በነፋስ በሚገፉ ጀልባዎች ዛሬ ኢትዮጵያ (ያኔ የፐንት ግዛት) በሚባለው ግዛት ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ ጋር የንግድ ልውውጥ ማድረጋቸውን እና ግዛቱን ምድረ ታ-ኔትጄሩ (Land Ta-Netjeru) ማለትም “ምድረ አማልዕክት” እንደሚሉት እና “የመጀመሪያ አገራችን ነው” ይሉም እንደነበር የኢትዮጵያውያን ድንበር-መሬቶች (The Ethiopian Borderlands) በሚለው መጽሐፉ ዘርዘር አድርጎ ጽፏል። የቅርቡን ብንመለከት ደግሞ በተለይ ከ1813 ዓ. ም. ጀመሮ ግብጽ የኢትዮጵያ ባለቤትነቷን በጦርነት ለማረጋገጥ የዮሐንስን ኢትዮጵያ ከሱዳን ቀላቅላ ለመግዛት በአራት አቅጣጫዎች ወረራዎች ከፍታ ሳይሳካለት ወደ መጣችበት መመለሷን ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ “ዐፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፉ በሰፊው ተርኳል። በኃይለስላሴ እና በደርግ ዘመንም ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የጦር መሳሪያ እና ስልጠና በማቀነባበር፣ ገንዘብ በመለገስ፣ በመካከለኛው ምስራቅ አረብ አገሮችን በማስተባበር፣ የአማርኛ ስርጭት ሬዲዮ በመክፈት ድጋፍ ማድረጓን እናውቃለን። ህውሃት ከተጠቃሚዎቹ ተቃዋሚዎች ውስጥ አንዱ ነው። በአባይ ጉዳይ ከጥንት ጀምሮ ግብጽ ከስጋት ነፃ የሆነ እንቅልፍ የለታም። ዛሬም ሆነ ወደፊት ግብጽ የሰላሙን መንገድ ትታ የጸበኛነቱን መንገድ ከመረጠች እንቅልፍ አይኖራትም። ይኽን የግብጽ ጭነቀት እና ስጋት ህውሃት ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህ ግንቦት 20 ቀን ጸብ ጫረ። ላብራራ።
የጥናቱን ውጤት ተቀበለችውም አልተቀበለችው ስለ አባይ ጉዳይ በጥናት ላይ የተሰማራው ኤክስፐርቶች ቡድን ሪፖርት እየጠበቀች ሳለች ድንገት ግንቦት 20 ቀን 2005 ዓ. ም. ህውሃት የአባይ ወንዝ የፍሰት አቅጣጫ መቀየሩን ሰበር ዜና ተሰራጨ። የኢትዮጵያ ሽብርተኛው ኢ.ት.ቭ. አስተጋባ። ዜናው ግብጽ ደረሰ። ከጥንት ጀምሮ የአባይ ጉዳይ የዛፍ ላይ እንቅልፍ የሆነባት ግብጽ ተደናገጠች። አምባገነኑ ሞርሲ ከገበባት የውስጥ ችግር ለማምለጥ የህውሃትን ቁስቆሳ ተጠቀመ። አካራሪ የግብጽ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ጋበዞ ‘እኔ ሳልሞት ግብጽ አትጠማም’ አለ። ያጀቡት አክራሪዎችም ‘ግፋ’፣ ‘በርታ’፣ ‘አይዞህ ከጎንህ ነን’ አሉት። ይኽ  ምክክራቸው ዜና ሆኖ አደባባይ ወጣ። ህውሃት ሁካታውን ያልጫረ መስሎ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግብጽ ልትወጋህ ነው የሚል ፕሮፖጋንዳ ጀመረ። የቀድሞ አባቶቻችን ድሎች ሳይቀሩ እየተጠቀሱ የቀረርቶ ድምጽ በአዲስ አበባ እየጎላ መጣ። አልባራዳይን የመሰሉት የግብጽ ዴሞክራሲ ኃይሎች የግብጽን መንግስት ወቀሱ። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎችም ቀረርቶው ገደብ ይበጅለት አሉ። የኢትዮ-ግብጽ የጦርነት ሁካታ አነሳሱ ይኽን ይመስል ነበር። ህውሃት የማያስፈልግ ጸብ ጭሯል።
ለመሆኑ ለምን የአባይ ወንዝ አቅጣጫ ግንቦት 20 ቀን ተቀየረ? ዜናውስ ለምን ግንቦት 20 ቀን አደባባይ ወጣ? ለዚኽ ጥያቄ አቶ በረከት ስሞዖን ሰኔ 7 ቀን ግድም 2005 የሰጠውን መግለጫ እንመልከት፥ የአባይ ወንዝ አቅጣጫ ግንቦት 20 ቀን የተቀየረው በአጋጣሚ እንጂ ህውሃት ሰልጣን ከጨበጠበት ቀን ጋር እንዲገጣጠም ሆን ተብሎ የተደረገ እንዳልሆነ ሊያስተባብል ሞክሯል። ይኽ የበረከት ስሞዖን ማስተባበያ በሽብርተኛው ኢ.ቲ.ቭ. እና በኢሳት ተዘግቧል። የአቶ በረከትን መቀላመድ ወደ ጎን አድርገን እውነቱን ሃቁን እንመልከት። የአባይ ወንዝ ፍሳሽ አቅጣጫ ግንቦት 20 ቀን እንዲቀየር ያስደረገው ህውሃት ነው። ዜናው ግብጽ እንዲደርስ ያደረገውም ህውሃት ነው። ግቡም ስልጣን ነው። ላብራራ!
1ኛ) የተለየ አሳቢ እና ከድኽነት ነፃ አውጪህ እኔ ህውሃት ነኝ የሚል መልዕክት ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማስተላለፍ እንዲችል ሆን ብሎ የአባይ ፍሳሽ የተቀየረበትን ቀን ስልጣን ከጨበጠበት ግንቦት 20 ቀን ጋር አገጣጠመው። የዚኽ እርምጃ ፖለቲካዊ ግብ ህዝቡ እንዲያመልክበት እና ስልጣኑ እንዲጠናከር ነው። ግድብ መገንባት አይደለም ግቡ።
2ኛ) የአባይ ጉዳይ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ለሆነባት ግብጽ የአባይ ፍሳሽ አቅጣጫ መቀየር ዜና የጦርነት ፖለቲካ ውስጥ እንደሚያስገባት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በምላሹ የኢትዮጵያን ህዝብ በአገር ወዳድነት ስሜት አሳውሮ በሚፈልገው የፖለቲካ አቅጣጫ ለማስጓዝ አስልቶ ነበር። የዚኽም ፖለቲካ ስሌት ግቡ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ኃይሎች ለመምታት እና ስልጣኑን ለማጠናከር ነበር። በአገር ከሃዲነት እና በሽብርተኛነት ሽፋን። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች ፈጥነው ስላጋለጡት የኢትዮጵያን ህዝብ በአባይ ስሜት አሳውሮ የዴሞክራሲ ኃይሉን ለመምታት የሚያስችለው ጊዜ ሳያገኝ ቀረ። ከሸፈበት።
ግርማ ሞገስ
ግርማ ሞገስ
ህውሃት ከግድቡ ይልቅ ስልጣኑ እንደሚበልጥበት ለአንዲት ደቂቃ እንኳን መዘንጋት አያስፈልግም። ወደፊትም ሌሎች ጸቦች ሊጭር እና ከዚያ ግብጽ ልትወጋን ነው ይልሃል። የዴሞክራሲ ኃይሎች የነፃነት ሰላማዊ ትግላቸውን አጠናክረው በመቀጠል እራሳቸውን ከህውሃት ማጭበርበር እና ጥቃት መጠበቅ አለባቸው።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar