mandag 24. juni 2013

አቶ ገብረመድህን አርአያ የዘማናችን አሉላ አባ ነጋ ተብለው በከፍተኛ ክብር ተሰየሙ

June 24, 2013


በምእራብ አውስትራሊያ በፐርዝ ከተማና አካባቢዋ ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጁን 23 ቀን 2013 ባደረጉት ልዩ ዝግጅት ታዋቂውን የነፃነት ተፋላሚና የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጅ አቶ ገብረመድህን አርአያን የዘመናችን አሉላ አባ ነጋ በማለት በክብር ሰይመዋቸዋል። በዚህ ለእርሳቸው ታስቦ በተደረገው ልዩ የእራት ግብዣ ስነ ስርዓት ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን የተገኙ ሲሆን፣ እንግዶቹ ለአቶ ገብረመድህን አርአያ ያላቸውን ልዩ ክብርና አድናቆት በየተራ እየተነሱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። በዚሁ መሰረትም አቶ ገብረመድህን ህወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ይዞ የተነሳውን እኩይ አላማና ተግባር በማጋለጥ ያደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ፣ በተለያዩ የሚዲያ ዘርፎች በመረጃ የተደገፉ መግለጫዎችን እና ትምህርቶችን በመስጠት የከወኗቸው ሥራዎች፤ እንዲሁም ለእሩብ ምእተዓመታት ያህል በጽኑነት፤ በቆራጥነትና በሕዝብ ወገናዊነት መቆማቸው በምሳሌነት በጉልህ ተጠቅሰዋል።Gebremedhin Araya, awarded in Australia
ለአቶ ገብረመድህን ማህበረሰቡ በጋራ ባዘጋጀው በዚሁ ስነስርዓት ላይ በአረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ቀለማት በደመቀ የኢትዮጵያ ሙሉ ካርታ ላይ የጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ ምስል የተቀመጠበት የታሪክ ማስታወሻ ከታላቅ አክብሮት ጋር ተበርክቶላቸዋል። እንዲሁም ግለሰቦች በራሳቸው አነሳሽነት ያዘጋጁላቸው የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል።
በዚሁ ደማቅ ስነስርዓት ላይ አቶ ገብረመድህን ባደረጉት ንግግር ለሳቸው ተብሎ የተደረገውን ይህን ታላቅ ዝግጅት ያልጠበቁት እንደነበር ገልጸው ለዚህ ክብር ያበቃቸውን ወገናቸውን እጅግ አድርገው እንደሚወዱ፣ እንባ እየተናነቃቸው የታዳሚውን ስሜት በጥልቅ በሚነካ አኳኋን ገልጸዋል። ይህ ለርሳቸው የተደረገው የክብር ዝግጅት የበለጠ ለወገናቸውና ለሃገራቸው ሌት ተቀን ተግተው እስከመጨረሻው ለመታገል ብርታት እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በርትቶ በመታገል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ በአጽንኦት አሳስበዋል። “አገራችን የጋራ ናት፣ በመሆኑም ችግሩ የጋራችን ነው፣ እንዲያ በመሆኑም የጋራ መፍትሄ ያስፈልገዋል” በማለት ወያኔን ከስሩ ነቅለን እስካልጣልነው ድረስ በጥገናዊ እርምጃ መፍትሄ የማይገኝ መሆኑን አቶ ገብረመድህን አስገንዝበዋል። ለዚህም ሴት፣ ወንድ፣ ሽማግሌ፣ ህፃን ሳይል ሁላችንም ተዋናይ በመሆን ቆርጠን መነሳት አለብን ብለዋል።
አቶ ገብረመድህን በተለይ አማራ በተባለው ነገድ ላይ በህወሓት እየተደረገ ያለው የዘር ማጥራት ድርጊት በዚሁ ከቀጠለና በአስቸኳይ እንዲቆም ካልተደረገ ይህ ሕዝብ የሚደርስበት ጉዳት መመለሻ የሌለው ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። ለዚህ ማስረጃም በዋናነት ሟቹ የህወሓት መሪ መለስ ዜናዊ ለይስሙላ ባዋቀረው ፓርላማ ላይ እንዳመነው ከ2.5 ሚሊዮን በላይ አማራ መጥፋቱን እንደገለጸ አውስተው፣ እሳቻው ባላቸው መረጃ መሰረት ግን በህወሓት ምክንያት የጠፋው አማራ ከ5 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን አመልክተዋል። ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቀላሉ ዘዴ አማራውን ማጥፋት ነው በሚለው እስትታተጂው ገፍቶ እንደቀጠለበት በገሃድ እየታየ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡም አስገንዝበዋል። በአማራው ላይ የሚደረገው የከፋ ጭፍጨፋ ሌላውን ወንጀል አደበዘዘው እንጂ ብዙ ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን እንዳለቁና እንደተሳደዱም አቶ ገብረመድህን መስክረዋል። በአፋር፣ በሲዳማ፣ በሱማሌ፣ በጉራጌ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚካሄደው ጭፍጨፋ የከፋ መሆኑንም ገልጸዋል። ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን ጎሰኛና ጨፍጫፊ ስርዓት በአንድነት ተነስተው ታግለው በመጣል የሁሉም መብት የሚከበርበት የራሳቸው የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማምጣት እንደሚገባቸው በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
ታዳሚው በበኩሉ ለአቶ ገብረመድህን ያለውን አድናቆት ከምግለጹም በተጨማሪ፣ የሳቸውን ጥሪ እንደተቀበለው ኢትዮጵያዊ ወኔ በተሞላበት ስሜት አረጋግጧል። እኚህን የኢትዮጵያዊ አርበኝነት ምሳሌ የሆኑትን ጀግና አቅፎና ደግፎ እስከመጨረሻው እንደሚንከባከባቸውም ታዳሚው ገልጿል። ምክራቸውን እና ምሳሌነታቸውን በመቀበልም ተግቶ እንደሚንቀሳቀስም አረጋግጦላቸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ወያኔና የወያኔ ጥቅም አስከባሪዎች በአቶ ገብረመድህን አርአያ ላይ የሚሰነዝሩትን ማንኛውንም ትንኮሳ አምርሮ እንደሚዋጋ ታዳሚው በአንድ ድምጽ ገልጿል። ለምሳሌም በቅርቡ በአቶ አብርሃም ያየህ በአውራ አምባ ድረገጽ ላይ የተሰነዘረባችውን የሃሰት ዘመቻ በመጥቀስ ይህን አይነት ተግባር የሚፈጽሙ ወገኖች ከዚህ አይነቱ አጸያፊ ተግብራቸው ተቆጥበው ለወግን እና ለሃገር በሚበጅ ተግባር ላይ ቢሰማሩ የተሻለ እንደሚሆን ታዳሚው አሳስቧል።
በመጨረሻም ታዳሚው ለአቶ ገብረመድህን አርአያ የሚመኝላቸው ብዙ መስዋእትነት የከፈሉላትን እና የሚወዷትን የእናት ሃገራቸውን የኢትዮጵያን ትንሳኤ ከሕዝቡ ጋር በጋራ ድል ለማየት የሚያበቃ ረጅም እድሜና ጤንነት ፈጣሪ እንዲያድላቸው መሆኑን በከፍተኛ ስሜት ገልጿል።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር
የፕርዝና አካባቢዋ ኗሪ ኢትዮጵያውያን

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar