"አሸባሪነትን መዋጋት የግፍ ማከናወኛ ሽፋን አይሆንም"
ኢህአዴግ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም ከአሜሪካ ጋር የመሰረተውን ግንኙነት አስታክኮ የሚፈጽመው ኢሰብዓዊ ድርጊት ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ተገለጸ። አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ የምትመረምርበት ወቅት ላይ ትገኛለች ተባለ። ኢህአዴግ ጸረሽብርተኝነትን ለአፈናና ለበጀት ማሟያ እየተጠቀመበት እንደማይቀጥል ተመለከተ።
አሜሪካና ሌሎች ለሰብአዊ መብት መከበር ዋጋ የሚሰጡ አገሮች በሙሉ በ”አዲስ አበባው” አገዛዝ ላይ ጠንካራ አቋም መያዛቸውን ያለ አንዳች ማወላወል ማሳየት እንደሚገባቸው እንደራሴ (ኮንግረስማን) ክሪስ ስሚዝ ያስታወቁት ሽብርተኛነትን አስመልክቶ ጠንካራ ማሳሰቢያ በማስቀመጥ ነው።
እንደራሴ ስሚዝ የኢትዮጵያ ጉዳይ የተደመጠበትን የምክክር ሸንጎ ከዘጉ በኋላ በተለይ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት “አሜሪካ በኢህአዴግ ላይ ያላትን አቋም የምትመረምርበት ወቅት ላይ ትገኛለች” ብለዋል።
አሜሪካ ከሰብአዊ ርዳታ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግና በተለይም ኢትዮጵያና አሜሪካ አሸባሪነትን በመዋጋት በኩል አብረው እንደሚሰሩ ያመለከቱት እንደራሴው፣ “ሽብርንና ሽብርተኛነትን የመታገል ትብብር ግን የዜጎችን ሰብአዊ መብት ለመርገጥ ፍቃድ ማግኛ አይደለም። የመብት ረገጣ ሽፋን ሊሆን አይገባም” በማለት የኢህአዴግና የመሪዎቹን ተግባር ኮንነዋል።
“አንድ አገር ገና ለገና ሽብርተኛነትን ለመዋጋት ከአሜሪካ ጎን ስለቆመ ብቻ የህዝብ ሰብአዊ መብቶችና የዴሞክራሲ አተገባበር ላይ ዝም ሊባል አይገባም” በማለት አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ስሚዝ፣ ሽብርን መዋጋት የኢትዮጵያ የራስዋም ፍላጎት አንደሆነ አመልክተዋል።
“ስለዚህ” አሉ ክሪስ ስሚዝ፣ “ስለዚህ የአሜሪካ መንግስትም ሆነ ሌሎች የምራብ አገራት፣ ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊያን ላይ እየፈጸመ ያለውን ተግባር በመረዳት አቋማቸውን በግልጽ ማስቀመጥ ይገባቸዋል”
“ለሰብአዊ መብት መከበር ዋጋ የሚሰጡ አገሮች በአዲስ አበባው መንግስት ላይ የማያወላውል ጠንካራ አቋም መያዛቸውን ማሳየት አለባቸው” ሲሉ የተደመጡት ክሪስ ስሚዝ “ከዚህ ቀደም አርቅቄ፣ አስተዋውቄ፣ ለውይይት አቅርቤው የነበረውን ኤች አር 2003 ህግ እንደገና በማሻሻል ለድምጽ አቀርበዋለሁ” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ህገደንብ” የሚል ስያሜ ያለው ህግ፣ ኢትዮጵያን የሚመራው ኢህአዴግ ከአሜሪካ መንግስት ለሚፈልገው ማናቸውም ድጋፍ መሟላት የሚገባቸውን የሰብአዊና የዴሞክራሲ መብት ግብአቶችን በቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጥ ነው። እንደራሴ ክሪስ እንደገና ለድምጽ እንደሚያቀርቡት ደጋግመው የገለጹት ይህ ህግ ኢህአዴግ በከፍተኛ ደረጃ ገንዘብ አፍስሶ በአሜሪካን ጎትጓቾች (ሎቢዪስቶች) ዘመቻ ያካሄደበት ነው።
መለስን ”አሮጋንት/ዕብሪተኛ/“ በመለት የገለጹት ክሪስ ስሚዝ “ከመለስ ሞት በኋላ ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ታመራለች” የሚል እምነት እንደነበራቸው በመናገር “የሰማሁት ምስክርነት ከዚህ የተለየ፣ ተስፋ ከተደረገው ተቃራኒ ነው” ብለዋል። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ “ብዙዎች” ሲሉ በጥንቃቄ የገለጹዋቸው አካላት ከመለስ ሞት በኋላ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ መንግድ ታመራለች የሚል እምነት እንደነበራቸው ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። በውል የተየው ነገር ኢትዮጵያዊያን ወደ ባሰበት ችግርና የመብት ረገጣ የመዘዋወራቸው ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል። ይህም አሳሳቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በማብቂያቸውም “አሁን ፖሊሲያችንን ዳግም የመፈተሽያ ጊዜ ላይ ነን። ቁም ነገሩ ከተጨቆኑት ወገኖች ጋር መቆሙ ላይ ነው። ከተጨቆኑት ወገኖች ጋር እንቆማለን” የሚል ከተለመደው የአሜሪካ አቋም የተለየ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ኦባንግ ሜቶና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የተገኙበትን የምክክር ሸንጎ ተከትሎ እስካሁን ድረስ የኢህአዴግ አቋምና ምላሽ አልታወቀም። ይሁን እንጂ ቀደምሲል ኤች አር 2003 ህግ ሆኖ እንዳይጸድቅ ኢህአዴግና ወዳጅ ባለሃብቶች ተመሳሳይ ተግባር ለማከናወን ሩጫ መጀመራቸው ተሰምቷል። በተጨማሪም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዲፕሎማሲ ጅምናስቲክ መጀመሩ ታውቋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በተለያየ ወቅት መለስ በሽብርተኛ ትግል ሰበብ አሜሪካንንና የምዕራቡን ዓለም እያምታቱ እንደሆነ በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል። ሆን ተብሎ በተሽከርካሪዎች ላይ የተቀነባበረ የፈንጂ ማፈንዳት፣ ህዝብን የማሸበር ተግባር እንደሚፈጸም በማመልከት ተቃዋሚዎች ሲጮሁ ሰሚ አልነበራቸውም። የሹልክዓምድ (ዊኪሊክስ) መረጃ ይህንኑ ይፋ ማድረጉና ኢህአዴግ ራሱ ፈንጂ አፈንድቶ “አሸባሪዎች ፈንጂ አፈነዱ” በሚል እንደሚያምታታ ማጋለጡ ይታወሳል።
አቶ መለስ አሜሪካና ምዕራባዊያን ሰብአዊ መብትን፣ ምርጫንና የዲሞክራሲ መብቶችን አስመልክቶ ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው “ጦራችንን ከሶማሊያ እናስወጣለን፣ ቀጠናው ቢተራመስ ተጠያቂ አይደለንም” የሚል ምላሽ እየሰጡ ያስፈራሩ እንደነበር የሚጠቁሙ የጎልጉል ምንጮች “ኢህአዴግ ብር ሲፈልግና ካዝናው ሲጎድል ዘወትር የሚያነሳው የሽብርና አሸባሪዎችን የመታገል ውለታ ድርጎ ነው” ብለዋል። በ1997 ምርጫ ወቅት የተሸነፈው ኢህአዴግ በወቅቱ አሜሪካን ጫና ልታደርግ ስትሞክር “ሰራዊታችንን ይዘን ወደ ክልላችን እንገባለን። ተቃዋሚዎች ጦር የላቸውም። በቀጣናው ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂ አይደለንም” በማለት አቶ መለስ አሜሪካን ጫናዋን አቁማ ከህወሃት ጎን እንድትቆም ማድረጋቸውን ለጉዳዩ ቅርብ የሆነ ይናገራሉ። ያም ሆነ ይህ እንደራሴ ክሪስ ስሚዝ ኢህአዴግ የውጪውን ዓለም የሚጋልብበትን የፖለቲካ “ጆከሩን” ወይም “ሽብርን መታገል” መርጠው ” ካሁን በኋላ በዚህ ሂሳብ መጫወት አይቻልም” ማለታቸው ቀጣዩን የፖለቲካ ጨዋታ እንደሚያከረው ተገምቷል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar