torsdag 23. mai 2013

ሰበር ዜና፣ ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፉን በታቀደው ቦታና ስዓት እንደሚያካሂድ አስታወቀ


ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ ማብራሪያ
ሕገ ወጥነት ከዓላማችን አይገታንም!!!
ሕግ ምን ይላል?
አዋጅ ቁጥር ፫/፲፱፻፹፫ ዓ.ም
ስለ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት የወጣ አዋጅ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የጠራው አካል ስላለበት ግዴታ በአንቀጽ ፬ ላይ እንዲህ ይላል  አንቀጽ ፬፤ የማሳወቅ ግዴታ፤
፩/ ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ህዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የሚያዘጋጀው ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ከሚካሄድበት ጊዜ ቢያንስ ከ፵፰ ሰዓታት በፊት በጽሑፍ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡
፪/ የማሳወቂያው ጽሑፍ ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ በከተማ ከሆነ የሚደረገው ለከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት፤ ከከተማ ውጭ ከሆነ ለአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ይሆናል፡፡
መልስ ሰጪው አካል የከተማ ወይም የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ያለበትን ግዴታና ኃላፊነት አንቀጽ ፮ ላይ እንዲህ ብሎ ደነግጋል፡፡
አንቀጽ ፮፤ የከተማው ወይም አውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊነት፣
፩/ ከተማው ወይም የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት የሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ጥያቄ በጽሑፍ ሲቀርብለት ሰላምን ከማስፈን ጸጥታን ከማስጠበቅና የሕዝቡን ዕለታዊ ኑሮ እንዳይሰናከል ከማድረግ አንጻር አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡
፪/ ከተማው ወይም የአውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፮ ንዑስ አንቀጽ ፩ የተመለከቱትን ሁኔታዎች በማገናዘብ ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ በሌላ ጊዜ ወይም በሌላ ሥፍራ ቢደረግ ይሻላል የሚል አስተያየት ካለው ምክንያቱን በመግለጽ ይህንኑ ጥያቄው በደረሰው በ፲፪ ሰዓት ውስጥ በጽሑፍ ለአዘጋጁ ማሳወቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሆኖም የከተማው ወይም አውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው ምን ጊዜም በየትኛውም ቦታ ሊካሄድ አይችልም ማለት አይችልም፡፡
ምን ተደረገ?
ሰማያዊ ፓርቲ የጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ ማወቅ የሚገባው በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሰላማዊ ሰልፍና የህዝባዊ ስብሰባ ማሰወቂያ ቢሮ እንዲያውቅ የሚያደርግበትን ደብዳቤ ግንቦት 14 ቀን 2005 ዓ.ም ከጧቱ 4፡00 ሰዓት የተጠቀሰው ቢሮ ድረስ አቅርቧል፡፡ የቢሮው ኃላፊ ደብባቤ አልቀበልም በማለታቸው ከሰዓት በኋላም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ደብዳቤውን እንደገና አቅርቦ አሁንም አልቀበልም በማለታቸው ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ የተለያዩ አካላት እስከ ከንቲባው ፅ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉጋዮች ምክትል ኃላፊ ድረስ በመሄድ ደብዳቤውን እንዲቀበሉ ቢጠየቁም “ደብዳቤ እንዳንቀበል ከበላይ ታዘናል” በማለት በቃል ተመሳሳይ የአንቀበልም መልስ ሰጥተዋል፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ ከፓርቲው በኩል ሦስት ሰዎች ከማዘጋጃ ቤቱ ደግሞ ሦስት ሰዎች የአይን ምስክርነት ባሉበት በሰላማዊ ሰልፍና የህዝባዊ ስብሰባ ማሰወቂያ ቢሮ ኃላፊ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠው ወጥተዋል፡፡ ከዚህም በጠጨማሪ ደብዳቤው በፖስታ ቤት በኩል በሪኮመንዴ እንዲደርስ ተልኳል፡፡
ምን ይደረጋል?
ሰማያዊ ፓርቲ በሕግ የተቋቋመ ህግ የሚያከብር ፓርቲ ነው፡፡ ፓርቲው የሚገዛው ለህግ እንጅ ለውንብድና ባለመሆኑ ሰልፉን በዚህ መልኩ ለማሰናከል የማይቻል መሆኑን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እንዲያውቁት ማሳሰብ ይፈልጋል፡፡ ሰልፉን ለማድረግ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በህግ በኩል የጎደለ አንድም ቅንጣት ነገር ባለመኖሩ ሰልፉ በታቀደው ቦታና ስዓት የሚካሔድ መሆኑን ያሳውቃል፡፡
ግንቦት 15 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar