torsdag 30. mai 2013

የአሜሪካ የህግ ባለሙያዎችና አኢጋን በኅብረት ስራ ጀመሩ!

ዓርብ የፖለቲካና የሙስሊም እስረኛ ጠበቆችን ያነጋግራሉ

aba nsmne
በኢትዮጵያ በግፍ የታሰሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን በተመለከተ የአሜሪካን የህግ ባለሙያዎች ማህበር (ABA – American Bar Association) ሙሉ በሙሉ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ስራ አርብ እንደሚጀምር ተገለጸ። አዲስ አበባ ካሉ የፖለቲካና የሙስሊም ወገን እስረኞች ጠበቆች ጋር የመጀመሪያ ስብሰባ አርብ ግንቦት 23፤2005ዓም ያደርጋሉ። አቶ ኦባንግ ሜቶ የተረሱ እስረኞች ጉዳይም እንደሚካተት ጠቅሰው በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ለታሰሩ ዜጎች ጥብቅና የቆሙ ካሉ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ በቀጥታ እንዲገናኙ ጥሪ አቅርበዋል።
(ABA) በሚል ስያሜ የሚታወቀውና ከተቋቋመ 135ዓመታትን ያስቆጠረው የአሜሪካ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ከ400 ሺህ በላይ የህግ ባለሙያ አባላት አሉት። ይህ በአሜሪካ ትልቅ የተባለ ማህበር በግፍ ለሚሰቃዩ ኢትዮጵያዊያን እስረኞች ድጋፍ ለማድረግ የወሰነው የአኢጋን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ በይፋ የድጋፍ ጥያቄ ባቀረቡ በቀናት ውስጥ ሲሆን፣ በጋራ በተከናወኑ ንግግሮችና የሰነድ ውይይቶች በወር ጊዜ ውስጥ ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት እንደተቻለ ለማወቅ ተችሏል።
ከወር በፊት በተካሄደ የማህበሩ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ንግግር እንዲያደርጉላቸው በተጋበዙት መሰረት አቶ ኦባንግ ህግን abaእየተንተራሰ ዜጎችን በቁም እስርና በወህኒ ቤት እያሰቃየ ስላለው የኢህአዴግ አገዛዝ በስፋት ባስረዱበት ወቅት ማህበሩ እሳቸው ከሚመሩት ድርጅት ጋር በትብብር ለመስራት ፈቃዱን አሳይቶ እንደ ነበር አቶ ኦባንግ ለጎልጉል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ኢህአዴግ ህግን ከለላ በማድረግ በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ግፍና ወንጀል፣ ለአፈና ተግባሩ ማስፈጸሚያም የጸረ ሽብርተኝነትን፣ የመያዶችን፣ ወዘተ ህጎችን በማውጣት ዜጎችን ለወህኒ ቤትና ለቁም እስር፣ ለስደት፣ ለስቃይ መዳረጉን፣ የፍትህ አካላቱን ህግን በሚያከብሩና ፍትህ በሚያስፈጽሙ ገለልተኛ አካሎች ሳይሆን ራሱ በመሠረተው ተቋም እያመረተ የሚጠቀምባቸው የፖለቲካው መሳሪያዎቹ ስለመሆናቸው፣ በመዘርዘርና ማስረጃ በማጣቀስ አቶ ኦባንግ ለጉባኤው መናገራቸውን አመልክተዋል።
ቀደም ሲል ጀምሮ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የስራ አስፈጻሚዎች የሚታወቁትም ሆነ ሚዲያው የዘነጋቸው ዜጎች ጉዳያቸው ዓለም ዓቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ በያቅጣጫው እየተደረገ ካለው የተለያየ  ጥረት በተጨማሪ ሲመክርበት የነበረው ጉዳይ እንደሆነ በመግለጽ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ኦባንግ “ተጽዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉት አካላት በራሳቸው ሰዎች በቂ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ታላቅ ተግባር ነው። ድርጅታችን እንደ ስኬት ይቆጥረዋል። ዓርብ በዝርዝራችን ካገኘናቸው የታዋቂ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪ ጠበቆች ጋር የስካይፕ ስብሰባ ይካሄዳል። በቀጣይ አገር ቤት በመሄድ ባመቻቸው መንገድ ስራቸውን ያከናውናሉ” ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ጥያቄ በማንሳታቸው የታሰሩት ወገኖች፣ ወዘተ ጠበቆች ጋር በስካይፕ ንግግር እንደሚደረግ አቶ ኦባንግ አስታውቀዋል። እስከዛሬ ጆሮ ያልተሰጣቸው ወገኖች ጉዳይ አደባባይ ከማውጣት በተጨማሪ የጋራ ንቅናቄው ባቋቋማቸው ግብረኃይሎች አማካይነት ወደ ህግ የሚሄዱ፣ ሌሎች አብረው መስራት የሚፈልጉ አካላት የሚያቀርቧቸውን አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክስ መስርቶ ለመሟገት ማህበሩ ዝግጁ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “አስፈላጊውን የህግ ድጋፍ የሚፈልጉ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ጥያቄያቸውን ለጋራ ንቅናቄው ማቅረብ ይችላሉ” ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ማህበሩ መንግስትን የሚያማክሩ፣ የሚመክሩ፣ ፖሊሲ በማርቀቅ ስራ ላይ የተሰማሩ ታዋቂ የህግ ባለሙያዎች፣ ለዓለም ዓቀፍ ሚዲያና ኔትወርኮች ቅርበት ያላቸውና ተሰሚነታቸው የጎላ በመሆኑ እንዲህ ካሉ አካላት ጋር በጨዋነት መስራት በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ለማስተጋባት መልካም አጋጣሚ ማመቻቸት እንደሆነም አቶ ኦባንግ አመልክተዋል።
“… ኢህአዴግ በስደተኛነት ስም ደጋፊዎቹን በስርዓቱ የተገፉ በማስመሰል የሃሰት ማስረጃ እያስጨበጠ  በአሜሪካ፣ በካናዳና በተለያዩ የምዕራብ አገራት ያሰማራቸውና በተቀነባበረላቸው መረጃ የስደት መኖሪያ ፈቃድ ካገኙ በኋላ ስደተኛውን እንዲሰልሉና ለሥርዓቱ እንዲሰሩ እያደረገ መሆኑ፤ በተለያዩ አገራት በገቢር የተያዙ መረጃዎችና ዋቢ ክስተቶች መኖራቸውን የተረዳው የባለሙያዎቹ ማኅበር ጉዳዩን በጥልቀት እንደሚያየውና ያለውን ከፍተኛ የሰው ኃይል በመጠቀም ከአኢጋን ጋር እንደሚሰራ ከሌሎች ማኀበራት ጋር በመሆንም በተለይ በምዕራቡ ዓለም የተሰገሰጉትን አስመሳይ ስደተኞች ወደ ፍትህ የማምጣቱ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ለድርጅታቸው አረጋግጠዋል” በማለት ከዚህ ቀደም ለጎልጉል ስለተናገሩት አስተያየት እንዲሰጡ አቶ ኦባንግ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
“ኢህአዴግን የሚደግፉ ዜጎችም ቢሆኑ ለጋራ ንቅናቄያችን ልጆቹ ናቸው” በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት አቶ ኦባንግ “ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ምስጢረኛ ለመሆን እገደዳለሁ። አንድ ነገር ለማስታወስ ያህል ግን ምዕራባውያን አሠራራቸው መጭበርበሩን ካረጋገጡ ምህረት የላቸውም። ከሰብአዊነትም አንጻር ቢሆን አገሩ መኖር ያልቻለን ዜጋ ስደት አገር ድረስ እየተከታተሉ ማሳደድ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። በህግም አይፈቀድም። እንደዚህ ካሉት ጋር የሚተባበሩ አገሮችን ህግ ፊት በማቆም በህግ ስለፍትህ እንከራከራል” የሚል መልስ ሰጥተዋል።
ABA የሚባለው የህግ ባለሙያዎች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት ሲያከብር ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት አቶ ኦባንግ ሜቶ በርካታ ጉዳዮችን በማንሳት ድጋፍ ጠይቀው አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኙ፣ ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል። አቶ ኦባንግ እንደሚሉት አርብ የሚደረገው ንግግር የድጋፉና አብሮ የመስራቱ ሂደት መጀመሪያ ነው። ሥራው ጊዜ የሚወስድና እልህ የሚያስጨርስ መሆኑን ሁሉም እንዲያስተውለውና ፈጣን ውጤት በመጠበቅ ቶሎ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ሁሉም ዜጋ አለኝ የሚለውን መረጃ ለጋራ ንቅናቄው በመላክ ትብብሩን እንዲቀጥል ጨምረው ገልጸዋል፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar