onsdag 20. mars 2013

ቋንቋ የሕወሃት የጥፋት ሚዛን እና የመጭው ዘመን የኢትዮጵያዊያን ስጋት


መጋቢት 19 2013

ልቃቂት ነው ሂዎት፤ በእንዝርት ላይ እንደሚሽከረከረው የጥጥ ንድፍ ዘለላ እየተጠማዘዘ እየተሽመለመለ፣ እየጠበቀና እየላላ፣ እየተወጠረና እየረገበ የሚጠመጠም የሂዎት አንጓ። ያንዱ ሂዎት ዘርፍ በሌላው መሰረት ላይ እየተመጠነና እየተደረበ የሚከወን ኩነት። የስረኛው የላይኛውን ተሸክሞ፣ የላይኛውም በስረኛው ላይ ያለጭንቀት ተመቻችቶና ተንደላቆ የሚቀመጥበት ልቃቂት ነው ሂዎት። ደግሞም እንደ ታሪክ የሚመዘዝ፣ የሚተረክ እንደ ልቃቂት የፈትሉን ጫፍ ይዘው የሚተረትሩት የሚያወጉት፤ ክፉ ደጉን፣ ሳቅ ዋይታውን፣ የጀግንነት የፍቅር ወጉን፣ ያንን ዘመን ያን የጥንቱን፣ የነንቶኔን የነንቶኔን፣ ምርቃቱን ቱፍቱፍታውን፣ የልጅነት ያፍላነቱን፣ የሚያሳየን የሚያሞቀን፣ ወዲያው ደግሞ የሚያበርደን፣ አበሳጭቶ የሚያነደን፣ አስደስቶ የሚያነጥረን፣ ያው ሂዎት ነው ልቃቂቱ፣ የጥንት ያሁን ወደፊቱ፣ እናም እንዲህ እንዲህ ብሎ፣ ስቃያችን አበሳችን ፉከራችን በያይነቱ ተጠቅልሎ፣ አሁን እኛ ከለንበት እኔ ዛሬ ከማወራው፣ ታሪክ አንጓ እንኳ ለመድረስ 68 ዓመት ሞላው። ይችን ትንሽ የታሪክ ጫፍ፣ ይዘን ሽምጥ ስንከንፍ፣ ልክ ከ68 ዓመት ደጃፍ፣ ሆሎኮስት ነው የሚገዝፍ። ከምስራቅ ጫፍ ጃፓን ጠረፍ፣ እስከ አሜሪካ ዳር ድንበር ጽንፍ፣ ከሩሲያ ጀርመን ጓዳ፣ ሳውዝ አፍሪካ ድረስ የፈነዳ፣ የዓለምን ቅስም የሰበረ፣ ያማረረ ያሳረረ፣ አውራ ኩነት እኩይ ተግባር ይህ ነበረ። እኔም እንግዲህ ዛሬ፣ ከታሪክ አንጓ ቆንጥሬ፣ ከሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር እየቃኘሁ፣ ዝግጅቴን ያው ለእናንተ ብያለሁ።
ኩነቱ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በቅርብ ርቀት የተከወነ ቢሆንም ለወቅቱ ከፍተኛ የሚባል ዝግጅት ተደርጎበታል። ዓለምን በሁለት ጎራ አቧድኖ አቆራቁሷል አፋጅቷልም። እስከ አሁንም ድረስ ለማሰብ የሚያዳግቱ፣ ለማስታወስ የሚዘገንኑ፣ ለማየት የሚቀፉ በፍርሃት የሚያርዱ ድርጊቶች ተከውኖበታል። በወቅቱ የወደመውን ንብረት የጠፋውን ሃብት መጠን ለጊዜው እንተወውና ስድስት ሚሊዮን አውሮፓዊያን ይሁዲዎችን ጨምሮ ካስራ አንድ ሚሊዮን በላይ ንጹሃን ዜጎች ሂዎታቸውን ገብረውበታል- ሆሎኮስት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት።
ዓላማዬ ስለ ሁለተኛው ዓለም ጦርነት መተረክ ወይም በወቅቱ ስለጠፋው የንብረትና የሂዎት ብዛት መዘርዘር አይደለም፤ ሆሎኮስት እየተባለ ስለሚታወቀውና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት አንድን ዘር ለይቶ የማዳከም፣ የማመናመንና የማጥፋት እኩይ ስራ በእኛም አገር የመከሰቱ አይቀሬነት ስላሰጋኝ አንዳንድ ለማለት እንጅ።
ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ በጀርመን ፖለቲካ በአክራሪ ብሔርተኛ ጀርመኖች አማካኝነት በሰፊው ሲቀነቀን የነበረው ፓን ጅርመኒዝም ጀርመንኛና የጀርመን ተወራራሽ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሀገሮችን ወደ አንድ ሀገርነት ለመቀየር ብዙ ስራ ሰርቷል። በመጨረሻም በአዶልፍ ሂትለር የሚመራ ቋንቋን ብሔርንና ዘርን መሰረት ያደረገ ናዚ ፓርቲን መስርቷል።
በሀገራችንም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ1950ዎቹና 1960ዎቹ ሲቀነቀኑ ከነበሩት የዲሞክራሲ ጥያቄዎችና የብሄሮች እኩልነት ፍላጎቶች ባፈነገጠ መልኩ፤ የትግራይን ትንሽ ጎጥ ከኢትዮጵያ ነጥሎ በማየትና (ፓን ትግራያኒዝም ልንለው እንችላለን) የዚህን ክልል ፍላጎት ብቻ ለማሟላት የሚተጋ ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) የተባለ ድርጅት በቀድሞው ጎጠኛ መሪ መለስ ዜናዊ አማካኝነት መስርቷል። ይህ ድርጅት ልክ እንደ ፓን ጀርመኖቹ ናዚ ፓርቲ ቋንቋን ብሔርንና ዘርን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት በመመስረት ባንዱ ወይም በሌላ ምክንያት ትግሪኛ የሚናገሩ አካባቢዎችን በሙሉ የትግራይ ክልል አካል ናቸው በማለት በራሱ የቅዠት ካርታ ውስጥ አካቷል። በዚህም ምክንያት ከወሎ፣ ከጎንደር እንዲሁም ከአፋር ሰፋፊ መሬቶችን ወደ ትግራይ ክልል ተካተዋል።
ሂትለርና ናዚ ፓርቲ ምክንያቱ እስካሁንም ድረስ በግልጽና በእርግጠኝነት ባይታወቅም በሃብት በልጠውናል፣ ከኛ ይልቅ እነሱ ከፍ ብለው ታዩ፣ ሃይማኖታቸውን ከመጥላትና ጀርመን ለአርያን ብቻ ከሚል እጅግ ጠባብ አስተሳሰብ በመነሳት በጀርመንና በደፍን አውሮፓ ይኖሩ የነበሩ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አይሁዶችን በግፍ ጨፍጭፏል። ሕወሃትም በኢትዮጵያ ገና ከጅምሩ በ1968 ዓ/ም ካወጣው ጥበት ያጠበበው ማንፌስቶው ጀምሮ አማራ የሚባለውን ብሔር አምርሮ ጠልቷል። የትግራይ ሕዝብ እራሱን እንዲጠላ፣ በአካባቢውም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስራ እንዳያገኝ፣ በትምህርት በጤና በግብርና ወደ  ሗላ እንድንቀር፣ በትግራይ አካባቢ ኢንዱስትሪዎች እንዳይገነቡና ባጠቃላይ የአማራ ብሔር በትግራይ ብሔር ላይ ከፍተኛ የብሔር ጭቆና ታካሂዳለች ይላል ጥበት ያጠበበው ማኒፍሰቶ። ከዚህም እጅግ በከፋ መልኩ ልክ ናዚዎች የይሁዲዎችን ሃይማኖት እንዳራከሱት ሁሉ ሕወሃትም ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን የአማራው የግል ሃብት አድርጎ በመቁጠር የትምክህተኛውና የነፍጠኛው ዋሻ በማለት የብዙውን ኢትዮጵያዊ ሃይማኖት ሲያራክስ መቆየቱ ያደባባይ ሚስጥር ነው።
ናዚዎች ይሁዲዎች እንዲጠሉ፣ እንዲገለሉ፣ ስራ እንዳያገኙ፣ እንዲዋከቡ፣ ሃብታቸው እንዲወረስ፣ እንዲሰደዱና ሕዝባዊ ፖሊሶችንና ብሄራዊ ወታደሮችን ሳይቀር በማዝመት በግፍ እንዲገደሉ አድርገዋል። ሕወሃትም በኢትዮጵያ አማራው ቦታ እንዳይኖረው በርትቶ ሰርቷል። ስራ እንዳያገኝ የተለያዩ የተንጋደዱ መለኪያዎችን በመጠቀም አስወግዷል። በስራ ላይ የነበሩትንም ውጤት ተኮር፣ ቢ ፒ አርና የመሳሰሉትን ስልታዊ መመንጠሪያች በመጠቀም ከስራ አፈናቅሏል። በልማት ሰበብ አማራው ከይዞታ መሬቱ ከመኖሪያ ቤቱ እንዲፈናቀል አድርጓል። ከዚህም በባሰ መልኩ ሲጨቁናችሁ የኖረው አማራው ነው በማለትና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ሕወሃት የራሱን ፖሊሶችና ወታደሮች በማዝመት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አማራው እንዲመነጠርና እንዲገደል ከማድረጉም በተጨማሪ ከነ ሂወቱ ወደ ገደል እንዲወረወር ማድረጉ የቅርብ ጊዜ አሳዛኝ ትዝታችን ነው።
ሂትለርና ናዚ ፓርቲው ጥላቻቸው እጅግ አይሎ ‘ጀርመን ለአርያን ዘር ብቻ ይሁዲዎች ወደ ሀገራቸው’ በማለት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ይሁዲዎችን ከጀርመንና ከአጎራባች የአውሮፓ አገሮች እንዲሰቃዩ፣ እንዲዋከቡና ሃብታቸው እየተወረሰ እንዲባረሩ አድርጓል። በመጨረሻም እስካሁንም ድረስ ሆሎኮስት በመባል የሚታወቀውን ዘግናኝ ግድያ ከስድስት ሚሊዮን በሚበልጡ ይሁዲዎች ላይ ፈጽሟል። ሕወሃትም በሀገራችን በአማራው ላይ ተመሳሳይ ድርጊት በመፈጸም ላይ ይገኛል። ሕወሃት ከናዚም እጅግ በከፋ መልኩ አማራውን ከራሱ ሀገር በማፈናቀል ሰርቶ የመኖር መብቱን አሳጥቶ በስማሰቃየት፣ በማዋከብና ሰርቶ ያፈራውን ሃብት በግፍ በመውረስ እያንከራተተው ይገኛል። ምናልባትም የቀረው ልክ እንደ ናዚ ጀርመን በማጎሪያ ካምፖች በማጠራቀም የህብረት ግድያ ማከናወን ብቻ ነው። ይህንንስ እንዳይከውን ሕወሃትን ምን የሚያግደው ሃይል አለ? ለሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ህግጋት የሚገዛ አይደለምና፤ አበቃሁ።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar