torsdag 26. juni 2014

ኦክስፎርድ፡ ኢትዮጵያ ከዓለም 2ኛዋ ድሃ አገር ናት

f78a1330f27fafbdf18deabc7e6add28_Mኢትዮጵያ ከ108 የዓለም ሃገራት በድህነት ከአፍሪካዊቷ ሃገር ኒጀር ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ  የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያመለከተ ሲሆን የኢኮኖሚ  ባለሙያዎች ሃገሪቷ ድሃ መሆኗ የሚስተባበል አይደለም ብለዋል፡፡ 

ሰሞኑን  ዩኒቨርሲቲው ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት፤ በኢትዮጵያ ከሚኖሩ ዜጎች 76 ሚሊዮን ያህሉ ድሆች ሲሆኑ በድሆች ብዛትም ከህንድ፣ ከቻይና፣ ከባንግላዴሽና ፓኪስታን ቀጥሎ ኢትዮጵያ  በ5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብሏል፡፡ 

የድህነት መጠኑን በመቶኛ ስሌት ያስቀመጠው ጥናቱ፤ ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ህዝቧ 87.3 በመቶው ድሃ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 58.1 በመቶው ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ያልተሟሉለት ምስኪን ተመፅዋች ዜጋ ነው ብሏል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የአገራትን የድህነት ደረጃ የለካው የትምህርት፣ የጤናና የኑሮ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረጉ አስር መስፈርቶችን  በመጠቀም ሲሆን፣ በአገሪቱ በገጠር ከሚኖረው ህዝብ 96.3 በመቶው፣ ከከተማ ነዋሪው ደግሞ 46.4 በመቶው  በድህነት አረንቋ ውስጥ እንደሚኖር በሪፖርቱ  ተመልክቷል፡፡ 

የድህነቱ መጠን በክልል ደረጃ ሲታይ፣ የሶማሌ ክልል 93 በመቶ ድሃ ህዝብ በመያዝ ቀዳሚ ሲሆን፤ ኦሮምያ በ91.2 በመቶ ሁለተኛ፣ አፋር በ90.9 በመቶ ሶስተኛ፣ አማራ በ90.1 በመቶ አራተኛ፣ ትግራይ በ85.4 በመቶ አምስተኛ ደረጃን ይዘው እንደሚገኙ ጥናቱ  ጠቁሟል፡፡ 20 በመቶ ድሃ ህዝብ ይኖርባታል ያላትን አዲስ አበባ ከአገሪቱ አነስተኛ ቁጥር ያለው ድሃ በመያዝ ቀዳሚ ያደረጋት ይሄው  ጥናት፣ ድሬደዋን በ54.9 በመቶ፣ ሐረርን በ57.9 በመቶ ሁለተኛና ሶስተኛ አድርጎ አስቀምጧቸዋል፡፡

 በሌላ በኩል የአፍሪካ ልማት ባንክ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መረጃ፣ ኢትዮጵያ ባለፉት አስር  አመታት በአማካይ ከአስር በመቶ በላይ እድገት ማስመዝገቧን ሲመሰክር፣ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ቻንታል ሄበርት በበኩላቸው፤ አገሪቱ የከፋ ድህነትን በመቀነስ ረገድ ስኬታማ መሆኗን ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ 

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲን የጥናት ሪፖርት በተመለከተ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንትና የኢኮኖሚ ባለሙያው  አቶ ሙሼ ሰሙ በሰጡት ምላሽ፤“ረሃቡንና ጥማቱን እንዲሁም የኑሮ ውድነቱን በተጨባጭ እየኖርኩት ስለሆነ አውቀዋለሁ” በማለት የኢትዮጵያን  ድህነት  ለማመን የኦክስፎርድና የአይኤምኤፍ ሪፖርት አያስፈልገኝም ብለዋል፡፡ 
“የድህነት መለኪያው  መስፈርት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዓለም የተመዘነበት  ነው፤ በእርግጥም ውጤቱ  ኢትዮጵያን በትክክል ይገልፃታል” ያሉት አቶ ሙሼ ፤ዜጎች ራሳቸው ድህነቱን እየኖሩት ስለሆነ የማንንም ምስክርነትና ማስተባበያ አይፈልጉም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ እንደተለመደው ሪፖርቱን ያወጡት የአገራችንን እድገትና ብልፅግና ማየት የማይፈልጉ ጠላቶቻችን ናቸው በማለት ራሱን ማታለል እንደሌለበት የገለፁት አቶ ሙሼ፤ መንግስት አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የተለየ መላ መዘየድ  እንዳለበት የኦክስፎርድ ጥናት  አመላካች ነው ብለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ ማንም አይክደውም ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፤“ሪፖርቱ የእኛን ፍላጎት ካላንፀባረቀ አንቀበልም የሚለው የተለመደ የኢህአዴግ ምላሽ   አያዋጣም፣ እንደውም ራሱን ለመፈተሽ የሪፖርቱን መውጣት እንደ መልካም አጋጣሚ ሊቆጥረው ይገባል” ሲሉ መክረዋል፡፡ 

በዜጐች መካከል ሰፊ የሃብት ልዩነት መኖሩን የጠቆሙት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው፤ “በኢትዮጵያ ድህነት አሁንም አለ” የሚባለው ትክክል ነው ብለዋል፡፡ “ትላልቆቹ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ተቋማት- እነ ንግድ መርከብ፣ ቴሌኮም የመሳሰሉት በመንግስት ስር በመሆናቸው የሚያገኙት ገቢ መልሶ ለመሰረተ ልማት ነው የሚውለው፡፡ ለእያንዳንዱ ዜጋ የሚደርስበት መንገድ  የለም፡፡ የኢኮኖሚ እድገቱን በGDP (አጠቃላይ የምርት እድገት) ስንመለከተው፣ የድሃውን ህዝብ ትክክለኛ ህይወት እያሳየንም፡፡” በማለት ምሁሩ  አስረድተዋል፡፡
ፕሮፌሰር አማር ካስያን የሚባሉ ምሁር፣ የሰብአዊ  እድገት መለኪያ (human development indicators) ማውጣት አለብን በማለት ትምህርት፣ ጤናና  ረጅም እድሜ መኖር የሚሉ ሶስት መለኪያዎችን  እንደፈጠሩ የጠቆሙት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ ረጅም እድሜ የሚለው መለኪያ በምግብ ራስን መቻል ስለሚያካትት  እንደተባለውም ኢትዮጵያ ወደ ኋላ ቀርታለች ብለዋል፡፡ 
የሚሊኒየም የልማት ግቦች ተብለው የተነደፉትን በእርግጠኝነት እንደርስባቸዋለን፤ እንደውም እኔ ነበርኩ ስመራው የነበረው ያሉት ምሁሩ፤ “በእቅዱ እንደተቀመጠው ሁሉም ህፃናት ትምህርት ቤት የመግባት እድል አላቸው፣ ነገር ግን 1ኛ ደረጃን የመጨረስ እድላቸው የመነመነ ነው፡፡” በማለት በሚሊኒየም የልማት ግቡ የተቀመጠውን አሳክተናል ማለት የሰውን ልጅ ልማት አሳክተናል ማለት እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ 

በጤና ዘርፍም በርካታ የጤና ተቋማት  ተገንብተዋል፣ጥያቄው ግን በቂ ሃኪሞችና  የህክምና መሳሪያዎች ተሟልቶላቸዋል ወይ የሚለው ነው ያሉት ምሁሩ፤ እንዲያም ሆኖ በጤና መስክ መንግስት የሰራው ስራ የሚመሰገን ነው ሲሉ አድንቀዋል፡፡ 

በቅርቡ ወደ አድዋ ሄደው ያዩትና በሌሎች ክልሎች በስራ አጋጣሚ የተመለከቱት የድህነት ሁኔታ የሚዘገንን እንደሆነ ዶ/ሩ አልሸሸጉም፡፡ በመንግስት ሚዲያዎች “ህብረተሰቡን በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተጠቃሚ አድርገናል” የሚሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ መስማታቸውን የጠቀሱት ምሁሩ፤ ጥያቄው እነዚህ ፕሮጀክቶች የምን ያህል ሰው ህይወት ቀይረዋል  የሚለው ነው ብለዋል፡፡ 
“ቻይና ባለፉት አምስት አመታት 5 ሚሊዮን ህዝብ ከድህነት  አውጥታለች፤ ሆኖም  ዛሬም ከአፍሪካ ህዝብ ብዛት የሚልቅ ድሆች አሏት፤ በነደፈቻቸው ስትራቴጂዎች ግን በፍጥነት ዜጐቿን ከድህነት እያወጣች ነው” ሲሉም ዋናው ጉዳይ ህዝቡን ከድህነት አረንቋ ማውጣት  እንደሆነ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ 

በእድገት ጉዳይ ላይ በአገር ደረጃ ግልጽ የሆነ ህዝባዊ ውይይት አለመኖሩን የተቹት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ መንግስት ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ያወጣው ሪፖርት ሃሰት ነው የሚል ከሆነ፣ ያንን  በተግባር ማረጋገጥ መቻል አለበት ብለዋል፡፡ 

የኦክስፎርድን ሪፖርት እኔም አንብቤዋለሁ፤ ነገር ግን ሪፖርቱን እንዴት እንደሰሩት አናውቅም ያሉት በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሀጂ ኢብሳ፤ “እኛ እንደመንግስት ማንም እብድ ከመሬት ተነስቶ አጠናሁ ብሎ የሚያወጣውን አንቀበልም” ብለዋል፡፡ “የመረጃው አላማ ምንጩና መነሻው ምንድን ነው? የሚለውን አናውቅም፤ ከኛ ጋርም ግንኙነት የለውም”፡፡ በማለት መልሰዋል- ሃላፊው፡፡ “እኛ በሃገር ደረጃ ድህነት ምን ያህል ቀንሷል የሚለውን የምንለካው አለም በተቀበላቸውና በተስማማባቸው መለኪያዎች ተጠቅመን ነው” የሚሉት ኃላፊው፤ “ከድሮው በተለየ ከአለማቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ጋር የኢትዮጵያ መንግስት ተቀራራቢ የሆነ የእድገት ሪፖርት እያወጣ መሆኑ የኦክስፎርድን ጥናት ተቀባይነት ያሳጣዋል” ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከኒጀርና ከኢትዮጵያ በመቀጠል “የአለማችን ቀዳሚ ድሆች” ብሎ ያሰለፋቸው ስምንት አገራት አፍሪካ ውስጥ ሲሆኑ እነሱም  ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ብሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ላይቤሪያ፣ ጊኒና ሴራሊዮን ናቸው፡፡ 

ምንጭ- አዲስ ዜ

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar