Sept 28, 2014
አምባገነኖች በውድም በግድም ህዝብ ስብሰባ ጠርተው ህዝቡ ፊት በቆሙ ቁጥር ሌት ከቀን የሚያባንናቸውን የተመረረ ህዝብ የነጻነት አመጽ የሚያስቀሩ ይመስላቸዋል። የህዝብ ሃብትና ጊዜ በከንቱ እንዳሻቸው እያባከኑ፣ ነጋ ጠባ ስብሰባ፣ ግምገማ፣ “ስልጠና” ወዘተ የሚጠሩት ህዝብ የነሱን ፍላጎትና ውሳኔ የኔ ነው ብሎ የሚቀበላቸው፣ የሚሰማቸው እና ፍርሃታቸውን ያቀለላቸው እየመሰላቸው ነው።
የወያኔ ጉጅሌና ሎሌዎቹ ሰሞኑን ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ ሰራተኞችንና መላውን ለፍቶ አዳሪ ተሰብሰብና እናሰልጥንህ የሚሉት በአገዛዛቸው የተንገፈገፈው ህዝብ ምሬቱ ወደ አመጽ እንዳይገነፍል ያደረጉ እየመሰላቸው ነው። ዲሞክራሲንና የህዝብ ወሳኝነትና ልእልናን በተቀበሉ ሀገሮች እንደወያኔና ቀደም ብሎ እንደነበረው የደርግ ስርአት የመንግስት ስብሰባ የማይዘወተረው ለዚህ ነው። የህዝቡን ፍርድ በስብሰባ እና በስልጠና እንደማያቆሙት ስለሚያውቁ ህዝብን ስለሚያከብሩ ነው።
ሰሞኑን በመላ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ወያኔዎች ‘ስልጠና’ ብለው የሚጠሩት፣ በይዘቱ አያቶቻችንን ድሮ ላውጫጪኝ ይጠቀሙበት የነበረውን አፈርሳታ የመሰለ የመደናቆሪያ ስብሰባ አላማው ግልጽ ነው።
አላማው ህዝብ ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ ቢቻል ለማደንዘዝ ካልተቻለም ለማስፈራራት ነው። ግፍን፣ ፍትህ ጥፋትን ልማት፣ ጭካኔን፣ ርህራሄ ለማስመሰል አፈጮሌ ነኝ ያለ ካድሬ ሁሉ የምላስ ጂምናስቲክ የሚሰራበት ጉባኤ ነው። ከተሰብሳቢው ህዝብ ከረር ያለ ጥያቄ በመጣ ቁጥር መላ ቅጡ የሚጠፋቸውም ለዚህ ነው። እነሱ የተዘጋጁት የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ አይደለማ! የህዝቡን ጥያቄ እንደማይመልሱማ ያውቁታል።
ነገሩ መልከ ጥፉን በስም ይደገፉ ሆነና ይህንን ቧልት ‘ስልጠና’ ብለው ይጠሩታል። እነዚህ ራሳቸው መሰረታዊ ስልጣኔ የሌላቸው አሰልጣኞች መምህራኑን ስለትምህርት ጉዳይ ሊያሰለጥኗቸው ሲንጠራሩ አይፍሩም። ባለሙያውን ሁሉ በሙያው ካላ ሰለጠንህ ብለው ግዳጅ ስብሰባ ያጉሩታል። ይህ የወያኔ ተግባር እውቀትና ስልጣን ከተምታታባቸው የወያኔ ጉጅሌዎች ስለመጣ ብዙ ላያስገርም ይችል ይሆናል። እንደ ህዝብና እንደ ዜግነታችን ግን በያንዳንዳችን ላይ እየደረሰ ያለ ውርደት ነው። ወያኔ ካላዋረደንና ሰበአዊ ክብራችን ካላሳነሰ የሚገዛን አልመሰለውም።
ግንቦት 7 ውስጥ ያለን የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች ይህ ዘርፈ ብዙ ውርደት እንዲቆም ነው የምንታገለው። የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ዘመን ይህን በመሰለ ውርደት ውስጥ ሊኖር የሚገባው ህዝብ አይደለም ብለን እናምናለን። የማያቋርጠው ጥሪያችን ዛሬም ተመሳሳይ ነው። ፈልገናቸው ሳይሆን በሃይል ራሳቸውን የጫኑብንን የወያኔ ጉጅሌዎች ከጫንቃችን ላይ እናራግፋቸው።
በአንድነት እንነሳ! በያለንበት ለዚህ ውርደት እምቢ እንበል። ውርደታችን እምቢ ያልን ቀን ይቆማል። ያን እለት ጨለማው ይገፈፋል። የነጻነታችንና የክብራችን ጎህ ይቀዳል።
በያለንበት እምቢ እንበል! ስለተገፋንና ስለተዋረድን ማመፅ መብታችን ነው። የቻልክ ተቀላቀለን። ያልተመቸህ በያለህበት በራስህ አነሳሽነት ራስህን አደራጅ። የነጻነታችን ቀን ቅርብ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar