tirsdag 20. mai 2014

በቡራዩ ከተነሳው ተቃውሞ ጋር አሁንም በርካታ ወጣቶች ታስረው እንደሚገኙ ታወቀ

ግንቦት ፲፪ (አስራ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአዲስ አበባ አዲሱ ካርታ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በቡራዩ ከታሰሩት ከ200 በላይ ወጣቶች መካከል ከ40 በላይ የሚሆኑት አሁንም ታስረው ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን የእስር ቤት ምንጮች ገልጸዋል።

አብዛኞቹ በ25 ሺ ብር ዋስ ወይም በቦታ ካርታ እንዲፈቱ ቢደረግም ገንዘብ መክፈል ያልቻሉትና ከኦነግ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተብለው የተጠረጠሩት እንዳይፈቱ ተደርጓል። እስረኞቹ ፍርድ ቤት ሳይቀረቡ በፖሊስ ዋስ ብቻ 25 ሺ ብር እየከፈሉ እንዲወጡ መደረጉ ግልጽ ዘረፋ መሆኑን አንዳንድ ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል።
በእስር ላይ ከሚገኙት 6 ሴቶች መካከል አያንቱ የምትባለዋ ወጣት እጆቿ በድብደባ መሰባበሩንና በከፍተኛ ህመም ላይ እንደምትገኝ ታውቋል።
ጋዲሳ እና ዳውድ ሃሰን የተባሉት እስረኞች በኦነግ አባልነት በመጠርጠራቸው በዋስ እንዳይፈቱ ተደርጓል።
ጆቴ፣ ስራታ እና ስሮንሳ ፋይሳ ደግሞ የአዋሽ ባንክ ሰራተኞች ሲሆኑ እነሱም በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጸመባቸው ነው። ጋዲሳ የተባለው የመንግስት ሰራተኛም ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ይጠቀሳል።
ንጉማ፣ ወጋሪ፣ ኡመድ ኡመርና ዳባ ቱፋ የተባሉትም እንዲሁ ከፍተኛ ድብደባ የተፈጸመባቸው በመሆኑ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
በክልሉ ውስጥ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተይዘው የታሰሩ ሲሆን አንዳንዶች በገንዘብ ዋስ ሲለቀቁ በርካቶች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።
በሌላ ዜና ደግሞ በምስራቅና ምእራብ ወለጋ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የሌሎችን ብሄር ሰዎች እያሰቃዩ መሆኑን ለኢሳት የሚደርሱት መረጃዎች ያመለክታሉ።
በወረዳና በዞን ደረጃ የሚሰሩ የኦህዴድ ሹሞች የሌሎች አካባቢ ተወላጆችን አቤቱታ እና ችግር ለማየት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ፣ የሌሎች አካባቢ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሆን ተብሎ እንደተቀናበረ በሚያሳይ መልኩ የተደራጁ ወጣቶች ማታ ማታ በሌሎች አካባቢ ተወላጆች ቤቶች ላይ ጉዳት ሲያደርጉ ሰንብተዋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው ሰዎች እንደሚሉት የኦህዴድ ባለስልጣናት በሚዲያ ቀርበው የሚናገሩትና በተግባር እየፈጸሙ ያሉት ድርጊት የተለያየ ነው።
ህወሃት ብሄሮችን እርስ በርስ በማጋጨት በአገር ውስጥ የገጠመውን አስተዳደራዊ ችግር አቅጣጫ ለማስቀየር እየሞከረ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar