ምርቃቱ የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ግጭት ከተጀመረበት 20ኛ ዓመት ጋር ገጥሟል
ኢትዮጵያን እየመራ የሚገኘው ኢህአዲግ/ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከቀን ወደ ቀን እርስ በርሱ እንዳይተማመን፣ እንዲነቃቀፍ፣ እንዲጠራጠር ከእዚህ ባለፈ ደግሞ ግጭት እንዲፈጠር እያደረገ 22 ዓመታትን ዘለቀ። ህዝቡ እለት ከእለት በገዢው መንግስት የሚወጠኑለትን የእርስ በርስ ማጋጫ ተንኮሎች እየተመለከተ ልቦናው በእጅጉ እየደማ ነው።
አንድ ወራሪ የውጭ ጠላት ሊሰራ የሚችለውን ያህል ህዝብን ከሕዝብ ጋር የማጋጨት ሥራ ኢህአዲግ/ወያኔ በትክክል ሰርቶበታል። የሃገሪቱን ፌድራል አስተዳደር በየትኛውም ዓለም ያልታየ ቋንቋን መሰረት ያደረገ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ደገሰላት። ፌድራላዊ አስተዳደር በዘመናዊው ዓለም አንዱ እና አማራጭ የአስተዳደር ዘይቤ ይሁን እንጂ በየትኛውም ሀገር መሰረት የሚያደርገው የመልክዓ ምድርን አቀማመጥ እና ታሪካዊ አሰፋፈርን ነው። እርግጥ ነው ጣልያን ሀገራችንን በወረረ ዘመን አሁን ወያኔ የሚጠቀምበትን የክልል አስተዳደር የመሰለ ቋንቋን መሰረት ያደረገ የአስተዳደር መዋቅር ዘርግቶ ነበር።
አንዳንዶች የአሁኑ ቋንቋን መሰረት ያደረገ አስተዳደር የብሔር ብሄረሰቦችን መብት ከማስከበር አንፃር የሚመስላቸው የዋሃን አይጠፉም። ግን ፈፅሞ አላማው ይህ ላለመሆኑ ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል።እርግጥ ነው የህዝብ ባህል ማለትም ቋንቋው፣ አለባበሱ፣ ታሪኩ ወዘተ ሊጠበቅለት እና ከለላ ማግኘት አለበት። ይህ ከለላ በማግኘት መብት ስም ወንጀል ሲሰራ፣ ቁርሾ በባትሪ እየተፈለገ ሲራገብ እና ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ሲውል ነው ወንጀሉ።
ኢህአዲግ/ወያኔ ሕዝብ እርስ በርሱ በጎሳ ሲጋጭ መፍትሄ ለመፈለግ ከመነሳት ይልቅ ጉዳዩን ሲያባብስ እና ቤንዚን ስያርከፈክፍ ማየት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕለት ከዕለት የሚመለከተው ድራማ ሆኗል። ለእዚህም ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ለእዚህ ፅሁፍ ግን ሁለት ምሳሌዎችን እንጥቀስ -
- በዩንቨርስቲዎች ውስጥ ወጣቶች ‘አንተ የእገሌ ነህ አንተ የእንቶኔ ነህ’ ተባብለው ፀብ ሲነሳ ጉዳዩ የመጪው ትውልድ እና የአሁኑ ትውልድ አደገኛ አቅጣጫ ነው ብሎ የችግሩን ስር ለመፍታት ከመጣር እና የጉዳዩን አስከፊነት በመገናኛ ብዙሃን ከመግለፅ እና ከማስተማር ይልቅ ፖሊስ ይልቁን ከአንድኛው ወገን ቆሞ ሌላውን ሲያስር እና ሲቀጣ መመልከት ዘግናኝ ተግባር ነው።
- ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት የእርሻ ቦታ ”የእገሌ ዘር ነህ” ተብሎ በክልል መስተዳድሮች ጭምር ሲባረር ለጉዳዩ እንደ መንግስትነት ለመዳኘት ሳይሆን የሚሞከረው እንደ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ አባባል ”ቀድመው ባልተወለዱበት ሀገር መስፈር የለባቸውም” እንደ አቶ አለምነህ የብአዴን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደግሞ ”የትዕቢት ልጋግ” ነው የሚሉ መልሶችን መስማት እራስ ያማል። መሪዎቻችን እንዲህ እያሉ ከጉርዳፈርዳ እስከ አሶሳ፣ ከአሶሳ እስከ ሐረር፣ ከሐረር እስከ ጅጅጋ፣ ከጅጅጋ እስከ ቦረና ጉጂ፣ ድረስ በብዙ አስር ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በኢህአዲግ/ወያኔ የጎሳ ፖለቲካ ተሰደዱ፣ ተገደሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን መንግስት ጉዳዩን እንደ ትልቅ ችግር ሳይሆን እንደ አንድ የማስተዳደርያ ዘዴ እንደቆጠረው በ እርግጠኝነት መረዳት ይቻላል።
በያዝነው ሳምንት በሃያ ሚልዮን ብር ወጪ የሚመረቀው የመርዝ ብልቃጥ
የእርስ በርስ ግጭቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገሩ የሚጥረው ኢህአዲግ/ ወያኔ ለእርስ በርስ ጦርነቶች እየመረጠ ሃውልት ሲሰራ ከርሞ በእዚህ ሳምንት ደግሞ ለየት ያለ የጥፋት ድግስ የሚሆን ከመቶ አመታት በፊት ለመፈፀሙ ምንም አይነት የታሪክ ማስረጃ የሌለው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በአርሲ ዞን በሂቶሳ ወረዳ ተፈፅሟል ያለውን የታሪክ ምሁራን ያላረጋገጡትን የፈጠራ ታሪክ ከሃያ ሚልዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያሰራውን ”አኖሌ ሐውልት” እና ሙዝዬም በእዚህ በያዝነው ሳምንት እንደሚመረቅ ኢቲቪ ዛሬ መጋቢት 22/2006 ዓም የዜና እወጃው ላይ አስታወቀ። የፈጠራው ታሪክ ከመቶ ዓመታት በፊት የአፄ ምኒልክ ሰራዊት የኦሮሞ ሴቶችን ጡት ቆርጦ ነበር እና ማስታወሻነቱ ለተቆረጡት ጡት እና እጅ ይሁን” ይላል የሃውልቱ የመሰራት ምክንያትን ኦህዴድ /ኢህአዲግ/ወያኔ ሲናገር። አሳዛኝ የደረስንበት የዝቅጠት ዘመን። በየትኛውም ሀገር ውስጥ በቀደሙ መሪዎች ያውም ከመቶ አመታት በላይ ለሆነው ታሪክ ቀርቶ የቅርቦቹም ቢሆን ለተሰሩ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ለመጪው ትውልድ የሚያቆይ የእልቂት ድግስ ከፋች ሃውልት አይሰራም። የሚጠጣ ውሃ፣ የምበላው ምግብ ለሌለው ሕዝብከ 20 ሚልዮን ብር በላይ አውጥቶ መበተን ምን የሚሉት ፈልጥ ነው?
አንድ መንግስት ሕዝብ ከህዝብ ጋር አብሮ የሚኖርበትን ዘዴ ሲቀይስ ልዩነትን እያጎላ ሳይሆን አንድነትን እያሳየ እና እያጎላ ሕዝብ በፍቅር እና በስምምነት እንዲኖር ይጥራል እንጂ እንዴት ከአሁኑ ትውልድ አልፎ ለመጪው ትውልድ ቂም ለማውረስ ተግቶ ይሰራል? ይህ ተግባር ማንን ይጠቅማል? ለመሆኑ ያለፉ ነገስታት በወቅቱ በነበረው የቅጣት መንገዳቸው ሁሉ የቀጡትን የቅጣት አይነት እየዘረዘርን ሃውልት ብንሰራ የቱን ከየቱ እንመርጣለን?
የሃውልቱ ምርቃት እንደ ትልቅ የሀገር ልማት ዛሬ ኢቲቪ ቀድሞ ዛሬ ይናገረው እንጂ ወቅቱ የሩዋንዳው እልቂት የተጀመረበት 20ኛ አመት ጋር ገጥሟል። በሚያዝያ 7/1994 ዓም እስከ ሐምሌ/1994 ዓም እ ኤ አቆጣጠር የቆየው በቱትሲዎች እና በሁቶዎች መካከል የተደረገው እልቂት ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ሕዝብ ሕይወት ቀጥፏል። የሩዋንዳው እልቂት በአንድ ሌሊት ድንገት የደረሰ ጉዳይ አይደለም። በሂደት አልፎ አልፎ በተነሱ ቁርሾዎች ጥርቅም ሳብያ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። የዛሬ የባለ ሃያ ሚልዮን ሃውልት ገንቢዎችም ሆኑ አስገንቢዎች መዘንጋት የሌለባቸው በሰሩት ሥራ ሁሉ የሚጠየቁበት ቀን እንደሚመጣ መጠራጠር አይገባም። የመርዝ ብልቃጡም ይሰበራል የፍርድ ቀኑም ይቆረጣል።
(ምንጭ: ጌታቸው በቀለ ጉዳያችን)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar