fredag 7. mars 2014

ኢህአዴግ – ሌባ ወይስ አገር አስተዳዳሪ?



eprdf t or a
ከላይ የጠየቅነው ጥያቄ ዛሬ የተነሳ አዲስ ነገር አይደለም። ኢህአዴግ መሰረቱን ዝርፊያ ላይ ያደረገ አገር አስተዳዳሪ መሆኑ ግብሩ ራሱ ምስክር ነውና “ሌባ አገር አስተዳዳሪ” ስለመሆኑ ማስተባበያ ሊያቀርብም አይቻለውም፤ አያስፈልገውም። ሌብነቱ አገርንና ህዝብን ወደ ገደል እየሰደደ መሆኑ ግን ሁሌም የሚያስጨንቅ ነውና ዛሬ እንደ አዲስ አነሳነው እንጂ!!
ኢህአዴግ ግዙፍ፣ ሃብቱ በዶላር ካልሆነ በብር የማይቆጠር፣ በህገወጥ ንግድ ሰላማዊ ነጋዴዎችን የሚውጥ፣ ለብቻው መግቢያና መውጪያ የተዘጋጀለት፣ የተለየ ጨረታና የነጻ ቀረጥ እድል የሚበጅለት፣ በየትኛውም ተቋም እንደፈለገ መጋለብ የሚችል ልጓም አልባ የሆነ፣ በፈለገው ቦታና ማህበረሰብ ጥቅም ላይ እንዳሻው ከበሮ እየደለቀ የሚጨፍር፣ ጡሩምባ ይዞ የሚያንጠራባ፣ የፈለገውን ማስወገድ፣ ማሳገድ፣ ማስከፈት፣ ማዘጋት የሚችል፣ ድንበርና ኬላ የማይዘው የንግድ ተቋም አለው። እወክላቸዋለሁ በሚላቸው የአንድ ክልል ሕዝብ ስም ባቋቋመው ሻርክ ኦዲት በማያውቀው የ”ንግድ” ተቋም አማካይነት አገሪቷን እየዘረፈና እየዋጠ ነው።
አገሪቱ አምጣ የምታገኘውን የውጪ ምንዛሬ በበላይነት ሲፈልግ ከራሱ ባንክ፣ ሲያሻው የራሱ ሰዎች በሚያዙበት የህዝብ ባንኮች በተራ ትዕዛዝ ያግበሰብሳል። በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ እጅና እግሩን ነክሮ እንዳሻው ያንቦጫርቃል። የሚቀናቀኑ ብቅ ሲሉ እየበለተ ይሰቅላቸዋል። ሲያሻው ፋይል አስከፍቶ በ”አጎብዳጅ ባንዳ” ዳኞች ያስፈርድባቸዋል። “ጸረ ልማት” ብሎ የፍየል ወጠጤ ያዘፍንባቸዋል።
እንቶኔን ያየ … በሚል አገር ወዳዶች ሸሽተው አለቁ። ምሁሩ አገሩን ከዳ። ነጋዴው ኮበለለ። ወጣቱ በኑሮ ጠኔ መጨረሻው በማይታወቅ ስደት የባህር ላይ ሞትን መረጠ። የቻሉ አረብ ምድር ገብተው በግፍ አለንጋ ተጠበሱ። ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ የበረታባቸው ራሳቸውን ማጥፋት ጀመሩ። ይህ ሁሉ የማያስደነግጣቸው ህወሃትና ጭፍሮቹ በጥጋብ ያገሳሉ።
ተቀናቃኞቹን በሰበብ ለማላመጥ የተቋቋመው የፌደራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በቅርቡ በሰጠው ማረጋገጫ ያለ ህጋዊ ቀረጥ ከሚነግዱ ድርጅቶች መካከል ይኸው የህወሃት ድርጅት ግንባር ቀደም ነው። ነገር ግን ጠያቂ የለውም። ለምን ቢባል ባለቤቱ ራሱ አገር መሪ ነውና። ሌባ አገር አስተዳዳሪ ነውና!!
“አስገራሚውና አነጋጋሪው ጉዳይ ህወሃት መቼ ነው ዘርፎ የሚጠግበው?” የሚለው ነው። አንድ ነጻ አውጪ ድርጅት አገር መምራቱ በራሱ ይገርማል፤ ምን አልባትም በዓለም ላይ በነጻ አውጪ የምትገዛ ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ትሆናለች ። በዚህም ላይ ይህ “ነጻ አውጪ” ከፍተኛ አመራሮቹ እንደሚሉት ከበረሃ ጀምሮ ዘርፎ ዘርፎ አለመጥገቡ ያስደንቃል። ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ግን በየቀኑ የጠላቶቹን ቁጥር በሺህዎች እያባዘ ነገ ምን ሊገጥመው እንደሚችል ያለመገመቱ ነው።
እዚህ ላይ አጠንክረን የምንለው ይኖረናል። ህወሃት አንዱን ከሌላው በማጋጨት መሰረት ላይ በተከለው ፖለቲካ የትግራይ ህዝብ የሌላውን ብሔረሰብ ህዝብ ሙሉ በሙሉ እንዲጠረጥርና ራሱን እንዲከላከል እየሰራ መሆኑን እናውቃለን። የማያውቁና መረጃ የሌላቸው ከግምት በላይ ይረዱታል። ይህ ሰይጣናዊ አካሄድ ዋጋው አስቀድመን እንዳልነው “ደም” ነውና ከወዲሁ ማርገቢያ እንዲበጅለት እናሳስባለን።
በቁጥር እየከፋፈሉ በምስጢር ከየአይነቱ በማስታጠቅ የትግራይ ህዝብን ከሌላው ህብረተሰብ ጋር ለማጋደል በምርጫ 97 ወቅት ሟቹ አቶ መለስ የሰጡትን ትዕዛዝ አጠንክሮ መያዝ አሁንም መዘዙ የከፋ ነውና ህዋሃት ከዚህ ተግባሩ እንዲታቀብ እንመክራለን። በወቅቱ “ራስህን ተከላከል፣ ሊያጠፉህ ነው” በሚል በመታጠቅ በየቀበሌው ለመተላለቅ መመሪያ የተጠበቀበት ደረጃ ተደርሶ እንደነበር ለምናውቅ ድርጊቱን ስናስበው ይቀፈናል። ያመናል። ያስበረግገናል። ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ጠባሳው ምን ያህል በከፋ ነበር?
የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ እንደ ማንኛውም የተረገጡ ዜጎች ሁሉ የስርዓት ለውጥ ያስፈልገዋልና ሌላው ህብረተሰብ ከጭፍን ጥላቻ ራሱን እንዲያርቅ እንመክራለን። የትግራይ ልሂቃንም በገለልተኛ ሚዛን በራሳቸው ላይ እንዲሆን የማይፈቅዱት በሌሎች ላይ እየተደረገ መሆኑንን በመቃወም በህዝብ መካከል የተረጨውን መርዝ በማምከን ተግባር ላይ ሊሰማሩ እንደሚገባ ለመጠቆም እንወዳለን። ዙሪያችንን የከበቡን ጠላቶች ይበቁናልና!!
ኢህአዴግ እንደ ገዢ ያለው አቅም ተቦርቡሯል። ሟርት ነው ካልተባለ የኑሮ ብሶት፣ ሌብነትና በሌላው ህዝብ ላይ የሚፈጽመው የግፍ ክምር ሊንደው ተቃርቧል። የሚመካበት የጦር ሃይልም ቢሆን ወገን አለውና አንድ ቦታ ከተፈረከሰ አደጋው የአገር ነው። በቡድን አደራጅቶ መሳሪያ በማደል በጎጥ ወኔ የህዝብን ቁጣና ምሬት መቋቋም የሚታሰብ አይደለምና ህወሃት በመፈክር አታሎ በጨረሳቸው ታጋዮች ደም ላይ የሚደንሰውን ከልክ ያለፈ የጥጋብ ጭፈራ ይግታው። በነጻ አውጪ ስም አገር እየመሩ ዝርፊያ ተራ የማፊያ ተግባር እንጂ አገር እምራለሁ ከሚል ወገን የሚጠበቅ አይደለምና ያደባባይ ዝርፊያ ይቁም!! ኢህአዴግ ሌባ ወይስ አገር አስተዳዳሪ በማለት የሚጠይቁ ሁሉ እውነት አላቸውና ልብ ያለው ልብ ይበል።
በግብር የምናየው ኢህአዴግ ከተዘፈቀበት ችግር ራሱን ከማጽዳት፣ ህዝብ የሚበጀውን እንዲመርጥ መንገድ ከማመቻቸትና አገሪቱን ወደ መልካም ጎዳና ከማሸጋገር ይልቅ፣ ህዝብን በጅምላ “ለሃጫም” እያለ መስደብ የሚያስደስተው ነው። ህዝብን “ጠባብ፣ አሸባሪ፣ ጸረ ልማት፣ …” በማለት መፈረጅ የድል ያህል የሚያስፈነድቀው ነው። ራሱ ስራ ፈት ያደረገውን ትውልድ “ቦዘኔ” ሲልና ሲሳደብ የስኬት ገድል ያስመዘገበ ያህል ይመስለዋል። ከሁሉም በላይ የህወሃት የእጅ ስራ ውጤት የሆኑ አሻንጉሊት ካድሬዎች እንደ ጌቶቻቸው “ለሃጫም” እያሉ ህዝብን ሲሰድቡ ሽልማት ለመስጠት ይሽቀዳደማል። ህዝብ ሲያኮርፍና ሲበሳጭ ይደሰታል። አገሪቱን ባህር አልባ አድርጎ ስለቀረቀረባት ኩራት ደረቱን ይነፋል። በማያገባው ጦርነት ምስኪን ወገኖችን ማሽጨፍጨፉ ልዩ ገድል ሆኖ ይታየዋል። ድንግል መሬት በሳንቲም ሲቸበቸበ ልማት ነው ይላል፡፡ ነዋሪዎችን ለትውልድ ከኖሩበት እያፈናቀለ መሬታቸውን ለውጪ ባለሃብቶች እየሰጠ “እስካሁን ያልሸጥነው መሬት ነው የሚያሳስበን” በማለት በሰው ደም ይቀልዳል፡፡ በዚህ ሁሉ ትዕቢቱ ላይ ንጹሃንን እያሰረ ማሰቃየቱ፣ መግረፉና መግደሉ፣ አሁን አሁን ይፋ የሆነበት የመርዝ ጣጣ ጀብድ ሆኖበታል። በልክ በልኩ የሰራቸውን አሻንጉሊት ተላላኪዎቹ ሰብስቦ በሚሰራው ድራማ መደነሱና ውሸታም አገር አስተዳዳሪ መሆኑ የኩራቱ ሁሉ ኩራቱ ነው። በዚህ ሁሉ ሲደመር ዜሮ በሚሆን ትምክህት ውስጥ ሆኖ አገር መምራቱ በእጅጉ ያሳስበናል፣ ያስጨንቀናል፣ ወደፊት የሚመጣውን ስናስበው እንደ ዜጋ ያስበረግገናል። ለዚህ ነው “ኢህአዴግ ሌባ – ወይስ አገር መሪ” ስንል የጠየቅነው። መልሱን የሚሰጥ ሁሉ እንዳመላለሱ ትግሉን ሊያካሂድ ይገባዋል እንላለን፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar