søndag 9. mars 2014

ወያኔ በግንቦት 7 ስም ሠላማዊ ዜጎችን ማሰቃየቱን ባስቸኳይ ማቆም አለበት

March 8, 2014

Ginbot 7 weekly editorialባለፉት አራትና አምስት አመታት በግልጽ እንዳየነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እኩልነቱን፤ መብቱንና ነጻነቱን ለማስከበር የሚያደርገዉ ትግል ጫና በፈጠረበት ቁጥር ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የራሱን ህገመንግስት የሚደፈጥጡ ህጎች አርቅቆ አያጸደቀ ሠላማዊ ዜጎችን አስሯል፤ ገድሏል ከአገር እንዲሰደዱም አድርጓል። ለምሳሌ በ2003 ዓም የኢትዮጵያ ፓርላማ ከቤተመንግሰት የተላለፈለትን ትዕዛዝ አክብሮ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነፃነት መከበር የሚታገለዉን የግንቦት 7 ንቅናቄ ሽብርተኛ አድርጎ ፈርጇል። ይህ ፈር የለቀቀ ፍረጃ ደግሞ ወያኔ የሱን ዘረኛ ስርዐት የሚቃወሙ ግለሰቦችን፤ ሀሳባቸዉን በነፃነት የሚገልጹ ዜጎችን፤ ጋዜጠኞችን፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና ከወያኔ ጋር አናብርም ያሉ ወጣት ኢትዮጵያዉያንን “ግንቦት ሰባቶች” ናችሁ እያለ በጅምላ እያሰረ እንዲያሰቃይ ህጋዊ ሽፋን ሰጥቶታል። ለምሳሌ ከፍትህና ከነጻነት ጥማት ዉጭ ከግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር ምንም አይነት ግኑኝነት የሌለዉን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዉን አንዱአለም አራጌን፤ ታዋቂዉን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና መምህርት ርኢዮት አለሙን የግንቦት 7 አባላት ናቸዉ የሚል ሰንካላና መሠረተ ቢስ ክስ መስርቶ ለረጂም ዘመን እስራት ዳርጓቸዋል።
ወያኔ እንደ ዛሬዉ ከተማ ዉስጥ ሆኖ ሥልጣን ሳይቆጣጠር ገና ጫካ ዉስጥ እያለ ጥርሱን ከነከሰባቸዉና ከተቻለ አጠፋቸዋለሁ ካለዚያም አሽመደምዳቸዋለሁ ብሎ አስራ ሰባት አመት ሙሉ ከተዘጋጀላቸዉ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ የአማራ ብሄረሰብ ነዉ። በለስ ቀንቶት ሥልጣን ከጨበጠ ማግስት ጀምሮም በወሎና በጎንደር በኩል ከትግራይ ጋር የሚያዋሰኑ ሰፊ የሆነ ለም መሬቱን ጠቅልሎ በመውሰድ ዘረኛ ሥርዓቱን ዕድሜ ሊያራዝሙልኛል ይችላሉ ብሎ የሚተማመንባቸውን የቀድሞ የትግል አጋሮቹንና ካድሬዎቹን አስፍሮበታል:: ይህ በደልና ግፍ አልበቃ ብሎትም ቀደምቶቹ የኢትዮጵያ ገዥዎች ለፈጸሙት ግፍና የአስተዳደር በደሎች ሁሉ አማራዉን በጅምላ ተጠያቂ የሚያደርግ ፕሮፖጋንዳ እነሆ እስከዛሬ በመርጨት ለዘመናት በሠላም ከኖረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በጠላትነት እንዲተያይ አድርጎታል:: በወያኔ አጋፋሪነት በበደኖ ፡በአርሲ በአረካና ሌሎች አካባቢዎች አማራው ላይ በግፍ የተፈጸመው ጭፍጨፋና ከ2004 እስከ 2005 ዓም አማራዉን ከጉራፈርዳና ከቤንሻንጉል ለማፈናቀል የተወሰደው እርምጃ የዚህ የወያኔ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ውጤት መሆኑን የሚስት የለም::
ሟቹ መለስ ዜናዊና በህይወት የሚገኙ ቀንደኛ የወያኔ መሪዎች የተጠናወታቸው የአማራ ጥላቻ በጸረ ፋሽስት ዘመቻ ወቅት ባንዳ ከነበሩ አባቶቻቸዉና አያቶቻቸዉ የተወረሰ ፋሽስት ጣሊያን ለደረሰባት ሽንፈት በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍለን እርስ በርሳችን እንድንጠፋፋ ተክላብን የሄደቺው ተንኮል አካል ነው ::
የዚህ የጥፋት አጀንዳ አስፈጻሚ የሆነው ወያኔ የጀመረውን አገር የማፍረስና ህዝብ የመከፋፈል አጀንዳ ለማሳካት በየክልሉ የተኮለኮሉ ምስሌኔዎች እንወክለዋለን በሚሉት ህዝብና ክልል ላይ እየፈጸሙት ያለው በደልና ሰቆቃ አዲስ ምዕራፍ በያዘበት በአሁኑ ወቅት እራሳቸዏን ለባርነት አዋርደው ህዝባቸውን በማዋረድ ላይ የሚገኙት የብአዴኑ አለምነህ መኮንንን የመሳሰሉ ሆድ አደሮች ውርደት በቃን ዘረኝነት በቃን ብለው በተነሱ ዜጎች ላይ እየወሰዱ ያለው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ እጅግ አሳሳቢ ሆኖአል::
ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከሰሞኑ በደረሰው መረጃ ወያኔ ከአማራው ቀምቶ በትግራይ ክልል ባስገባቸው ወረዳዎች ላይ የሚኖሩ ንጹሃን ዜጎች ለምን በወያኔ የግፍ አገዛዝ ትማረራላችሁ እየተባሉ በወያኔ ታማኝ ሚሊሻዎች እስር እንግልትና ድብደባ እየተፈጸመባቸው መሆኑን አረጋግጦአል:: በዚህ በአዲስ መልክ በተጀመረዉ የወያኔ የጥቃት ዘመቻ መሳሪያ ያነገቡ የህወሃት ሚሊሻዎች ከክልላቸዉ ዉጭ ወደ ተለያዩ የአማራ ከተማዎችና ወረዳዎች ሰርገዉ እየገቡ የእነሱን ቋንቋ የማይናገረዉን ሁሉ የግንቦት 7 ተላላኪዎች ናችሁ በሚል እያሰሩ በመደብደብ ላይ ናቸዉ።
ይህ በመሆኑ ዛሬ አትዮጵያን ከሱዳንና ትግራይን ከጎንደር ጋር በሚያዋስኑ የአማራ ክልል ዉስጥ የሚገኙ ገበሬዎች እጃቸዉ እርፍ ከሚጨብጥበት ግዜ ይልቅ በወያኔ ሰንሰለት የሚታሽበት ግዜ ይበልጣል፤ የመንግስት ሰራተኛዉና የከተማ ነዋሪዉም ቢሆን አብዛኛዉን ግዜ የሚያጠፋዉ ከወያኔ ካድሬዎች ጋር ግምገማ በመቀመጥ ሲሆን ተማሪዉና ወጣቱ ህብረተሰብ ደግሞ “መጡ አልመጡም” እያለ ሌሊቱን የሚያሳልፈዉ በየጫካዉ እየተሸሸገ ነዉ።
የዚህ አይነት አስከፊ ግፍና መከራ በአፋር ፡ በጋምቤላ በኦጋዴንና በኦሮሚያ በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ ሲፈጸም ቆይቶአል:: ወያኔ እራሱ አርቅቆ ባጸደቀውና በሐምሌ ወር 1987 ዓም በስራ ላይ በዋለዉ የወያኔ ህገ መንግስት ኢትዮጵያ በዘጠኝ የፌዴራል ክልሎች መከፈሏንና እያንዳንዱ ክልል እራሱን በእራሱ የማስተዳደር መብቱ የተረጋገጠ እንደሆነ ይደነግጋል። በዚህ ህገ መንግስት መሠረት እያንዳንዱ ክልል የራሱ ቋንቋ፤ የአስተዳደር ማዕከልና እንዲሁም የክልሉን ሠላምና ጸጥታ የሚያስከብር የፖሊስ ኃይል ይኖረዋል ይላል። ታድያ ለምንድነዉ እያንዳንዱ ክልል የራሱ ፖሊስ ኃይል እያለዉ ከትግርኛ ቋንቋ ዉጭ ሌላ ቋንቋ የማይናገሩ የህወሃት ታማኝ ሚሊሻዎች አማራ ክልል ዉስጥ እየገቡ አማራዉን የሚያሰቃዩት?
መልሱ ቀላል ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ህዝባዊ አምቢተኝነቱ እያየለ በመጣና የነጻነት ኃይሎች ጡንቻ በፈረጠመ ቁጥር ወያኔ አንገቷ ላይ ቃጭል እንደታሰረባት በቅሎ ይደነብራል። የደነበረ ደግሞ መራገጡ አይቀርምና መሳሪያ ያነገቡ ኃይሎችን እንቅስቃሴ እገታለሁ በሚል ከንቱ ጥረት ደንባራዉ ወያኔ የፈሪ ብትሩን በድንበር አካባቢ በሚኖሩ የአማራ ክልል አርሶ አደሮች፤ ወጣቶችና ሠራተኞች ላይ ማሳረፍ ጀምሯል።
ወያኔ እንደ ግንቦት ሰባት የኮነነዉና የህዝብና የአገር ጠላት አድርጎ የሳለዉ ድርጅት የለም፤ የወያኔ የዜና ማሰራጫዎችም ይህንን የአገዛዙን አቋም በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ህዝብ አሰምተዋል።የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ማን ለመብቱና ለነጻነቱ እንደቆመና ማን መብቱና ነጻነቱ ላይ እንደቆመበት ለይቶ የሚያዉቅ ህዝብ ነዉ። ስለዚህም ግንቦት ሰባት ወያኔዎች አላፊዉንና አግዳሚዉን “ግንቦት ሰባት” ነህ እያሉ ከሚያሰቃዩ፤ ህዝብንና ግንቦት ሰባትን ያስተሳሰረዉ ነጻነት፤ ፍትህና ዲሞክራሲ ነዉና የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ ቢመልሱ ለእነሱም፤ ለእኛም ለአገርም ይበጃል የሚል የጸና እምነት አለዉ። ወያኔ በኢህአዴግ ስም ያስጠጋቸዉን ምሰለኔዎች ጨምሮ ከራሱ ዉጭ ሌላ ማንንም አያምንም፤ ስለዚህም ነዉ የአገሪቱን የመከላከያ፤ የደህንነትና የፖሊስ ተቋሞች በራሱ ሰዎች ቁጥጥር ስር ያደረገዉ። ዛሬ በግልጽ እንደምንመለከተዉ ወያኔ በጉልበት ለያዘዉ ስልጣን ያሰገኛል ብሎ በሚጠረጥረዉ ቦታ ሁሉ የራሱን ልዩ ሚሊሺያ እየላከ የኢትዮጵያን ህዝብ መኖሪያ ቤቱ ድረስ አየሄደ እያጠቃ ነዉ። ግንቦት ሰባት ወያኔና የፈጠረዉ ዘረኛ ስርዐቱ የቆሙት በፍጹም ማንሰራራት የማይችሉበትት የመጨረሻ መቀበሪያ ጉድጓዳቸዉ ጫፍ ላይ ነዉ የሚል ጽኑ እምነት አለዉ። ሆኖም ጉድጓድ ጫፍ ላይ የቆመ ጠላት በራሱ ተወርዉሮ ጉድጓዱ ዉስጥ አይገባምና ይህንን የተዳከመ ጠላት እየተፈራገጠ ጉዳት ከማብዛቱ በፊት ለመደምሰስ ክንዳችንን አጠናክረን በህብረት እንደ አንድ ሰዉ እንነሳ ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar