tirsdag 20. august 2013

ነዋሪዎች በውሃ እጦት ተሰቃየን አሉ

water line
ነዋሪዎች በውሃ እጦት ተሰቃየን አሉ
በሳምንት አንድ ቀን ውሃ ማግኘት ብርቅ የሆነባቸው ሰፈሮች፣ በውሃ እጦት አካባቢያቸውን በመጥፎ ጠረን የሚበክሉ የኮንዶሚኒየም መኖሪያዎች፣ ለተደጋጋሚ አቤቱታ ምላሽ ሳያገኙ በርካታ ወራት እየተቆጠሩ የሚማረሩ ነዋሪዎች የአዲስ አበባ የዘመኑ ገጽታ ሆነዋል፡፡
በቂ ውሃ ስለሌለ በራሽን ለማከፋፈል እየሞከረ መሆኑን የሚልፀው የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ፤ የኤሌክትሪክ መቆራረጥና የአንዳንድ ሰራተኞች እንዝህላልነት፣ ለመንገድ ግንባታ የሚቆፈሩ ቧንቧዎች እንዲሁም በከንቱ የሚባክን ውሃ መብዛቱ የውሃ እጥረትን እንዳባባሱ ይናገራል፡፡
የአገሪቱ እንዲሁም የአህጉሪቱ መዲና በሆነችው ከተማ፣ ለዚያውም በሰለጠነ ዘመን በርካታ ነዋሪዎች የዝናብ ውሃን ደቅኖ ለማጠራቀም ሲሯሯጡና በጀሪካን ተሸክመው ውሃ ሲያመላልሱና የፎቅ ደረጃዎችን ለመውጣት ሲውተረተሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡
በገርጂ፣ አየር ጤና፣ ጀሞ፣ እንቁላል ፋብሪካ፣ አዲሱ ገበያ፣ እንዲሁም በየአቅጣጫው የተገነቡ ኮንዶሚኒየሞችን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ሰፈሮች፣ በውሃ እጥረት የተቸገሩ ነዋሪዎች “አወይ ስልጣኔ” በማለት መላ እንደጠፋባቸው ይገልፃሉ፡፡
የፉሪ አካባቢ ነዋሪ ወ/ሮ አልማዝ ሞገስ፣ ቀድሞም ቢሆን በሁለት በሶስት ቀን ነበር ውሃ የምናገኘው ይላሉ፡፡ አሁን ግን ብሶበታል፣ ይሄውና በሰፈሩ ውሃ ካገኘን ከሳምንት በላይ ሆኖናል የሚሉት ወ/ሮ አልማዝ፤ ውሃ የምናገኘው ጀሪካን ተሸክመን ሰፈር አቆራርጠን ነው ብለዋል፡፡ ብዙ ጊዜ አቤቱታ አቅርበን ደከመን፤ ምንም መልስ አላገኘንም ብለዋል – ወ/ሮ አልማዝ፡፡
በጀሞ ቁጥር 1 መኖር ከጀመረች ሁለት አመት የሆናት ሰናይት ፈቃደ በበኩሏ፣ የውሃ ችግር የጠናብኝ ዛሬና ትላንት አይደለም፣ በጣም ቆይቷል ትላለች፡፡ ድሮ ድሮ ሌሊት ላይ ብቅ ይል የነበረው ውሃ፤ ዛሬ ሽታውም የለም የምትለው ሰናይት፣ የኮንዶሚኒየም ቤት ያለ ውሃ የስቃይ ቤት ማለት ነው ብላለች፡፡ የመጀመሪያ ፎቅ ነዋሪዎች የዝናብ ውሃ ደቅነው ለማጠራቀም ይሞክራሉ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ፎቅ ግን አይሞከርም፡፡ ቧንቧ በየቤታችን አለ፤ ውሃ የምናመጣው ግን እንደ ጥንቱ የገጠር አኗኗር ነው የምትለው ሰናይት፤ ለውሃና ፍሳሽ አመልክተናል፡፡ ውሃውን ወደ ላይ ለመሳብ የፓምፕ ሃይል ስለሚያስፈልግ ነው ይሉናል፤ ይህንን እንደ በቂ ምላሽ ይቆጥሩታል በማለት ግራ መጋባቷን ትገልፃለች፡፡
ጀሞ ብቻ አይደለም፡፡ የጐሮ ነዋሪ ናርዶስ አስማረ አንድ ቀን ውሃ ከመጣ ለሁለትና ለሶስት ቀን ይጠፋል፤ ቅዳሜና እሁድ ውሃ ያገኘንበት ጊዜ የለም ትላለች፡፡ በየሳምንቱ አቤቱታ ስናቀርብ የምናገኘው ምላሽ ሁልጊዜ ተመሳሳይ ነው የምትለው ናርዶስ፤ አሁን ይስተካከላል ይሉናል፤ ግን ተስተካክሎ አያውቅም ትላለች፡፡
ውሃ የሚጠፋበትን ቀን ዘርዝሮ ከመናገር ይልቅ ውሃ የሚመጣበትን ቀን መናገር ይቀላል የሚለው የአዲሱ ገበያ ነዋሪ ልዩነህ አያሌው፤ ውሃ ይግባልን ብንል ይሻላል፤ በሳምንት አንዴ ውሃ ከመጣ ፌሽታ ነው፤ ብርቅ ይሆንብናል ሲል ይናገራል፡፡
አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ወ/ሮ እፀገነት ተስፋ ምላሽ ሲሰጡ፤ በአዲስ አበባ የውሃ ችግር አለ በማለት ነው የሚጀምሩት፡፡ ዋናው ምክንያት የውሃ እጥረት ነው የሚሉት ወ/ሮ እፀገነት፤ ከነእጥረቱም ቢሆን ውሃውን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ደግሞ የተለያዩ መሰናክሎች እንደሚገጥሙ ገልፀዋል፡፡ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ከፍታ ቦታ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በፓምፕ ውሃ ማድረስ አንችልም ይላሉ፡፡
ሌላው ችግር በራሳችን ሰራተኞች የሚፈጠር ነው የሚሉት ሃላፊዋ፣ የውሃ ቧንቧ ተበላሽቷል ተብሎ ሲነገራቸው አንዳንድ ሰራተኞች ብልሽቱን እንደመጠገን ውሃውን ዘግተውት ይመጣሉ ብለዋል፡፡ በመንገድ ስራና የተለያዩ ግንባታዎች የውሃ ቧንቧ እንደሚሰበር ሲያስረዱ፣ ለምሳሌ በሃያ ሁለት አካባቢ፣ በመንገድ ግንባታ ምክንያት ዋናው የውሃ ቧንቧ በመቋረጡ አሁን በተዘረጋ ጊዜያዊ ቧንቧ የምናቀርበው ውሃ በአስር እጥፍ ያነሰ ነው ብለዋል፡፡ በዚያ ላይ ለከተማዋ ከሚቀርበው ጠቅላላ የውሃ መጠን ውስጥ ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጠው በከንቱ ይባክናል ብለዋል ሃላፊዋ፡፡ (ምንጭ፤ አዲስ አድማስ)
የኢህአዴግ አባላት ክርስቶፎር ስሚዝ በሚያረቁት ህግ ላይ የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰብ ጀመሩ
ከደጋፊዎቹ የመረጃ ለውውጥ ለመረዳት እንደተቻለው ኮንግረስ ማን ክሪስ ስሚዝ በቅርቡ በኢትዮጵያ ዙሪያ የግንቦት 7 መሪ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋን፣ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሀላፊ ሚ/ር ያማማቶ እና ሌሎችንም ታዋቂ ሰዎች በመጋበዝ በኢትዮጵያ ዙሪያ የተለያዩ ሀሳቦችን ማሰባሰባቸው ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችን እንድታከብርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን እንድትገነባ፣ ኮንግረሱ የህግ ረቂቅ እንደሚያዘጋጅ ሚ/ር ስሚዝ ገልጸዋል።chris smith
የህጉን መረቀቅ የተቃወሙት የኢህአዴግ ደጋፊዎች  ለሚ/ር ስሚዝ ደብዳቤ መላክ ጀምረዋል። በደብዳቤው ላይ ሚ/ር ስሚዝ በኢትዮጵያ መንግስት አሻባሪ የተባሉትን ሰዎች ለውውይት መጋበዛቸውን አውግዘዋል። በኢትዮጵያ ላይ የሚረቀቀው ህግ የአሜሪካንና የኢትዮጵያን ግንኙነት የሚያበላሽ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ በውጭ ተጽኖ አቋሟን የማትቀይር መሆኗንና ሚ/ር ስሚዝም ኢትዮጵያን ለመደገፍ የሚያስችል የህግ ረቂቅ እንዲያዘጋጁ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች እየፈረሙ በሚልኩት ደብዳቤ ላይ ተመልክቷል።
አስቸኳይ በሚል ርእስ ለኢህአዴግ አባላት በተላከው የኢሜል መልዕክት ላይ ህጉ የሚረቀቅ ከሆነ በኢትዮጵያ ላይ ከባድ ተጽኖ እንደሚያስከትል ተመልክቷል።
ህዳሴ ካውንስል የሚባለው የኢህአዴግ አባላትንና ደጋፊዎችን የያዘው ቡድን የድጋፍ ፊርማ የማሰባሰብ ተልእኮ የተሰጠው ሲሆን፣ በአጠቃላይ እስከ 10 ሺ የሚደረሱ ፊርማዎችን አሰባስቦ የመላክ እቅድ ተይዟል።
የ1997 ዓም ምርጫን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ በተመሳሳይ መንገድ የተረቀቀው ህግ ዲኤል ኤ ፓይፐር በተባለው ተቋም ድለላ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወቃል።(ምንጭ፡- ኢሳት)
በሙስሊም ማኀበረሰብ አካላት ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃ ሶስት ፓርቲዎች አወገዙ
የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አካላት ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለው የኃይል እርምጃ አጥብቀው እንደሚቃወሙት ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ አስታወቁ።
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ እና የመላ ኦሮሞ ሕዝብ ድርጅት ነሐሴ 5 እና 6 ቀን 2005 በተናጠል ባወጡት መግለጫዎች መንግሥት አለመግባባቱን ለመፍታት እየተከተለ ያለውን የኃይል እርምጃ ተገቢ አለመሆኑን ገልፀዋል።
muslim ethiopiansጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለምልልስ ‘‘ጽንፈኞች’’ ያሏቸውን የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊም ማኀበረሰብ አካላት እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ፀረ-ሕገመንግስታዊ መሆኑን አመልክተዋል። ‘‘የሃይማኖት መንግስት እንመሰርታለን፣ የሸሪዓ ሥርዓት እናሰፍናለን’’ የሚል አቋም እንደሚያራምዱ የጠቀሱት ጠ/ሚኒስትሩ መንግስት ሃይማኖታዊ ተልዕኮ ያላቸው መስሏቸው ከፅንፈኞች ጋር የሚተባበሩ ተከታዮችን በጅምላ ላለመጉዳት በትግስት ሁኔታውን ሲከታተልና የማሳመን ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ጽንፈኞችን ከሌሎች የእምነቱ ተከታዮች ለመለየት የተደረገው ጥረት የተሳካ እንደነበርና መንግስት ሰሞኑን የወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ከጽንፈኞች ጋር ተቀናጅተው የአገሪቷን ሠላም ለማወክ ይንቀሳቀሳሉ ያሏቸውን የተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል። (ምንጭ፡- ሰንደቅ)
የዋጋ ግሽበት በድጋሚ በማገርሸት ላይ ነው
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ላለፉት በርካታ ዓመታት እየፈተነ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት ለዓመታት ከነበረበት ባለሁለት አኃዝ ምጣኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ነጠላ አኃዝ ከሦስት ወራት በፊት ቢወርድም፣ በሐምሌ ወር መጨረሻ ደግሞ በድጋሚ በማሻቀቡ ስምንት በመቶ ደርሷል፡፡
መንግሥት በወሰደው ከፍተኛ የገንዘብ አቅርቦት ቁጥጥር፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የበጀት አጠቃቀምና መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ከውጭ በማስገባት ማከፋፈል ዕርምጃዎች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ፈተና የሆነውን የዋጋ ግሽበት ከሁለት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ነጠላ አኃዝ ማለትም ወደ 7.6 በመቶ ማውረድ አስችሎታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የዋጋ ግሽበቱ መውረዱን አስመልክቶ መንግሥታቸው የወሰዳቸው ጥብቅ ቁጥጥሮች ውጤት ማምጣታቸውን በተደጋጋሚ በመግለጽ፣ በቀጣይም በበለጠ ቁጥጥሩን በመቀጠል የዋጋ ግሽበት ምጣኔው እንዳያንሰራራ መንግሥታቸው እንደሚሠራ መናገራቸው ይታወሳል፡፡market
የዋጋ ግሽበቱ ወደ ነጠላ አኃዝ ከወረደበት ከመጋቢት ወር ቀጥሎ ባሉት ወራት ማሽቆልቆሉን የቀጠለው እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ብቻ ነው፡፡ በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የአገሪቱ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት ምጣኔ 6.3 በመቶ የደረሰ ቢሆንም፣ በቀጣዮቹ ወራት ግን ከቁጥጥር ማምለጥ የጀመረ ይመስላል፡፡
አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ በሰኔ ወር በፍጥነት ማሻቀቡን በመቀጠል በወሩ መጨረሻ አጠቃላይ ዓመታዊ ግሽበቱ 7.4 በመቶ ሲደርስ፣ ይህም የግሽበቱን ግስጋሴ ለመግታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ውጤታማነት እምብዛም መሆኑን ያሳያል፡፡ በመሆኑም በሐምሌ ወር አጠቃላይ ዓመታዊ ግሽበቱ ግስጋሴውን በመቀጠል 8.0 በመቶ መድረሱን ማዕከላዊ የስታትስቲክስ ባለሥልጣን በየወሩ ይፋ የሚያደርገው የአገር አቀፍ የገበያ ዋጋና የዋጋ ግሽበት መረጃ ያስረዳል፡፡
ከዚህ ቀደም 45 በመቶ ደርሶ ለነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያት በምግብ ነክ ምርቶች ላይ የሚታይ የዋጋ ጭማሪ ነበር፡፡ ይህንንም አስመልክቶ በቅርቡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት መነሻ ዋነኛው በምግብ ነክ ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህንን የዋጋ ግሽበት ያመጣው የምግብ ነክ አጠቃላይ ፍላጐትና አቅርቦት አለመጣጣም መሆኑን በመግለጽ፣ መፍትሔውም የግብርና ዘርፍ ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን ጠቁመው ነበር፡፡
ማዕከላዊ የስታስቲክስ ባለሥልጣን መረጃዎችም የቀድሞዎቹ ዓመታት ከፍተኛ የግሽበት መንስዔ የምግብ ነክ ዋጋ መናር መሆኑን ያሳያሉ፡፡ አሁን እየታየ ላለው የዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያት በመሆን የተጠቀሰው ግን ምግብ ነክ ባልሆኑ ምርቶች ላይ የሚታይ የዋጋ ንረት ነው፡፡
በተለይም አልባሳትና ጫማዎች፣ የቤት ቁሳቁሶችና የማስጌጫ ዕቃዎች ላይ የታየው የዋጋ ግሽበት ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ለታየው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት ማሻቀብ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን የባለሥልጣኑ ትንተና ያስረዳል፡፡ (ምንጭ፡- ሪፖርተር)
የ6 አመቷን ህፃን የደፈሩት የ60 አመት አዛውንት በ14 አመት እስራት ተቀጡ
*ዐቃቤ ህግ ቅጣቱ አንሷል ሲል በውሳኔው ላይ ቅሬታ አለኝ ብሏል
የ6 አመቷን ህፃን አታለው ደፍረዋታል ሲል የፌዴራሉ ዐቃቤ ህግ ክስ የመሰረተባቸው የ60 አመቱ አዛውንት አቶ አምደላ ነአምሳ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ፍርድ ቤት በ14 አመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል የቅጣት ውሳኔውን አስተላለፈ። የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፍትህ ጽሕፈት ቤት ዐቃቤ ህግ ግን በቅጣት ውሳኔው ላይ ቅሬታ እንዳለው በመግለፅ ለፍርድ ቤቱ ደብዳቤ ፅፏል።
በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 7ኛ ወንጀል ችሎት ግለሰቡን ጥፋተኛ ያላቸው የዐቃቤ ህግን የክስ መዝገብ መርምሮና የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ነው። ዐቃቤ ህግ በክሱ እንዳመለከተው፤ ተከሳሽ ለአቅመ ሔዋን ካልደረሰች ልጅ ጋር የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ለመፈፀም አስበው በሐምሌ 8 ቀን 2004 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 7 ሰዓት ሲሆን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 14/15 ክልል ልዩ ቦታው ገብስ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ስሟን የማንገልጽላችሁን የ6 አመቷን ህፃን አታለውና አግባብተው ወደመኖሪያ ቤታቸው በማስገባት፤ አልጋ ላይ እንድትተኛ አድርገው የመድፈር ወንጀል ፈፅመውበታል ሲል ይከሳል።
Injusticeየጉዳዩን ግራና ቀኝ ሲመረምር የቆየው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 7ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሹ ዐቃቤ ህግ ያቀረባቸውን የሰውና የሠነድ ማስረጃዎች በአግባቡ ማስተባበል አልቻሉም ሲል ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
ፍ/ቤቱ ሐሙስ ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት፤ ተከሳሹ ጥፋተኛ በሆኑበት ወንጀል ላይ ቅጣት ያስተላለፈ ሲሆን፤ የወንጀሉን ደረጃ ከባድ በማለት የህፃኗን ዕድሜ እንደምክንያት ያቀረበው ፍርድ ቤቱ ከ20 አመት እስከ 22 አመት ሊያስቀጣ እንደሚችል ይጠቅሳል። ዐቃቤ ህግ ምንም አይነት የወንጀል ማክበጃ ያላቀረበ ሲሆን፤ ተከሳሹ በበኩላቸው የቤተሰብ አስተዳዳሪና ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆናቸውን መጥቀሳቸው የቅጣት እርከኑን ዝቅ እንዳደረገላቸው ለመረዳት ተችሏል። በዚህም የቅጣት መነሻው 22 አመት ላይ እንዲያርፍ ሆኗል።
የግራቀኙን አስተያየት ያደመጠው ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ የ60 አመት አዛውንቱን ጥፋተኛ በተባሉበት ወንጀል በ14 አመት ከ5 ወር ፅኑ እስራትና ለአምስት አመታት በሚዘልቅ ከመምረጥ መመረጥ ህዝባዊ መብታቸው እንዲታገዱ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ደስተኛ ያልሆነው የክፍለ ከተማው ፍትህ ጽ/ቤት ዐቃቤ ህግ ቅሬታውን ጠቅሶ ደብዳቤ መፃፉንና ቅጣቱ መሻሻል እንደሚገባው ማመልከቱን ለማወቅ ተችሏል።(ምንጭ፡-ሰንደቅ)
አንድነት ፓርቲ የማተሚያ ማሽን ለመግዛት ጨረታ አወጣ
በሶስት ቋንቋዎች የፓርቲው ልሳኖች ይዘጋጃሉ
አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የራሱን ማተሚያ ቤት ለመክፈት ባለፉት ሶስት ወራት በአገር ውስጥና በውጭ ባከናወነው የገቢ ማሰባሰቢያ ጥረት በቂ ገንዘብ ማግኘቱን በመግለጽ የማተሚያ ማሽን የግዢ ጨረታ አወጣ።andinet -UDJ
በፓርቲው ሲዘጋጅ የነበረው “ፍኖተ ነፃነት” ጋዜጣ በማተሚያ ቤት እጦት እንደተቋረጠ የገለፁት የፓርቲው አመራር አባል፣ ማተሚያ ማሽን ተገዝቶ ስራ ሲጀምር “ፍኖተ ነፃነት”ም ለአንባቢያን ትደርሳለች ብለዋል፡፡ ከጋዜጣው በተጨማሪ በትግርኛና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ጋዜጦችና ሌሎች ህትመቶችንም እንደሚሰራ ፓርቲው ጠቅሶ፣ ፓርቲዎች በንግድ ስራ ውስጥ መግባት ስለማይችሉ ለግል ጋዜጦች የህትመት አገልግሎት አንሰጥም ብሏል።
የሀገር ውስጥ አቅራቢዎች በጋዜጣ ላይ በወጣ የጨረታ ማስታወቂያ በቀረበው ዝርዝር መረጃ መሠረት መሳተፍ እንደሚችሉ የተናጋሩት የፓርቲው ተወካይ፤ ማሽኑን ከሀገር ውስጥ መግዛት ያስፈለገበት ምክንያት ከውጭ ተገዝቶ ሲገባ ያለውን ረጅም ጊዜ ለመቀነስና ማሽኑን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመግዛት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡(ምንጭ፤ አዲስ አድማስ)
ከአንድ ሥጋ ቤት በተመሣሣይ ወቅት ሥጋ ገዝተው የተመገቡ ነዋሪዎች በህመም እየተሰቃዩ ነው
ከአንድ ሥጋ ቤት በተመሳሳይ ወቅት ሥጋ ገዝተው የተመገቡ የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች በህመም እየተሰቃዩ ነው። ነዋሪዎቹ ከቆየ ደንበኛቸው ሥጋ ገዝተው ለልደት፣ ለሽምግልና፣ ለሰርግ የተጠቀሙበት ሁኔታ ቢኖርም ታዳሚዎቹም ሆነ ባለቤቶቹ በሙሉ ለህመም መዳረጋቸውን ገልፀውልናል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ፀሐይ ሙላቱ ቤተሰቧ ለነበረበት የሽምግልና ፕሮግራም ከሥጋ ቤቱ 25 ኪሎ ሥጋ የገዙ መሆናቸውን ገልፃ ተጠርተው የነበሩት ወደ 60 የሚጠጉት ታዳሚዎች በዕለቱ ከምሽትና ከሌሊት ጀምሮ ለከባድ ህመም የተጋለጡ መሆናቸውን ገልፃልናለች። በአመጋገብ በኩልም የተገዛውን የከብት ሥጋ ሳይሆን ዶሮ ብቻ የተመገቡ ሰዎች ግን ያልታመሙ መሆናቸው ወጣት ፀሐይ ገልፃለች።
meat sellerበተመሳሳይ መልኩ አቶ ተሾመ ሙላቱ የተባሉ በልደታ ክፍለከተማ የቀድሞው ወረዳ 5 የቤት ቁጥር 048 ነዋሪ ከሥጋ ቤቱ የተገዛውን ምግብ ተመግበው ለህመም መዳረጋቸውን ገልፀውልናል። ጌጃ ሰፈር የሚባል ነዋሪዎችም ከዚያው ተመሳሳይ ሥጋ ቤት ገዝተው ለልደት ዝግጅት የተጠቀሙ ነዋሪዎችም ለከፍተኛ ህመም የተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸውልናል። የህመሙን ሥሜት በተመለከተ የገለፁልን ታማሚዎቹ በዋነኝነት ማንቀጥቀጥ፣ ማስመለስ፣ ተቅማጥ፣ የአቅም ማነስ፣ ቁርጠት የራስ ምታትና ለመግለፅ የሚያስቸግር የህመም ስሜት የፈጠረባቸው መሆኑን ገልፀውልናል።
በልደታ ተክለ ሃይማኖት ክሊኒክ በተደረገላቸው ምርመራም ውጤቱ የምግብ መበከል የሚያሳይ መሆኑን የተገለፀ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልፀውልናል። ነዋሪዎቹ ምግቡን ከተመገቡ ቀናት ቢቆጠሩም የህመሙ ስሜት ባለመጥፋቱ የምርመራቸውን ውጤት ይዘው ወደ ክስ የሚያመሩ መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል። (ፎቶ ለማሳያ የቀረበ – ምንጭ፡-ሰንደቅ ጋዜጣ)
መንግስት የሼህ ኑሩ ይማምን ግድያና የሙስሊሙን ተቃውሞ ከአንድነት ፓርቲና ኢሳት ጋር ሊያያዝ ሞከረ
መንግስት ትናንት ሼህ ኑሩን ማን ገደላቸው በሚል ርእስ በኢቲቪ በለቀቀው ዘጋቢ ፊልም ላይ አንድነት ፓርቲ የሼህ ኑሩን ግድያ ደግፎ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲጠራ ማድረጉን የግንቦት7 ልሳን የሆነው ኢሳት ቴሌቪዥንም አሸባሪዎችን ” አይዞአችሁ በርቱ” እያለ ድጋፍ እንደሰጣቸው አንድ ግለሰብን በማናገር አቅርቧል
በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ሶስት ተጠርጣሪ ገዳዮች ቀርበው የሚናገሩ ሲሆን፣ ፊልሙ  ከአንዱ ክፍል ተቆርጦ ከሌላው ክፍል እየተገጣጠመ የተቀናበረና ገዳይ የተባሉትም ከፉኛ የተደበደቡ በሚመስል መልኩ ለመናገር ሲቸገሩ ይታያል።
አንድነት ፓርቲ   ”የሙስሊሞችን ጥያቄና የሼክ ኑሩን ግድያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ማያያዝ ወንጀል ነው” በሚል ርዕስ  ባወጣው መግለጫ ዘጋቢ ፊልሙ መቅረቡን በጽኑ ተቃውሞአል።nuru
ፓርቲው  ፊልሙ ” የገዥውን ፓርቲ ብፅእና ከመተረክም በላይ ጉልበተኝነትንና ፍረጃን ማእከል አድርጎ ከአኬልዳማ እና ከጃሀዳዊ ሀረካት የቀጠለ በፓርቲያችን እና በዜጎች ላይ የተቃጣ ህገ ወጥ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው” ብሎታል፡፡
የመንግስትነት ስልጣን የያዘ አካል ሀገራዊ ችግሮችን ለምን በዶክመንተሪ ፊልም ለመፍታትና ለማዳፈን እንደሚጥር እንቆቅልሽ ሆኖብናል የሚለው አንድነት ”  የሙስሊም  ጥያቄ በውይይትና በመግባባት ላይ ተመስርቶ ሊመለስ እንደሚገባና የሀይል እርምጃው መቆም እንዳለበት አሳስቧል።
ፊልሙ የኢህአዴግ የፍረጃ ፖለቲካ የተንፀባረቀበት፤ የተለየ ሀሳብና ጥያቄ ያቀረቡ ግለሰቦችንና ተቋማትን ማሸማቀቅ ብሎም የማጥፋት እኩይ ተግባር ማሳያ መሆኑንም ፓርቲው ገልጿል። አንድነት ፍርድ ቤት በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ አድርጎ ውሳኔ ሳያሳልፍ በቴሌቪዥን ፍርድ መስጠቱ ገዢው ፓርቲ በህግ የማይገዛ አምባገነን ስለመሆኑ ግልጽ ማሳያ ሲሆን የፍትህ ስርዓቱ ልዕልናም በአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ መገፈፉን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት የፓርቲያችን አመራሮች በየግዜው የሚያደርጉትን ንግግሮች ሞያንና ንጹህ ህሊናን በሚያጎድፍ መልኩ እየቆራረጠ ሙሉ ትርጉሙን እንዳይዝ አድርጎ በማስተላለፍ እየፈጸመ ያለው አሳፋሪ ተግባር እንዲታረም፣  በሼህ ኑሩ ላይ የተፈጸመው ግድያ በየትኛውም አካል የተፈጸመ ቢሆንም ህገ ወጥ እና ኢሰባአዊ መሆኑን ፓርቲው ጠቅሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት በክርስቲያኑና በሙስሊሙ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር እየሰራ ነው በማለት አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ለኢሳት ገልጸዋል።
መንግስት በተለያዩ ቀበሌዎች ስብሰባዎችን እየጠራ ክርስቲያኑ ወገን በሙስሊሙ ጥያቄ ፍርሀት እንዲሰማው እያደረገ መሆኑን እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar