August 2, 2013
የሪፖርተር ጋዜጠኛ የማነ ናግሽ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዙሪያ ያቀናበረውን የተንኮል ወጥመድ ተመርኩዤ በሰጠሁት ምላሽ ዙሪያ የማነ አስገራሚና ከርእሰ ጉዳዩ ጋር የማይገናኝ “መልስ” ለመስጠት ሞክሯል። ካድሬ ሆኖ የቀረበው የሪፖርተሩ የማነ ምላሹን ሲጀምር በኢትኦጵ ጋዜጣ በኢየሩሳሌም…ይቀርብ የነበረውን ዘገባና የፃሓፊውን ማንነት ከጠቀሰ በኋላ « በ2005 እ.ኤ.አ ችግር ውስጥ ሊከቱን ከነበሩ…» ይላል። መለስ ዜናዊ የሚመሩት ፓርቲ 18 ጋዜጠኞችን እስር ቤት በመወርወር፣ ከጋዜጣ ዝግጅት ክፍሎቹ ንብረትና ገንዘብ በሃይል በመዝረፍና ሁሉንም ነፃ ፕሬሶች በሃይል በመዝጋት የወሰዱትን እርምጃ ነው…የማነ «ችግር ውስጥ ሊከቱን..» ሲል የመለስ/በረከትን የፈጠራ ክስ ..እርሱም ቃል በቃል የደገመው።
በተጨማሪ በነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ በጅምላ የተወሰደውን እርምጃ አለቃው አማረ አረጋዊ በጋዜጣው በወቅቱ ደጋግሞ በርእሰ አንቀፅ በ<አቋም> ደረጃ የፃፈውን « አርፋችሁ ተቀመጡ ያልነው ይህ እንዳይመጣ ነበር..» እያለ የቸከቸከውን እንድናስታውስ አድርጎናል። ከዚህ አልፎ የቅንጅት መሪዎች ላይ በማላገጥ ለገዢው ፓርቲ ግልፅ የሆነ ድጋፍ እንዳለው ያረጋገጠበትን አንዘነጋውም። “ኢህአዴግ በምርጫ መሸነፉን በዘገበና “ የሽግግር መንግስት ይቋቋም” ብሎ በፃፈ ማግስት ነበር፥ ተግልብጦ የጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ አመራሮችን መታሰር በመደገፍ በየጎዳናው የተረፈረፉ ንፁሃን ዜጎች ደም ላይ ሲያላግጥ የታየው። እንዲያውም « እነኢንጂነር ሃይሉ ሻውል በቃሊቲ እስር ቤት መንግስት መሰረቱ» ሲል ለመሳለቅና በህዝቡ ቁስል ለማላገጥ ሞክሯል።
ዛሬም እነ የማነ ናግሽ የህዝብን ያልሻረ ቁስል እየቆሰቆሱና የተወሰደውን እርምጃ እያቆለጳጰሱ እግረ መንገዳቸውን የገዢው ፓርቲ ደጋፊነታቸውን በአደባባይ ሊነግሩን ይዳዳቸዋል። አንድ ነገር ማወቅ ያለብህ አንተ የምትሰራበት ጋዜጣ 10ሺህ የማይሞላ ኮፒ ሲያሳትም እነኢትኦጵ፣ ነፃነት፣ ምኒሊክ፣ አስኳል…የመሳሰሉት ጋዜጦች እስከ 160 ሺህ ኮፒ በማሳተም በህዝቡ ከፍተኛ ተቀባይነት ነበራቸው። ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው!! ሪፖርተር ብቻውን ቀርቶም 10ሺህ ኮፒ መድረስ አልቻለም።
ሽመልስና አለቃው ይህንኑ ጠቅሰው አማረን ፊት ለፊት አብጠልጥለውታል። « ፍትህ » ጋዜጣ እስከ 40ሺህ ኮፒ ያሳትም የነበረው ከናንተ ኋላ መጥቶ ነው። ህዝብ ሁሉንም ስለሚያውቅ መርጦ ያነባል። በህብረተሰቡ ተቀባይነት የማጣቱ ምስጢር “ የምታራምዱት ፅንፈኛ አቋም ወይም ወገንተኛነታችሁ” ነው። በዚህ ያላበቃውና ራሱን “ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ ነኝ” ሲል የገለፀው የማነ ናግሽ፥ “በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ስለሙስሊሙ ማህበረሰብ የመብትና የነፃነት ጥያቄ ዘገባ እንደሚቀርብ፤ ከፈለገም የጋዜጣው ድረገፅ ላይ በመግባት መመልከት እንደሚቻል” ያለሃፍረት ሊገልፅ ሞክሯል። በእርግጥ የበረከት ልሳኖች ኢ.ት.ቪና ራዲዮ እንደሚያቀርቡት « በሽብርተኛነት የተከሰሰው እስክንድር ነጋ ማስረጃና ምስክር ቀረበበት..ተፈረደበት» ዜናዎች በሪፖርተር ጋዜጣ ሲወጡ እንደነበር አይካድም።
ይህንን ነው « ዘግበናል» የምትለው?..ይህንን ድራማ የመንግስት ሚዲያዎቹ ቀርቶ ካንጋሮው ፍ/ቤት አስቀድሞ ተፅፎ የተሰጠውና ያሳለፈው ፍርደ ገምድል ውሳኔ፣ ከመነሻው የበረከት « ድርሰት» ለመሆኑ « አኬልዳማና ጀሃዳዊ ሃረካት» በቂ ማስረጃ ናቸው። አንተም አለቃህም እውነቱን ሸፍናችሁ የገዢውን ፓርቲ ድርሰት ስለደገማችሁ ይሆን? .. በእስክንድርና በሌሎቹም ንፁሃን ዙሪያ « ዘገባ ሰራን፣ ዜና ለጠፍን..» እያልክ የምትቀባጥረው?…በጣም የሚያሳፍረው የሙስሊሙን ጥያቄና ሰላማዊ ተቃውሞ በተመለከተ « በየጊዜው ዘግበናል» ብለህ ያለአንዳች ህፍረት ልትናገር መሞከርህ ነው። እውነታውን ታዛቢው ወገን ይፍረድ! ?..ይልቅ ሰላማዊ የሆነ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄን በማንሳታቸው በድሬዳዋ በፖሊሶች የተወሰደውን እርምጃ እንዴት እንደዘገባችሁት ላስታውስህ?..« በድሬዳዋ በተፈጠረው ግጭት አንድ የዘጠኝ አመት ታዳጊ ከመሞቱ በቀር የከፋ ጉዳት አልደረሰም» ብላችሁ በጋዜጣው ፃፋችሁ። እንዲህ አይነት ዜና “ዘገባ” ይሰራል?…”የከፋ ጉዳት ደረሰ” የሚባለው ስንት ታዳጊዎች ሲገደሉ ይሆን?..ይህን ልትነግሩን ትችላላችሁ?..ደግሞም ስለሙስሊሙ ፍትሃዊ ጥያቄ አንድም መስመር እንዳልፃፋችሁ አስረግጬ ልነግርህ እወዳለሁ!! ቀጠልክና፥ « ሕገ መንግስቱን እናከብራለን፣ አንተና መሰሎችህ ምን እንድንፅፍ እንደምትፈልጉ እናውቃለን..» ስትል አስገራሚና የተደበቀ የሚመስለው ማንነትህን ግልፅ አውጥተሃል።
የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄም ፥ “በህገመንግስቱ የተቀመጠው የሃይማኖት ነፃነት ይከበር፤ መንግስት በሃማኖት ጣልቃ መግባቱን ያቁም፤ የሃይማኖት መሪዎቻችንን የመምረጥ መብት ይረጋገጥልን፤” የሚሉ ናቸው። በአንፃሩ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋግመው የሚቀርቡት ጥያቄዎች ገዢው ፓርቲ ራሱ ላወጣው ሕገመንግስት ተገዢ እንዲሆንና የዜጎች መብትና ነፃነት ይከበር የሚል ነው። ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ « ህገመንግስቱን እናከብራለን» በማለት መግለፅህ ሌላውን በህገወጥነት ለመወንጀል በማሰብ ይሆን?..ይህቺ ገለፃህ የነበረከትን የሰለቸ የማስፈራሪያና ሌላውን የመወንጀያ ዲስኩር ቃል በቃል የደገመች ናት። አያያዝክና፥ « አንተና መሰሎችህ የምትፈልጉት..» ብለሃል፤ “ምንድነው የምንፈልገው?.” ግልፅ ብታደርገው ጥሩ ነበር። ነገር ግን ምን ለማለት እንደፈለክ ከግምት በላይ መናገር ይቻላል፤ ይኸውም « ስለሕወሐት ምንም አንፅፍም፤ ስለነአዜብና ተከታዮቻቸው ዘረፋ አናጋልጥም፣ የምንፅፈው አማረ ስለሚጠላውና አጥብቆ ስለሚቃወመው በረከት ስሞኦን፣ ስለአላሙዲና አብነት..ብቻ ነው የምንፅፈው» ለማለት እንደፈለክ አያከራክርም። የሚያሳዝነው « ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ ነኝ » ባልክበት ብእር መልሰህ ጋዜጠኞችን በጅምላ ለመፈረጅና እንደገዢው ፓርቲ የተለመደ የፈጠራ < ታፔላ> ለመስጠት መሞከርህ ነው። በጣም አሳፋሪ ነው!! ባጭሩ “ ሚናህን ለይተህ” አደባባይ መውጣትህ የበለጠ የአንተና የአለቃህ « አቋም» እንዲታወቅ ማድረግህን ልገልፅልህ እሻለሁ።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar