søndag 19. mai 2013

ልቅ የሆነ የሙስና ግንኙነት… (ትንሽ ወግ)



አቶ መላኩ ፈንታ መንግስት የሚያውቀው በሽታ አለብኝ እና በዋስ ልፈታ፤ አሉ አሉ፤…
እኔ ደግሞ እንዲህ አልኩ፤
ምን ነካዎ አቶ መላኩ፤ መንግስት በሚያውቀው በሽታዎ ነውኮ ዘብጥያ የወረዱት፤ እርግጥ ነው ይህንን በሽታ ከየትም አላመጡትም፤ ከመንግስትዎ ጋር ባደረጉት ጥንቃቄ የጎደለው እና ልቅ የሆነ የሙስና ግንኙነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እርግጥ ነው መንግስታችን ራሱም የዚህ በሽታ ተጠቂ መሆኑ እሙን ነው፡፡ እርግጥ ነው በማራዘሚያ ብዛት እንጂ ሁሉም ባለስልጣኖቸች የዚህ ህመም ሰለባ መሆናቸውም ግልጽ ነው፡፡Melaku Fenta, a senior ruling party member in Ethiopia.
ታድያ መንግስት የሚያውቀው በሽታ ስላለብኝ ማሩኝ ከማለት በሽታውን ያመጣሁት ከእነርሱ ነውና ሁሉም ይምጡ ማለት አይሻልዎትም ነበር… ሃሃ (በቅንፍም የምር ግን ምንድነው መንግስት የሚያውቀው በሽታ…)
አቶ ገብረዋህድ ገብረ መድን በቤተሰቦቼ ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል… ሀገሪቱ ምን አይነት ሀገር እየሆነች ነው… ብለዋል አሉ፡፡
እኔ ደግሞ እንዲህ አልኩ፤
አቶ ገብረዋህድ ቆየችኮ እርስዎ በስልጣን ነጠላ ሰረዝ በዶላር ነጠላ ሰረዝ በፓውንድ እና በብር የሞቀ ቤትዎ ሆነው የውጪው ቅዝቃዜ አልታወቅዎትም እንጂ “ሀገሪቱ ምን አይነት ሀገር እየሆነች ነው…” የሚለውን ጥያቄ እኮ እነ አቶ አንዷለም አራቄ መጠየቅ ከጀመሩ ቆዩ፣ ሀገሪቷ ምን አይነት ሀገር እየሆነች ነው የሚለውን ጥያቄ እነ አቶ በቀለ ገርባ ጠይቀው ማንም መልስ አልሰጣቸውም፡፡
በቅርቡ እንኳ አቡበከር በቴሌቪዥን እጁን በካቴና ታስሮ ፖሊሶች ሲሳሳቁበት በአደባባ እያየን ሁላችንም በአንድ ድምጽ ሀገሪቷ ወዴት እየሄደች ነው… ብለን ጠይቀን ነበር፡፡ ግን እርስዎም ሆኑ ጓደኞችዎ ድምፃችን አልሰማችሁም፡፡
እነ ርዮት አለሙ እነ እስክንድር ነጋ እነ ውብሸት ታዬ በፍትህ እጦት እና በኢሰብአዊ አያያዝ ተማረው “ሀገሪቷ ምን አይነት በያይነቱ ሆነች…” ብለው ከጠየቁ ቆዩኮ… ታድያ ያኔ የት ነበሩ… (በቅንፍም ይቺን ነገር ሁሉም ባለስልጣን በየተራ ይያት ብለን እንመርቃለን)
ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሌሎችንም ሙሰኞች አጋልጡ ብሎ ስልክ ቁጥሩን ሰጥቶናል፡፡ አሉ
እኔ ደግሞ እንዲህ አልኩ፤
እኔ የምልህ ፀረ ሙስናዬ የምን ቁጥ ቁጥ ነው ብዬ… አጠቃላይ ኢህአዴግን በሙስና ብልግና ብጠቁም ለማሰር የሚያስችል ሰፊ ቃሊቲ አለህ… ከሆነ ዛሬውኑ እደውላለሁ…

ስድስት:- ቃል ኪዳን፤ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ



ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም

እንግዲህ ኢሳት በነገረኛነትም ሆነ በጠመንጃ-ያዥነት በኩል ከሎሌነት ጠባይ ጋር የተያያዘውን ኢትዮጵያውያን ያለንን አጉል ባህል ሁሉ እየነቀስን እየጣልን በዘመናዊና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ መሠረት ለመጣል ዋና መሣሪያ ሊሆነን ይችላል ብሎ ማመን መነሻ ይሆናል፤ ይህ እምነት ከሌለ የእምቧይ ካብ ነው፤ ይህ እምነት ራስን ማጽዳትንም ይጠይቃል።
ማክሸፍ እንደምንችልበት ከማመን እንጀምር፤ ስለዚህም ኢሳት ሊከሽፍ የሚችልበትን እያንዳንዱን መንገድ ማጥናትና በቅድሚያ ፈውሱን ማዘጋጀት የሚጠቅም ይመስለኛል፤ ይህንን ጉዳይ በትጋት ለመከታተል የኢሳትን አማራጭ የማይገኝለት የአገር ጥቅም በእውነትና በትክክል መገንዘብ ያሻል፤ ዘመን-አመጣሽ ነገር ብቻ አድርጎ መመልከቱ ለወረት ይዳርገዋል፤ ወረትን ማክሸፍ ቀላል ነው፤ ከከሸፈ በኋላ እንዲያንሰራራ ለማድረግ በጣም ከባድ ሥራን ይጠይቃል፤ ስለዚህ ከወዲሁ ኢሳት ጠንካራ መሠረት ላይ እንዲተከል የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ዘለቄታ እንዲኖረው ማረጋገጫ ይሆናል።Prof. Mesfin Woldemariam
የኢሳት መክሸፍ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያጨልማል፤ አንፈራጥጠው ከላይ ቤት እታች ቤት እየቀላወጡ አካላቸውን፣ አእምሮአቸውንና መንፈሳቸውን የሚያባልጉ ሰዎችን ያበራክታል፤ የድብቅብቆሽ ዓለምን እየፈጠሩ የጠራውን ከደፈረሰው፣ የጸዳውን ከአደፈው፣ ሳይለዩ ለሚያወሩት ደካሞች ሜዳውን ያሰፋላቸዋል፤ የወያኔ/ኢሕአዴግን ፍርሃት ወደመርበድበድ ይለውጠዋል፤ የጦርነት ጥሩምባ ለሚነፉትም ሜዳውን እያሳየ  የቀረርቶ በር ይከፍትላቸዋል፤ ይህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምንና ስምምነትን፣ እድገትንና ብልጽግናን፣ ኩራትንና ክብርን አያስገኝም።
ንስሐ ለመግባት ወኔ ለሌላቸው፣ በሠሩት ጥፋት አገርን ወይም ወገንን በመበደላቸው ዛሬም ለመኩራራት ለሚፈልጉት፣ አርበኛውንና ባንዳውን ባንድ ሚዛን አስቀምጠው ለሚተቹት፣ የኢትዮጵያውያንን ሰውነት አራክሰው ጊዜያዊ ጥቅማቸውን ለሚያከማቹ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በተንኮል እየመነዘሩ የሥልጣን መሰላል ለሚያበጁ ሁሉ ፊት-ለፊት ቆሞ ለሚጋፈጣቸው ኢሳት መድረክ ይሆናል፤ የኢሳት ዋና ጥቅሙ እዚህ ላይ ነው፤ ይህንን ተግባር ለመፈጸም ኢሳት የኢትዮጵያ፤ ኢሳት የኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲሆን መንገዱን እንጥረግ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በባለቤትነት የሚመራውና የሚያካሂደው እናድርገው፤ ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢሳት ላይ ያለው መብት ነው ከተባለ፣ ግዴታውንም አብሮ መቀበል ሳይታለም የተፈታ ይሆናል፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉ ግዴታውን በቃል ኪዳን መቋጨት ከቻለ ኢሳት ከቀፈፋና ለመክሸፍ ይድናል።
የእኔ ምኞት ኢሳት በኢትዮጵያውያን ቃል ኪዳን ተገንብቶ በሕገ ኀልዮት እየተመራ አዲስ ዓላማ፣ አዲስ የአሠራር ዘዴ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ጉድለቶችን ሁሉ አውቆ በጥንቃቄ እየነቀሰ አዲስ የመተማመንና የመተባበር ባህል ይፈጥራል የሚል ነው፤ (እኔ ቃል ኪዳን የምለው ሁለት ቁም-ነገሮችን የያዘ ነው፤ በአንድ በኩል እውነትን አለመፍራት (ወይም በጥሩ መልኩ ለእውነት መቆም፣) በሌላ በኩል ለአንድ የጋራ ዓላማ የራስን ግዴታ ሳያስተጓጕሉ ለመወጣት በቆራጥነት መቆም፤ ስንት ልጆች አሉህ ተብሎ ሲጠየቅ ሁለት ወይም ሦስት እያለ አጥር ላይ ተንጠልጥሎ የሚመልስ ለቃል ኪዳን አይበቃም፤) ከሩቅ እንደማየው ጥቂት ሰዎች ኢሳትን በቃል ኪዳን ተይዘው ሲጥሩ አብዛኛው ደግሞ በአጋጣሚ እንደተመቸውና እንደፈለገ የተቻለውን የሚያደርግ ምንም ዓይነት ቃል ኪዳን የሌለው ነው፤ ከተሳሳትሁ ደስ ይለኛል፤ አስተያየቴ ትክክል ከሆነ ኢሳት አይዘልቅም፤ መክሸፍ ዕጣ-ፋንታው ይሆናል።
ዓላማውን ሳይመታ እንዳይከሽፍ ኢሳት በቃል ኪዳን መታሰር አለበት፤ እንዴት? ቢባል፣ አንድ ሚልዮን ኢትዮጵያውያን ለኢሳት በአማካይ በወር አሥር ዶላር ለመስጠት ቃል ኪዳን ቢገቡና የየዓመቱን ግዴታቸውን በአንዴ ቢወጡ፣ በወር አሥር ሚልዮን ዶላር (በዓመት አንድ መቶ ሃያ ሚልዮን ዶላር) ኢሳትን  ኢትዮጵያዊነትን የሚያስከብር የሰላምና የፍቅር፣ የብልጽግናና የተስፋ መድረክ ሊያደርገው ይችል ነበር፤ አብዛኛዎቹ ችሎታው ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለኢሳት የሚገቡት ቃል ኪዳን ለጥሬ ሥጋና ለመጠጥ የገቡትን ቃል ኪዳን ካላሸነፈ ታማኝ በየነን በያገሩ እየላከ በሚያደርገው ዓመታዊ ቀፈፋ ኢሳት ይገነባል ብዬ ለማመን ያሰቸግረኛል፤ በኢሰመጉ አይቼዋለሁ።
ቀፈፋ ወይም ልመና አንዱና ዋናው የባህል ሕመም ነው፤ እያንዳንዳችን ከዚህ ሕመም ለመዳን በራሳችን ላይ መዝመት የሚያስፈልገን ይመስለኛል፤ በተለይ በአገር ጉዳይ፣ በወገን ጉዳይ ማን ነው ለማኝ? ተለማኙስ ማን ነው? ስለአገሩና ስለወገኑ ችግር የማያውቅ አለ? ለማወቅ የማይፈልግ ይኖራል እንጂ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ችግር ገሀድ ነው፤ በአስከፊ መልኩ ለመረዳት የሚፈልግ በመረረ ቋንቋ የተጻፈውን የዶር. በድሉ ዋቅጅራን ሀገሬ ገበናሽ(ክፍል አንድ፣  ክፍል ሁለትና ክፍል ሦስትን)  ያንብብ።  አንብቦ ካላለቀሰ፣ አልቅሶ ‹‹ምን ላድርግ!›› የሚል ቁርጠኛነት ያላደረበት በዓመት አንድ ጊዜ በታማኝ ቀፈፋ አገሩንና ወገኑን መርዳት አይችልም፤ እምነቱ ካለ፣ ስሜቱ ካለ በገንዘብ የሚደረግ ማናቸውም እርዳታ የመጨረሻው፣ መናኛው ነው፤ መናኛ የሚያደርገው የገንዘቡ መብዛት ወይም ማነስ አይደለም፤ ለአገርና ለወገን ከዚያ በጣም የበለጠ የሚከፈል ዋጋ በመኖሩ ነው፤ አያቶቻችንና ቅምአያቶቻችን የከፈሉት ዋጋ በገንዘብ አይመነዘርም፤ እነሱ በሕይወታቸው ያስገኙልንንና እኛ በገንዘብ የሸጥነውን ኩራትና ክብር በገንዘብ ብቻ አናስመልሰውም፤ ቃል ኪዳን እንግባ!

torsdag 16. mai 2013

“በኢንቨስትመንት ስም የሚፈጸም የመሬት ነጠቃ፤ በኢትዮጵያ” ጥናት ትርጉም ይፋ ሆነ!!


የጥናቱን ሙሉ ዘገባ ለማግኘት እዚህ ይጫኑ

በኢንቨስትመንት ስም የአገር ሃብትና ትውልድን እየበላ ስላለው የመሬት ነጠቃ አስመልክቶ የኦክላንድ ተቋምና ድርጅታችን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በጋራ ያዘጋጁት ጥናታዊ ዘገባ ይፋ ሆነ። የጋራ ንቅናቄያችን ዋና ዳይሬክተር ጥናቱ በትክክለኛ ጭብጥ ላይ ተመስርቶ እንዲዘጋጅ ለህይወታቸው ሳይሳሱ መረጃ በመስጠት ለተባበሩ ዜጎች “ታላቅ ክብር ይሁንላችሁ። አሁን አትታወቁም። ግን ከቶውንም አትረሱም። ክብር ለማትታወቁት ግን ለማትረሱት የአገር ጀግኖች” በማለት ምስጋና አቅርበዋል።Understanding Land Investment Deals in Africa (Ethiopia)Understanding Land Investment Deals in Africa (Ethiopia)
ኢህአዴግን በደፈናው መቃወምን ዓላማው ያላደረገው ይህ ጥናታዊ ዘገባ ዜጎችን ካደጉበት፣ ከኖሩበት፣ ከቀያቸው፣ ከህልውናቸው፣ ከርስታቸው፣ ወዘተ ያለ አንዳች ውይይት፣ ምክክርና ንግግር በማፈናቀል ለውጪ ኩባንያዎችና ለራሱ ለባለጠመንጃው አገዛዝ ሰዎችና ባለሟሎች መሬት ማከፋፈሉን በማስረጃ ያሳያል። የራሱ የኢህአዴግ አካላትም በሪፖርቱ ውስጥ በአግባቡ ድምጻቸው ተካትቷል። የሚጠቀሙባቸው አዋጆችና ህጎችም አልተዘለሉም።
“የውጪ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ለቴክኖሎጂ ዝውውር፣ በአገሪቱ ያለውን የምግብ እጥረት ለማስወገድ ይረዳል” የሚሉ ምክንያቶች እያቀረበ ያለው ኢህአዴግ በተግባር ሲፈተሽ ተግባሩና ዓላማው ምን እንደሆነ የሚያመለክተው ጥናቱ የስርዓቱ ሰለባዎች፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት፣ ኢንቨስተሮች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች፣ የቅርብ ምስክሮች፣ የተለያዩ ከዓለምአቀፍ ተቋማት የተገኙ መረጃዎች፣ አገዛዙ ራሱ ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎችና ለጥናቱ አስፈላጊ የተባሉ አኻዞች የተካተቱበት በመሆኑ እውነታውን ህዝብና ማናቸውም ወገኖች እውነቱን ለመረዳት ያስችላቸዋል ተብሎ በጉልህ ታምኖበታል።
በምሳሌ ለማሳያነት የተጠቀሰው የሳዑዲ ስታር ኩባንያ የሚያመርተውን ሩዝ ደብረዘይት በገነባው ተቋሙ አማካይነት ሩዙን የመለየትና ለኤክስፖርት የማዘጋጀት ስራ ይሰራል። የተመረጠውና መለኪያውን የሚያሟላው ሩዝ ኤክስፖርት የሚደረግ ሲሆን፣ ደቃቃውና በሚሊሜትር ተለክቶ ለኤክስፖርት ደረጃ የማይበቃው አገር ቤት እንዲቀር ይደረጋል። ከዚህ አንጻር እንኳ ቢታይ የመሬት ኢንቨስትመንት የተባለው ዓለም ጠንቅቆ ለሚያውቀው የአገራችን የምግብ እጥረት ችግር መፍትሄ ሊሆን አይችልም። በጥናቱ ዝርዝር ጉዳዩ አለ።
ኢህአዴግ በፖለቲካው ውድማ ላይ ቆሞ የሚያወራውና በተግባር የሚሆነውን እውነት ከሰለባዎቹ አንደበት በመቅዳት ሊስተባበል በማይችልበት ደረጃ ያቀረበው ጥናት፣ ዜጎች ከቀያቸው  ከመፈናቀላቸው በፊት ምክክርና የስነልቦና ዘግጅት እንዲደረግ ጊዜ እንደሚሰጥ በህግ የተደነገገ ስለመሆኑ፣ ነግር ግን እውነታው የተገላቢጦሽ መሆኑንን ጥናቱ በማስረጃ ያትታል። ዜጎች ነገ ስለሚሆነው እንኳ ሊያውቁ በማይችሉበት ደረጃ ማለዳ ካረፉበት ሲነቁ ዶዘር ማሳቸውን፣ የጓሮ አትክልታቸውን፣ የኑሯቸው መሰረት የሆነውን ደናቸውን፣ ቤታቸውን ሲጠርግ እንደሚያዩ እነዚሁ መከረኞች ለህይወታቸው ሳይሳሱ መናገራቸውን ጥናቱ ትኩረት ሰጥቶ አቅርቦታል።
የመሬት ካሳ እንኳ ባግባቡ የማያገኙት ወገኖች በራሳቸው አንደበት፣ በግብር የደረሰባቸውንና ከፊት ለፊታቸው ያለውን አደጋ አስመልክቶ በዝርዝር ሚዛናዊ በማድረግ ያቀረበው ጥናት ኢህአዴግ ለማስተባበል ከፈለገ በዜናና በተራ ጩኸት ሳይሆን በመረጃ የተደገፈ፣ ሁሉንም ወገኖች ያካተተ  ሚዛናዊ ሪፖርት ካቀረበ ብቻ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) በማስተባበያነት እንደሚቀበለው አስቀድሞ ለመግለጽ ይወዳል።
በአገርና በግለሰብ ደረጃ መረጃ ለማዳረስ፣ በተመሳሳይ ኢህአዴግ የሚያሰራጨውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ማጋለጥ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቱን ማሳየት፣ የተሳሳተውን ፖሊሲ ማስቀየር ዋናው የጥናቱ ዓላማ ነው። በጥናቱ በቀረበው ጭብጥ መሰረት የዓለም ባንክ፣ ወዳጅ አገሮች፣ አበዳሪ አገሮች ፖሊሲ አውጪዎች ወዘተ አካሄዳቸውን እንዲመረምሩ ለማስቻል ሰፊ ስራ የተሰራ መሆኑንን በዚህ አጋጣሚ እንጠቁማለን። በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ የውጪና የአገር ውስጥ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ሰፊ ስራ የተሰራ ቢሆንም፣ በዋናነት የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን እየተሰራ እንደሆነ ሲረዳ ትግሉን ማቅለል፤ ውጤቱንም ማቅረብ ይቻላል የሚል እምነት አለን።
በዚህና በሌሎችም ተዛማጅ ምክንያቶች በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት፣ ረዥም ጊዜ ተወስዶ የተሰራው የትርጉም ሰራ ሰውን የሚያክል ክቡር ፍጥረት ከማደሪያው እንዲወጣ ተደርጎ እንዴት ወደ ጉድጓድ እንደሚወረወር ለመጪው ትውልድ በታሪክነት፣ አሁን ላለነው በመረጃነት፣ ከሁሉም በላይ ከጩኸትና ከመረጃ አልባ ክስ የምናገኘው ጥቅም አለመኖሩን በመረዳት አቋቋምን ለማስተካከል ይረዳል፣ ታላቅ ምሳሌም ይሆናል ብለን እናምናለን።
ጥናቱን በማሰራጨትና ዜጎች እጅ እንዲደርስ በማድረጉ በኩል የሁሉም ወገኖች ያልተቆጠበ ጥረት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን። በዚህ አጋጣሚ እናወጣዋለን ብለን ካሰብንበት ጊዜ በማለፍ ተጨማሪ ሳምንታት በማዘግየታችን ታላቅ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ በአገራችን ካለው የመረጃ አፈና አኳያ የጥናቱ መጠን ሰብሰብና አጠር ባለ መጠን በኢሜይል እንደሚሰራጭ ሆኖ በአዲስ መልክ ሲቀናበር ተጨማሪ ሳምንታትን መውሰዱ የግድ ሆኗል፡፡
የጋራ ንቅናቄያችን ጽሁፉን የማሰራጨቱ ስራ በጨዋነት፣ ለጽሁፉ ባለቤቶች (ለእንግሊዝኛው የኦክላንድ ተቋም ለአማርኛው ደግሞ አኢጋን) አስፈላጊውን እውቅና በመስጠት እንዲሆን በዚህ አጋጣሚ አበክረን እንሳስባለን። ከመሬት ነጠቃ በላይ የከፋ ወንጀል የለም። ዜጎችን በምድራቸው ወደ ባርነት የሚያሸጋግረው የመሬት ነጠቃ የአገሪቱን ሃብትና ንብረት እየበላ ነው። ይህንን ወደር የሌለው ወንጀል ለማጋለጥ፣ ለመታገል፣ ለመቃወምም ሆነ ተዛማጅነት ያላቸው ተግባራት ለማከናወን ለሚፈልጉ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ሚዲያዎች ይረዳ ዘንድ (Land Grab– http://landgrabsmne.wordpress.com) የሚባል ብሎግ እንዲሁም በፌስቡክ Land Grab/መሬት ነጠቃመከፈቱን ለማሳወቅ እንወዳለን። በቅርቡ የሚሻሻለው ይህ ብሎግና የፌስቡክ ገጽ ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ ሁሉም ዓይነት ማስረጃዎች የሚታተሙበት ስለሚሆን መረጃ ለሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ መልካም አጋጣሚ ይሆናል። ጥናታዊ ዘገባውን ከድረገጻችን ላይ ለማግኘት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡ በኢሜይል ለማግኘት የሚፈልጉ በሙሉ በሚከተለው አድራሻ (media@solidaritymovement.org) ቢጠይቁን በቀጥታ የምንልክ መሆናችንን እናሳውቃለን፡፡
በመጨረሻም የጋራ ንቅናቄያችን ዋና ዳይሬክተር ለተርጓሚው ከሁሉም በላይ ግን የስርዓቱ ላንቃ ስር ሆነው የህይወት ዋጋ በመክፈል መረጃ ለሰጡት ወገኖች የአክብሮት ምስጋና አቅርበዋል። አቶ ኦባንግ በመልዕክታቸው “በቦታው ላይ ሆናችሁ ለህይወታችሁ ሳትፈሩ ይህንን መረጃ የሰጣችሁ ሁሉ የአገር ጀግኖች ናችሁ፤ አሁን አትታወቁም። አሁን ልንገልጻችሁ አንችልም። ጊዜና ወቅት ጀግንነታችሁን እስኪገልጹት ግን አትረሱም። ልትረሱም አትችሉም። ብዙ ባይነገርላችሁና ባይዘመርላችሁም ታላቅ ስራ ሰርታችሁዋልና ክብር ይሁንላችሁ” ብለዋል፡፡

አጀንዳን እያስቀደሙ ማዘናጋት ከተጠያቂነት አያድንም!

አልፎ አልፎ የጉዞን ጎዳና መመርመር ከብዙ ስህተት ያድናል። ግምገማ -እንደሚሉት የ”ለምን አልታዘዝክም” -“ለምን የብዝበዛው አካል/አፋኝ አልሆነክም” ውጠራ ሳይሆን የሕዝቡን የእርምጃ መስመር በተቻለ ለመጠበቅ- ከላስፈላጊ—–ፍጆታም ለመላቀቅ የሚበጅ መሆኑን በማጤን ነው።

በቀደመ መጣጥፍ ስርአቱ አሁን ሞቷል የሚንቀሳቀሰው በበበድኑ ነው የሚል ታማኒ የሆነ ሓሳቦች ተጨብጦ ነበር። ስርአቱ በቁሙ ሙት ነው ግን ዘለቀ ስንል ሊያዘልቁት ያበቁትን ጥቂት ነጥቦች በጥቅሉ ተቀምጠውም ነበር።
አንድ ሀቅ ይፋ መውጣት አለበት ከተባለ መነገር ያለበት አብይ ጉዳይ-የሆነውስ ሆነ- ትላትናና ዛሬ የህዝቡን ትግል የሚመራው ማነ ነበር-ዛሬስ ማነው ብለን መጠየቅ የግድ ነው። እንደ አነጋገርም ስልት “እርሱ አጀንዳ አለው” “የአንተ አጀንዳ ምንድር ነው” “እርሱ የሚያራምደው የራሱን አጀንዳ ነው” ይባላል። በእርግጥም የዚህ ጥቆማ አጀንዳ “አጀንዳ” እንደመሆኑ ሁሉም የራሱ አጀንዳ አለው። የሚያራምደውም አጀንዳውን ነው። የራስን አጀንዳ የሁሉ ማድረግ ደግሞ በክፉም በደጉም አንድ እርምጃ አስቀድሞ ማስተዋልን ያመለክታ።
አጀንዳን አጀንዳ አድርጎ መነሳቱም ትርጉሙ እዚህ ላይ ነው። ብዙ እንደታዘብነውና አሁንም እየተካሔደ እንዳለው የህዝቡን አረማመድ ትግልም ትንቅንቅ የሚመራው ማን ነበር ስንል የምናገኘው ምላሽ በእውነቱ-ባብዘኛው የህዝቡ እንቅስቃሴ ይመራ የነበረው አሁንም የሚመራው የመሰሪው ስርአት እንጂ በሕዝቡ እንዳልነበረ መተማመን መልካም ነው። እድሜ ለእከሌ እንዳንል ሞቷልና የተንኮሉ ምንጭ እንዴት እያንዳንዲቷን እርምጃ በቅጥ እያስተዋለ ሲሸርብ እንደነበረ በቂ ግንዛቤ የወሰደ እዚህ ላይ ግር አይለውም። በመሰረቱ ሕዝብ ወይንም ድርጅቶች አጀንዳ አልነበራቸውም አልተባለም-ተጠለፈ እንጂ-እንቀጥል።
ከየት እንጀምር? ሰለቸን እስከምንል ያሰለቸንን አረማመድ መቃኘት ታሪክ መጻፍ አይነለምና -ይህ ሁሉ ሲሆን የት ነበሩ የሚያሰኝ ሂደት ሆኖ እናገኘዋለን። ትንሽ ትዕግስትን የሚጠይቅ ቁምነገር።
አጀንዳ ስንል አሳቻነቱን፤ጠላፊነቱን፤ሳይቀድሙኝ ልቅደም ባይነቱን፤ ጩኸቴን ቀሙኝነቱን፤መሰሪነቱን ብልጣብልጥነቱን ምን የማይባል አለ -የሚደረደረው የጨለማ አስተሳሰብ ሁሉ እውን የሚሆንበት አረማመዱን ለመጠቆም ነው። ትንሽ ወደሗላ መለስ ብለን የተቻለንን እንናዘዥ-ወይ ፍርጃ!በቁም ኑዛዜ! እስኪ እንደወረደ እንበል።
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት(ባጭሩ አራት አመታት)
የሕዝብ ትግል በጠነከረበት-በቅርብ ለሚያስታውሰው- ስርአቱ የሁለት ባላንጣዎችን ውክልናና ሀላፊነትን ይዞ ሕዝብን በሚሞግትበት ወቅት የኢትዮ-ኤርትራ የእልቂት ጦርነት ሲከሰት ሕዝብን በብሔራዊ ስሜት አንቆ አገር አድን አጀንዳ ተሰመረለት። በዚህ ጊዜ “ከባደሜ መለስ ወደመለስ” -በቀላሉ ይችን ጦርንተ ጨርሰን አናንቀዋለን ተባለ። ሁሉም በተቀየሰለት ቦይ መፍሰስ ጀመረ። እዚህ ላይ ብዙ አርቆ አስተዋዮች-የማያዋጣ-የትግልን ስልት አጨናጋፊ”አጀንዳ” ለመሆኑ አበክረው ቢመክሩም አፈ ጮሌው ባገር ክህደት ከመወንጀል አልተቆጠበም ነበር። የአሰብንም ጉዳይ ያነሱ “ጦረኞች—“ ተባሉ-ለራሳቸውም መከፋፈል መሰረትን ጣሉ-ስንተ አመት?-ባጭሩ አረት አመታት ተሸመቱ። ሕዝብም አለቀ። ከወንጀልም ነጻ!!ያልጄርስን ውዝግብና የህዝብን “ድል አደረግን ሰልፍ ውጡን” ማሞኘት ጨምሮ።
ምርጫ-(ሶስት አማተት ከፊት -አራት አማታት ከሗላ)
ይህ በእንደዚህ እንዳለ ነብረ የ2005 ምርጫ አጀንዳ ሆኖ ሶስት አመት ከምርጫው በፊቱ -ሁለት አመት ከሁዋለው ሲያራኩት የከረመው። ባናሳው አምስት አመት። ከምርጫው ሶስት አመት አስቀድሞ፤ የምርጫ ቦርድን፤ ደንብና ህግን፤የሚዲያ አከፋፋልን፤ታዛቢ ወዘተ ወዘት፤ ምርጫ እንግባ አንገባም ሲባል ካለ በቂ ዝግጅትና የሁሉንም ፈቃደኝነት ባላካተተ መልኩ ወደ ምርጫ ዘው ተባለ። በጦርነቱ አንድ ሆነን ነበር እስኪ ተንፍሱ አይነት በተገኘችው ቀዳዳ የሕዝብ ድል ሲጠናቀቅ፤ በማግስቱ አሸንፌአለሁ ብሎ አውጆ ከዚየም ምድር ቀውጢ እንደሆነች አናስታውሳለን።
ነገሮች ተደማምረው አሁንም የሕዝቡ ድምጽ ይከበር በሚል አጀንዳ በተነሳ ውዝግብ ፤አስቀድሞም ሕዝብ እንዳለቀ፤ወደስር እንደተጓዘ ስናስብ አጀንዳዎችም መልክ እየቀየሩ አንደመጡ እናስተውላለን። ፓርላማ ለመግባት ቅድመ ሁኔታዎች ወዘተ። እዚህ ላይ ከሕዝቡ ድምጽ ይከበር ወደ ገዳዮቹ ለፍርደ ይቅረቡ ከዚያም የታሰሩት ይፈቱ የሚሉት ሁሉ በስርአቱ መሰሪነት የቀረቡ በየወቅቱ የሚፈለፈሉ የግፊት አጃንዳዎች እንጂ ሕዝቡ አስቦ ያቀዳቸው ጉዞዎች አልነበሩም። በቀላሉ አጀንዳዎች ተሰመሩለት።
የታሰሩት ይፈቱ-(አራት አመታት ሙግተ 2+2)
ይህ በዚህ እንዳለ አንድ ጊዜ ከታች ሕዝቡን ሁሉ እስር ቤት ለማስገባት ሞክሮ አንዳላዋጣው ሲረዳ፤ያሰረውን አስሮ አመራሩን በ አጠቃላይ ወደ እስር ሲከት ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ ተረስተው አገር ድፍን-አገር፤ ውስጥ ውጭ “የታሰሩት ይፈቱ” በሚል ሁለት አመት በላይ ሕዝብን በሙግት አጀንዳ ጸና። ምርጫው ተረሳ፤ድምጽ ተሰረቀ፤የተገኙትም ድምጾች ተነጠቁ፤ ነፍሰገዳይ በነጻነት ናኘ። አጀንዳ ተቀየረ።
የቅንጅት አመራርና ሕዝብ እስርቤት ባሉበት ጊዜ ነበር ድርጅቶችን መከፋፈል፤ ወደራሱ ማስጠጋት(ክሎኒንገ)አፋኝ ሕጎችን ማውጣት የተረፉትንም ድርጅቶች እንዳይነቀሳቀሱ ጠፍሮ የያዘበት ሁኔታ የተፈጠረው። የራሱንም ወንጀል አሳልፎ -ባገር ክህደትና -በዘር ማጥፋት ወንጀል ወዘተ አመራሩን ሌሎችንም ወነጀለ። ጩከቴን ቀሙኝ!-አሁን ማን አገርን እንደከዳ ማን ዘር እንዳጠፋ ሐቁ ገሀድ ሊወጣ!!
በጊዜው አጀንዳ ባጀንዳ እየለዋወጠ -ሲፈልገው ፍንጂ አፈንድቶ በማጯጯህ ሲያሰኘውም የፈጠራ ወሬውን እየደለቀ ለ2010 ምርጫ ከበቂ በላይ ዝግጅቱን አጠናቀቀ። በ2005 ስለ 2010 ምርጫ ማሰብ ወንጀል ነበር ማለት ማጋነን አይሆንም። የሶሟያ ጦርነት(ሁለት አመታት)
ድምጽ ሰረቆ፤ሕዝብን አፍኖ፤በቅንጅት አመራርና በሕዝብ መታሰር አገራቀፍና አለመቀፍ ውግዘት የተከናነበው የተንኮለ ስርአት በዚህ ወቅት ያደረገውና መዘንጋት የሌለበት ትልቅ ሸፍጥ-ቀልጠፍ ብሎ ከምእራቡና ተሰላፊዎቹ በበለጠ ግንባር ቀደም ሆኖ ሽብርተኝነትን እንዋጋለን ብሎ ወደ ሶማሌ መዝመቱ ነበረ። የሶማሊያም ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ሆነ! አንደገናም የብሔርን ስሜት ሊቀሰቅስ ሊያሰልፍም ሞከረ፤ሕዝቡ ተምሯልና ልጆቹም በእስር ላይ ናቸውና አልተሳካም። አላማና ውጤቱ ሲጤኑ-አላማው የታሰሩት እንዲረሱ ማዘናጋት ውጤቱ እልቂትና ውርደት ነበሩ። የገባበትን የወጣበትንም ታዝበላልና!። አገርን ካደጋ መከላከል ሌላ ወረራ ሌላ። የአገር ጉዳይ ሌላ፤ የሌሎችን ጥቅም በሕዝብ ልጆች ደም ማስከበር ሌላ። በወቅቱም የታሰሩት ለጊዜውም ቢሁን ተረሱ-ሁለት አመታትመ ተሰቃዩ። በሕዝብ ትግል ቢፈቱም የተነሱበትን አላመ አዳፍኖ ጥያቄው የህልውናና ከስር የመጀመር ጉዳየ ሆነ። እንደለመደው -በጎን ለሚቀጥለው እርምጃው ማውጠንተን መሸረቡን ቀጠለ።
በዚህ ወቅት ነበረ እህት ብርትኳንን ወደ እስር የሰደደዳት-ተከታይ አጀንዳ ይበሉ። ወ/ሮ ብርተኳንን ለማስፈታት እንዲሁ ሌላ ሙግት፤ እርሷን አፈነ፤ምርጫውም ደረሰ- እንደ ጩሉሌ ነጥቆ 99.6% ድል ተነገረ። ቤት ስራውን ጠንቅቆ በተገቢ ሠርቷል። ከስህተቱ ተማረ አምስ አመት ባፈና ደከመ፤ድሉን ነጠቀ አደባባይም ተደሰኮረ። አይን ያወጣ ፍጹም ለታሪክ ለተውልድ ለትዝብት የሚያበቃ ጭፍን ይሉኝታቢስ መሰሪነት።
ዘግይቶም ድርቅ ተከሰተ ብዙ ሙግት። በዚህም ህዝብን ለማትረፍ በሚደረገው ጥረት ዋና የተባሉ የሕዝብ የትግል መስመሮች ደብዝዘው ድርግቶች ታፍነው ተዳክመው- ደርግ ተቃዋሚዎቹን ጸት እንዳሰኘ -ለዚህም መሰሪ ስርአት አፈናው ሰራለት ትንሽ ተንፈስ አለ የተረፉትን ተቃዋሚዎች መለቃቀም ጀመረ።
ምንም የማያልቅበት ተንኮለኛ-ለስሙ መጠሪያ ግድብ ብሎ ተናሰ። ግድብ ሌላ አጀንዳ። ስንት አመት አለፈ በግድብ ሙግት። የሕዝቡ ልጆች ጸረ-ልማት የሆኑ ይመስል ካለአቅም በተጀመረው አወዛጋቢ የግድብ ስራ ብዙ ውጣውረድ ተነሳ፤ እስከ ውጭም ጎዳዩ ተዛምቶ የገንዘብ ቃርሚያው ተቃውሞ በዝቶበት አሁን ባለበት አለ።
ሞተ አለ፤
ሰውየው ታመመ-ሌላ አጀንዳ። ሞተ አለ ብዙ ወራት ተወራ፤ ይቀበር አይቀበር ብዙ ወራት፤ሙዝየም-ሙዚሊየም ነው ምንድር ነው ይገባል አይገባል አሁንም ሌላ ሌላ የሙግት አጀንዳ ——ፍጆታ።
የስልጣን ክፍፍል ሙግት፤
ትንሽ ቆይቶ የሰውየው እሬሳ ሳይደርቅ የስልጣን ክፍፍል ሙግት-አዲስ አጀንዳ። አዲሱ ሰው መጣ፤ አዲስ መነጋገሪያ ሆነ። ሰውየውም በስርአቱ ተጠፍሮ ለውጥ የውሀ ሽታ ብቻ ሳይሆን አራሱ የ“ራኢአይ/ቅዠት” አራማጅ ተብሉ ተኮፈሰ።
ይህ በዚህ እንዳላ ነበር ቀደም ብሎም ስርአቱን እንደ ግለሰብም እንደሺህም ሆነው ለመብት ለነጻነት ቆመው ሲታገሉ የነበሩት አነ እስክንድር–አንዱአለም ወዘተ-የታፈኑት የቀሩት ሸሹ-ሌላ አጀንዳ። አኔም አጃንዳ ማለቱ ደከመኝ፤አሰልቺ ነው። ከአንድ ወጥመድ ወደሌላ ወጥመድ ካንድ አዘቅት ወደ ሌላ አዘቅት-በተለያየ መለኩ። አሁንም ካለፈ ልምዱ -ብዙም መነጋገሪያና ተስፋ ሰጭም ባይሆን -የክልል ምርጫ ተባለ እንደተለመደው ተጠለፈ። ሐይማኖትንም በሚመለከት-ያመራሩንና ገዳማትነ አያይዞ ለብዙ ጊዛ ውጣውርደ እስካሁን እየቀጠለ ያለ መሆኑን ስንመለከት-ሌላው አነጋጋሪ የሐይማኖት ሙግት አጀንዳ እንደሆነ መጣዘብ መልካም ነው።
የሕዝብ ማፈናቀል፤
የሰውየውን ማጣጣር-ሞት አመላክቶ የሕዝቡ መነሳሳት ግልጽ በሆነበት ወቅት፤አደገኛ አካሄድ ቢሆንም -ለጊዜውም ሕዝብን በማንጫቻት የሰራላቸው አንድ አስከፊ ነገር ተከሰተ። ባገሪቱ አደገኛ አዝማሚያን የቀሰቀሰ ከሶስቱም ማእዘናት ሕዝብ ማፈናቀል። ሌላ መዘዘኛ አጀንዳ። በሔደቱም አዲሱ ሰው እግሩን ተከለ የመሰለውን መስሎ ወጣ። የመረጋጋት ስሜትን የፈጠሩ መሰላቸው ነገር ግን ምን ምሰው እንዳወጡ በቅጡ የተረዱት አይመስልም። በዚህም እስከዛሬ ሲያራምዱት የቆዩት የዘረኝነት ደባ ገሃድ ወጣ። አራስን የሚለበልብ አጀንዳ። ሟች ይህን እንዴት እንዳመለጠ ትዝብት ይወሰድ። ጭልጥ ያለች ውሸትን እወነት አድርጎ መናገር ይችልበት ነበር። በዚህም ከዚህ የቀደመውም የሕዝብ መሰረታዊ ጉዳይ ሁሉ ተረሳ።
ሙስና፤
አሁን ደግሞ የተያዘው አጀንዳ ሙስና ሆኗል። ሟቹ- የስርአቱ አማራማጆች በሙስና የተዘፈቁ መሆናቸውንና ከ50% በላይ ስለሆኑ መዋጋቱ አንደማያዋጣው ስለተረዳ -አልፎም ስርአቱ የቆመበትን ምሰሶ የሚያናጋ በመሆኑ ሳይነከው ተሰናበተ። የብልጠት አረማማድ ነበረ። የሚያዋጣውንና የማያዋታውን ያውቃል። አዲሱ ሰው ምን ውስጥ ተዘፈቀ? ሙስና የስርአቱ ስም እንጂ የአንድ ግለሰብ ወይንም የተወሰነ ባለስልጣን መስሪያቤት ችግር ብቻ አይደልም። ከሙስና ለመጽዳት ወይ 50ዎቹን ስርአቱ ይጨርስና ለሕዝቡ የቀረውን ይሰጥ ወይም ይሰናበቱ። እዚህ ላይ ምን ተረሳ -የሕዝብ መፈናቀል። ጥሩ ሙከራ።
ይህን ስርአት ከሙስና አጸዳለሁ ማለት ዘበት ከዘበትም ዘበት ነው-አያችሁ አጀንዳ -በል በል የሚያሰኝ፤ አጀንዳ ማለት ይህች ነች።በተግባር።
ይሀን ሁሉ ሲያደርግ ሶስት አነኳር ቁም ነገሮች መጠቀስ አለባቸው። ለዚህ ሁሉ -አላማው ግልጽ ነው፦
1. ማዘናጋት-አላማን ማሳት፤
2. ከተጠያቂነት ማምለጥ-በእያንዳንዱ አጀንዳን መቀያየር ከስንት ወንጀልና ተጠያቂነት እንዳመለጠ ግልጽ ነው፤
3. ተቃዋሚን /ሕዝብን ማዳከም፤
4. ፈጥኖ ጥቅምን ማግበስበስ፤
5. ብሎም የስልጣን እድሜን ማራዘም። ከሆነው ሁሉ፤የቱ እንተሳካለትና የቱ እንደከሸፈበት አንባቢው ይፍረድ።
እንዲህ እንዲህ ሲል ነበር 22 አመታት ሕዝብን ሲሞገግት ሲመሰጥር ሲያምስ የከረመው። መቃወምም አጀንዳ ሆነ- ሁሉም የታየውን ዘርዘር አድርጎ ማስቀመጥ ሀላፊነት አለበት- በዚህ ረገድም ብዙ ተብሏል። ባንድ መልኩ የስርአቱ ምንነት የተረጋገጠው ይህን ንቅዘቱን በማጋለጥ ረገድም ነበር፡
ለማጠቃለል ከዚህ ምን እንማራለን? በዚህችው በመጨረሻ የእስትንፋስ ጊዜው፦
1. የ ስርአቱን አዘናጊ አጀንዳ ጠንቅቆ መረዳት፤
2. ይህ ያንተ አጀንዳ እንጂ የሕዝቡ አይደለም ማለት፤ አለማጀብ፤በመንገዱም አለመሔድ፤ማምከን፤
3. ትኩረት ባለው የሕዝብ አጀንዳ ላይ መንቃሰቀስ፤
4. የህዝብን የመሰረታዊ የዲሞከራሲ፤የነጻነት፡የመብት ጥአቄዎችን፤የአገርን ሉአላዊነት አንድነትና ዘላቂነት የሚመለከቱትን ጉዳዮች በማጉላት-የለውጥን ባቡር ጉዞ ማፋጠን።
ከዚህ -ከምናውቀው ከተማርነውና ካስተዋልነው አንድ ተጨማሪ ግንዘቤ እንደወሰድን ይገመታል። በዚህም የስርአቱን የወደፊት አጀንዳ አስቀድም መተንበይ ይቻላል። በሚገርም ሁኔታ የ2015 ምርጫን አንስተው ሕዝን ሊያንጫጩ እንደሚሞክሩ መገመት አያዳግትም። አንድ ታምር -እንበለውና- አንድ ነገር ካልመጣ ስርአቱ እንዲሁ በድኑን እየተንቃሰቀሰ፤ ሙቱን አየተንገዳገደ፤ አደጋ አያንዣበበበት እዚያ ሊደርስ አንደሚሞክር መገመት አያዳግትም። ለነገሩ መሰሪነት ጨርሳ ባትጠፋም ሳትሞት አልቀረችም። ለእነርሱም ሰዎች -ጊዜአቸው
አስቀድሞ ያበቃ፤ በተዋሰ ጌዜ እንደሚንቀሳቀሱ፤ ጊዜና ሕዝብ እንደከዳቸው ሀይልም ትምክህትም ሸፍጥም አንደማያዋጣ ቢረዱና መንገዳቸውን ቢፈልጉ ከባሰ ሁለገብ ቀውስ መዳን ይሆናል ።
ይህም ሆኖ በየወቅቱ አዘናጊና አደናቃፉ አጀንዳዎች ቢደቀኑበትም -ሕዝቡ እንደተባለውም፦
በሰራው ወጨፎ በሰራው እርሳስ፤
ጥልያን ጠፈጠመ ዳግመኛ እንዳይደርስ!
ብሎ በገዛ አጀንዳው እተመታና እፍረትን ውርደትን እየተከናነበ እዚህ የድል ምእራፍ ላይ እንደደረሰ መጠቀስ አለበት። ሕዝቡ ምንጊዜም ባለድን ነው። ሕዝብን ዘለአለም ለማታለል መሞከርና -ለጊዜውም ቢሆን- ተላላነት ነው።
ለማጠቃለል-የኤርትራ ጦርንተ ተባለ ትረፉ እልቂት፤ውርደት። የአልጄርስ ስምምነት ድለ ነሳን ተባለ ባዶ ኳካታ ውርደት። ምረጫ ተባለ ሽንፈት። ወደእስር በሐሰት ክስ የገቡትመም ተፈቱ–ውርደት። የሶማሌ ጦርነትም ትረፉ እልቂት-ያለቀው ቁጠሩ እነኳ ሳይነገር-አሊ-ሽባውም አግር አውጠቶ ተጠናከሮ ጦርነቱን ቀጠለ። ድርቅ ተከሰተ-ድርቅና ረሃብ የቋንቋ አቃቂር መጣ-አንድም ሰው አልሞተም-ተባለ በቅርቡ በሶማሊያ ከ260፣000 ሕዝብ በላይ ማለቁን ተነገረ። አሁንም የምስራቁ ኢትዮጵያ ጉድ ተዳፍኖ አለ-ትልቅ መጪ ውርደት። ዳግም ምርጫ ተባለ-99.6% ውርደት። ሰውየው በሕይወት አለ ሲባል ተከረመ-ሰውየውም ሞተ። የሕዝብ ማፈናቀል ተሸረበ-የባሰ ውርደት የዘረኝነት ሴራ መጋለጥ። አሁን ደግሞ ሙስና ተባለ-ሲወተወት የነበረው የስርአቱ በዝርፊያ መንቀዝ በራሱ ኮሚሽን ይፋ መውጣት የባሰ ዝቅተት። ብዙ ሊጻፍ ሊነገር ይቻላል። ሕዝቡ ስርአቱን በአጀንዳው ካጠናቀቀው፤በራሱ አጀንዳ ቢራመድ ምንኛ የመከራው ጊዜ ባጠረች። ይህም ሲባል በሕዝቡ አጀንዳ ላይ ሳያሰልሱ ሲታገሉ በመጨረሻም የተናገሩት እውነት መሆሉን በተግባር በብቃት ያስመሰከሩ ብዙዎች እንዳሉ መጠቀስ አለበት።
ለቀባሪው አረዱት አይሁንና-ቁምነገሩ ሕዝቡ በስርአቱ አጀንዳ ሳይሆን በራስ አጀንዳ ስር መንቃሰቀስ አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን ማመልከት ተገቢ ነው። ስርአቱ ከእንግዲሕ የቀረው የቅዠት አጃንዳ ብቻ ነው። በዚህ መሄድ ደገሞ -በሌላው ቅዠት መቃዠት ነው የሚሆነው! ከእንግዲህም ቀልጠፍ ብሎ -አጀንዳህ ምድረ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል። አግባብነት ያለው ተመራጭ አጀንዳ-የተባበረ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ነው ቢባል ተገቢ ይሆናል! አጀንዳዎችን አጥንቶ መጓዝ ተገቢ ነውና!! እንቅስቃሴውም -ሲፈለግ የነበረውን አንድነት ቅንጅትና ሕብረት ሊያመጣ ይችላል።አንድነት ለእንቅስቃሴ፤እንቅስቃሴም ለአንድነት።
አጀንዳን እያስቀደሙ ማዘናጋት ከተጠያቂነት አያድንም!!!
ኢትዮጵያ በእግዚአብሔርና በጠንካራ ታጋሽ በሕዝቧ ተጠብቃ ትኑር!

የሰማያዊ ፓርቲ ለጠራው ሰልፍ ዝግጅት እያደረገ ነው



የሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት ፅ/ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥሪ ባስተላለፈው መሰረት አመራሮቹ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆኑ ገለጹ።
Ethiopian blue party, semayawi partyርቲው “በመንግስት ምላሽ የተነፈጓቸው ጥያቄዎቻችን የዓለም ዓቀፍ ማሕበረሰብን ትኩረት የሚያገኙበትን መንገድ ለመፈለግ…” በሚል ባስተላለፈው የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚከበረውን የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ሐገራትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች በሚገኙበት ድምፃችንን ለማሰማት ከግንቦት 15 – 17 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ጥቁር ልብስ በመልበስና ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ፅ/ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ያነሳናቸው ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ የሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሲቪክ ማህበራትና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በእነዚህ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ” ሲል አሳስቧል።
ይህ በዚህ እንዳለ በፌስቡክ፣ ፓልቶክና ሌሎችም የማህበራዊ መገናኛ መረብ (social media) ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን ለተጠራው የሰላማዊ ሰልፍ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ፎቶዎቻቸውን በጥቁር የሰው ምስል በመቀየር ድጋፋቸውን እያሳዩ ሲሆን የፓልቶክ መወያያ መድረክ ታዳሚዎች ደግሞ ጽሁፎቻቸውን በጥቁር ቀለም በመቀየር ሰማያዊ ፓርቲ ጥቁር ልበሱ ሲል ያስተላለፈውን መልዕክት ተግባራዊ እያደረጉ ነው።
እስካሁን ከገዢው ፓርቲ አካባቢ የተጠራውን የሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ የተባለ ነገር የለም።
የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ሰላማዊ ሰልፈኞች ቀደም ብለው ስለ ሰላማዊ ሰልፋቸው እንዲያሳውቁ የሚደነግግ ሲሆን። የግድ ፈቃድ መጠየቅ እና ማስፈቀድ አለባቸው አይልም።

ግንቦት 7 – ታሪካዊ ቀን በክፍሉ ታደሰ -(ግንቦት 7 /ኢትዮጵያ፤ እኮ ለምን? እንዴት?/ ከሚለው መጽሐፍ የተቀነጨበ


ginbot-7--በግንቦት 7/1997 ምርጫ 524 የምክርቤት ወንበሮች ለምክር ቤት ቀረቡ፡፡ 23 የሚሆኑት በነሐሴ ወር በሱማሌ ክልል ለሚደረገው ምርጫ ወደጎን ተተዉ፡፡
ግንቦት 7 በተካሄደው ምርጫ ተሳትፌያለሁ፡፡ ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ እንደሚባለው ያየሁትን፣ የሰማሁትን፣ የተሳተፍኩበትን ነው የማቀርበው፡፡ እኔ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ በሦስተኛ ሰው አድርጌ ታሪኩን ላቀርበው ሞክሬ፤ ራቀብኝ፣ ባዕድ ሆነብኝ፣ የኔ መስሎ አልሰማህ አለኝ፡፡ እናም ታሪኩን በቀጥታ ለመተረክ ወሰንኩ፡፡
ግንቦት 7/1997 ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከቤቴ ወጥቼ ወደምርጫጣቢያ አመራሁ፡፡ ከምኖርበት ሰፈር ወደምመርጥበት ጣቢያ ለመሄድ ከ15 እስከ 20 ኪ.ሜ. መንዳት ነበረብኝ፡፡ በጠዋት የተነሳሁትም አንድም ቀደም ብዬ ከመረጥኩ በኋላ ከተማውን ተዘዋውሬ ለማየት እንዲረዳኝ በማሰብ ነበር፡፡ ዘጠኝ ኪሜ ያህል ተጉዤ መገናኛ አካባቢ ስደርስ ከአንድ የምርጫ ጣቢያ ፊትለፊት ረዥም ሰልፍ አየሁ፡፡ መኪናዬን ትንሽ ቆም አድርጌ ሰልፉ ምን ያህል ረዥም እደሆነ ለመቃኘት ሞከርኩ፡፡ ሰልፉ እየተጠማዘዘ ቢያንስ 300 ሜትር የሚያክል ቦታ ይዟል፡፡ የተሰለፈውን የሰው ዓይነት ለማየትም ሞከርኩ ዝንቅ ነበር፡፡ ወንድ/ሴት፣ ትልቅ/ትንሽ፣ ወጣት/አዛውንት ሁሉም በትዕግስት ተሰልፈው ይጠብቃሉ፡፡ እንዴት በጥዋት ሊነሱ ቻሉ ብዬ እያሰብኩ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ መገናኛ አደባባዩጋ ስደርስ ወደሰሜን አቅጣጫ ወደሚወስደው መንገድ ወደቀኝ ታጠፍኩ፡፡ ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ ወደሚወስደው መንገድ፣ በድሮው አጠራር ወይዝሮል ወደሚባለው መንገድ ወደሚያስገባው አደባባይ ደርሼ ወደግራ ታጠፍኩ፡፡ ከዚህ ቦታ ጀምሮ ምርጫ የማደርግበት ሰፈር እስከምደርስ ድረስ ስድስት ወይም ሰባት የምርጫ ጣቢያዎች አየሁ፡፡ ሁሉም ቦታዎች እጅግ በጣም በርካታ ሰዎች ተሰልፈው በትዕግስት ይጠባበቃሉ፡፡ እንደዕንቁ ጠብቀው ያቆዩት የምርጫ ካርዳቸውን ከሳጥናቸው ለመጨመር በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡
መጀመሪያ እንዳየሁት የምርጫ ጣቢያው ሁሉ ሌሎች ቦታዎችም የተሰለፉት ዓይነት ተመሳሳ ነበር፡፡ ሰው በምርጫው ለመሳተፍ የነበረው ፍላጎት አስገረመኝ፡፡ ረዥም ዘመን በፖለቲካ ትግል ውስጥ ብቆይም ይህን የመሰለ አጋጣሚ አይቼ አላውቅም ነበርና ጥቂት ወራት ወደኋላ ተመልሼ የነበረውን ሁኔታ ለማስታወስ ሞከርኩ፡፡ ምርጫው ሲታወጅ ለመንግሥትም ሆነ ለተቃዋሚ ድርጅቶች አሳሳቢው የነበረው ሒደት ሰው በፖለቲካ ሒደቱ ለመሳተፍ ፍላጎት እያጣ በመሄዱና ተስፋ በመቁረጡ ለምርጫው መመዝገብ ብዙም ፍላጎት ያልነበረው መሆኑ ነበር፡፡ በዚህ የመጀመሪያ ወቅት የመንግሥት፣ የሲቪል ድርጅቶችም ሆነ የተቃዋሚዎቹ ዋና ሥራ ሰው እንዲመዘገብ መቀስቀስና መወትወት ነበር፡፡ በብዙኃን መገናኛ እና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰፊ ቅስቀሳ ሲካሄድ ቆየ፡፡ በቂ ሰው ሊመዘገብ ባለመቻሉ፣ የምዝገባው ጊዜ ሊራዘም ችሏል፡፡
የምርጫው ሒደት ከተጀመረበት መስከረም 1997 ጀምሮ ምዝገባው እስከተገባደደበት እስከ የካቲት 6 ድረስ የሁሉም ተቋማት ርብርብ በምርጫ ምዝገባው ላይ መሆኑ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ሌላ ቦታ እንደተጠቀሰው በኢሕአዴግ ዘመን ከ1997 በፊት ብቻ ወደ ስምንት የሚጠጉ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ ሕዝቡ ምረጥ እየተባለ በምርጫዎቹ ተሳትፏል፡፡ ከምርጫዎቹ በኋላ ለውጥ ሲመጣ አላየም፡፡ እናም ለምርጫ ለምን እንደሚቧግት ሊገባው አልቻለም፡፡ ምን አደከመኝ ለውጥ ላይመጣ እያለ ተስፋ እየቆረጠ ሄዷል፡፡ ምርጫ ከንቱ ድካም እንደሆነ ተረድቶ ካልተገደደ በቀር ለመሳተፍ ፍላጎት አልነበረውመ፡፡ ሕዝቡ ፈለገም አልፈለገ፣ ወደደም ጠላ መረጠም አልመረጠ ውጤቱ ገና ከወዲሁ ስለሚታወቅ አብዛኛው ሰው ምን አታከተኝ ብሎ ላለመሳተፍ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ ገዢው ፓርቲ ሁልጊዜም አሸንፌያለሁ እንደሚል ይረዳል፡፡ ገዢው ፓርቲ በሕዝቡ ቡራኬ የሥልጣን ዘመኔን አራዝሜያለሁ እንደሚል፣ ቀደም ሲል ጀምሮ ያውቀዋል፡፡ ሕዝቡ ይህንን ቡራኬ ለምን መስጠት እንዳለበት፣ ለምንስ ጉልበቱንና ጊዜውን እንደሚያባክን አልገባህ ስላለው ምርጫን የመድረክ ተውኔት አድርጎ ራሱን ማግለል እንዳለበት ወስኖ ቆይቷል፡፡
ለ1997 ምርጫ መንግሥትና የመንግሥት ደጋፊዎች ብቻ ሕዝቡን ለምርጫ እንዲሳተፍ ቢጠይቁት ኖሮ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ጥሪያቸውን ባልተቀበለ ነበር፡፡ ይሁንና ጥሪውን ከተቃዋሚዎችም አንደበት በመስማቱ ተመዘገበ፤ ለማንኛውም ካርዱን ልያዝ የሚሆነውን አያለሁ አለ፡፡ ወደኋላ ላይ እንደምናየው የምርጫ ውድድሩ መልክ እየያዘና እውነተኛ ፉክክር እየታየበት ሲሄድ ካርድ ያላወጡ ብዙ ሰዎች ለማውጣት ወሰኑ፡፡ ይህ የሚሆነው ከየካቲት 1997 በፊት ባለው ጊዜ ሲሆን ከዚያ በኋላ በነበረው ሒደት የተቃዋሚዎችና የገዢው ፓርቲ ክርክር ብዙዎችን ቢማርክም ጊዜው በማለፉ የምርጫ ካርድ ለማውጣት ቢፈልጉም ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡ ካርድ ባለማውጣታቸው የተፀፀቱ በርካታ ናቸው፡፡
ወደምርጫ ሒደቱ መለስ ልበልና ምርጫ የማካሄድበት ሰፈር ደርሼ ሰልፍ ያዝኩ ተራዬ እስከሚደርስ ባልሳሳት ሦስት ሰዓት ያክል ተሰለፍኩ፡፡ ቆይታዬን አልጠላሁትም፡፡ ብዙ እንድታዘብ ረዳኝ፡፡ የሕዝቡ አንድ አካል መሆኔ ተሰማኝ፡፡
የምርጫ ካርዴን ለማስገባት ተሰልፌ በነበረበት ወቅት ከኋላዬ ተሰልፈው የነበሩ አንዲት ሴት ደግመው ደጋግመው ይናገሩት የነበረው ነገር አስገረመኝ፡፡ ስለምርው ሥነስርዓት፣ ፎርሙ እንዴት መሞላት እንዳለበት፣ ምልክት እንዴት እንደሚደረግ፣ ፎርሙ እንዴት እንደሚተጣጠፍ፣ ወዘተ ቀበሌውን ወክላ አንዲት ሴት ታስረዳለች፡፡ ስለምርጫው ከማስረዳት በስተቀር ምንም የምታደርገው ነገር አልነበረም፡፡ ሴትየዋ የጠራ አማርኛ አትናገርም፡፡ አፏን ያዝ ያደርጋታል፡፡ ይህች ሴት ከቀበሌው ውስጥ ምን ሥልጣን እንዳላት አላውቅም፡፡ ከሌላ ቦታ የመጣች ትሁን አትሁንም ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ከኋላዬ የተሰለፉ አንዲት ሴትዮም ይወቋት/አይወቋትም አላውቅም፡፡ ብቻ ያስገረመኝ ሴትየዋ በተናገረች ቁጥር ‹‹ሰላቢ›› ይላሉ፡፡ አንዲት ቃል ናት የሚተነፍሷት፡፡ ‹‹ሰላቢ››፡፡ ዞር ብዬ ሴትየዋን አየኋቸው፡፡ ደርበብ ያሉ የቤት እመቤት ናቸው፡፡ ለምን ሴትየዋን እንደጠሏት ልረዳ አልቻልኩም፡፡ የግል ፀብ ይኑራቸው አይኑራቸው፣ ወይም ሌላ ምክንያት እንዳላቸው የማውቀው ነገር የለም፡፡ ምን በደለችዎት እና ነው የሚሰድቧት ብዬ ለመጠየቅ ዳዳኝ፡፡ አንተስ ማነህ፣ ምናገባህ ቢሉኝ አልኩ፡፡ ብቻ ድፍረት አጣሁና ጥያቄዬን ውጬ ቀረሁ፤ በጉዳዩ ላይ ትንሽ አብሰለሰልሁ፡፡
ምርጫ ያደረግኩበት ሰፈር ውስጥ አብዛኛው ነዋሪ የአማርኛ ተናጋሪ ሲሆኑ፣ በንግድ ሥራ የተሰማሩ በርከት ያሉ ጉራጌዎች አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ከሰፈሩ ትንሽ ከፍ ብሎ በሸማ ሥራ የሚተዳደሩ ጋሞዎች ይገኛሉ፡፡ ሁኔታው ይህ ሆኖ ሳለ የቀበሌው ሊቀመንበር ትግርኛ ተናጋሪ ናቸው፡፡፡ ምናልባትም የሕወሓት አባል ይሆናሉ፡፡ ስለሌሎቹ የቀበሌው ባለሥልጣናት ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ እነዚህ ሐሳቦች በአእምሮዬ ላይ ብልጭ አሉ፡፡ ከሴትዬዋ ድርጊት ጋርም ላዛምዳቸው ሞከርኩ፡፡ ጉዳዩ የትም ሊወስደኝ የማይችል ስለሆነ ብዙም አልቆየሁበትም፡፡ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማተኮር ጀመርኩ፡፡
በምርጫ በተሰለፍኩበት በዚህ ወቅት ብዙ ነገሮችን ታዘብኩ ተማርኩ፡፡ ሲፈልግ ሕዝቡ ሥነስርዓት ከሚገባው በላ ያከብራል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ምርጫው የግሉ አድርጎ ስለወሰደ እንዳይበላሽ ከመንገዱ ወጣ ብሎም እንኳን ሊያስተካክል ይሞክራል፡፡ ሰው ለምርጫ ሳይሆን ለሠርግ ወይም ለሌላ ዓመት በዓል የተጠራ ነበር የሚመስለው፤ ደስተኛ ነበር፡፡ ወጣቶቹም ያ ያልተፈጠረባቸውን ትዕግስት ከየት እንዳገኙት አላውቅም በጨዋነት ተራቸውን ይጠባበቃሉ፡፡ ብዙ እናቶች ተሰልፈዋል፡፡ እጃቸው ባዶ ነው፡፡ ካርዳቸውን አልያዙም እንዴ ብዬ ሳስብ፣ አንዳንዶቹ ከጡታቸው ስር እየመዘዙ ሲያወጡ አየሁ፡፡ ለካርዳቸው የሰጡት ዋጋ ከፍ ያለ መሆኑ አስገረመኝ፡፡ አዛውንቱ ይህንን ያለምክንያት አልነበረም፡፡ የተቃዋሚዎች ክርክር እየበረታ ሲሄድ ኢሕአዴግ ካርዶች እየገዛ ነው ተብሎ በከተማው ስለተወራ አዛዋንቱ ለጥንቃቄው ያህል ያደረጉት ይሆናል ብዬ ገመትኩ፡፡
ከወለደች 15 ቀናት ብቻ ያስቆጠረች አራስ ልትመርጥ መጣች፤ ታመን ከመጣንበት ተነስተን መጣን የሚሉ በሽተኞች፣ መሄድ ያቃታቸው ሽማግሌዎች፣ ወዘተ ሲመርጡ ማየት አስገራሚ ነበር፡፡ ከምርጫው በፊት በሥራ ጉዳይ ከሀገር መውጣት ነበረብኝ፡፡ ይሁንና በሕይወቴ የመጀመሪያ በሆነው በዚህ ምርጫ መሳተፍ አለብኝ ብዬ መወሰኔ አስደሰተኝ፡፡ ለረዥም ዘመን ጠፍቶብኝ የነበረው ደስታ ተመልሶ ወደሰውነቴ ሲገባ ታወቀኝ፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ላገኘውና በቃላት ልገልጸው የማልችለውን ስሜት አገኘሁ፡፡ ይህ ስሜት ምን እንደሚመስል ማወቅ በራሱ ፀጋ ነው ብዬ አልኩ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብዙ ዘመናት የታገለለት መብቱ ሊከበር ይሆን ብዬ እጅግ ደስ አለኝ፡፡ እኔ ያየሁትን እና የሰማሁትን ከጎኔ ያየሁትንና የሰሙትን ከ30 ዓመት በፊት ከጎኔ የነበሩ ጓደኞቼ ምነው በነበሩ ብዬ ተፀፀትኩ፡፡ የወደቁለት ዓላማቸው መሳካቱን ምነው ባዩ  ብዬ አሰብኩ፡፡ በዚህ መሐል ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ለፍርድ ቀርበው የሞት ፍርድ ሲፈረድባቸው ተናገሩ የተባለው ቃል ትዝ አለኝ፡፡ ‹የዘራችሁት ፍሬ ማሸት ጀምሯል›  ብለው ያሉት፡፡
ሕዝቡ እጅግ ሰላማዊ ከመሆኑ የተነሳ ለጥበቃ የተመደቡት ፖሊሶች ደከማቸው መሰለኝ ቁጭ አሉ፡፡ ወደሰልፈኛው ብዙም ትኩረት አያደርጉም ነበር፡፡ ብቻ አልፎ አልፎ አንዳንድ ወጣቶች ሰልፍ ጥሰው ወደፊት ሲሄዱ በዓይናቸው ይከታተሏቸዋል፡፡ ወጣቶቹ ከቤተሰቦቻቸውጋ ከተወያዩ በኋላ ወደነበሩበት ይመለሳሉ፡፡ ሥራዬ ብዬ ወጣቶቹን ስከታተል ያልተማሩ እናቶቻቸውን እንዴት መምረጥ እንዳለባቸው ለማሳሰብና ለማስረዳት ነበር የሚመጡት፡፡ ወጣቶቹ ሥራቸውን ካከናወኑ በኋላ ምልስ ይላሉ፡፡ ወጣቶቹ ለቤተሰባቸው የማስረዳት ኃላፊነት ሊወስዱ የቻሉት በምርጫው ወቅት ገዢው ፓርቲ ያልተማሩ ሰዎችን ሊያጭበረብር ይችላልና ጥንቃቄ አድርጉ የሚል ማስታወቂያ ለተቃዋሚ ኃይሉ በተደጋጋሚ ስለተሰጠ ሊሆን ይችላል፡፡
ግንቦት 7/1997 -  25,605,851 የሚሆን ሕዝብ በመራጭነት እጅግ በርካታ የሚሆን ደግሞ በተባባሪነትና በደጋፊነት ሲፍነቀነቅ ዋለ፡፡ ግንቦት ሰባት አንድ ነገር ይዛ ትመጣ ይመስል ሰው ደስታ በደስታ ሆነ፡፡ ሕዝቡ ግንቦት ሰባት የነገ ብርሃንን አብሳሪና በጫንቃው ተሸክሞ ከሚዞረው ችግር የምታላቅቀው ቀን አድርጎ ነበር የተመለከታት፡፡ በጥቅሉ ግንቦት ሰባት በሚሊዮኖች የሚቆጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ የሠርግ ታዳሚ ሆኖ የዋለበት ቀን ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ግንቦት 7 በቁምነገሯ ብቻ ሳይሆን ብዙ ገጠመኞችና ቀልዶች የተስተዋሉባት ቀንም ነበረች፡፡ ብዙዎቹ ገጠመኞች ስለምርጫው ሥነስርዓት ኅብረተሰቡ በተለይም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ያላቸው ግንዛቤ ዝቅ ያለ በመሆኑ ምክንያት የተፈጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ገጠመኞች አንድ ሰሞን አነጋጋሪ በመሆናቸው በግል ጋዜጦች ጭምር ሲወጡ ከርመዋል፡፡ በየትኛው ጋዜጣ ላይ እንደሆነ አላስታውስም፡፡ አንድ አዛውንት ሰልፈኛ ወደቆመበት ይሄዱና ‹‹የቅንጅት ሰልፍ የትኛው ነው?›› ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሁሉም ሰው አንድ ቦታ ነበርና የተሰለፈው ሰው ሳቀ፤ አዛውንቷ በየዋሕነት ወይም ባለማወቅ ማንን ሊመርጡ እንዳሰቡ አሳወቁ፡፡ ሰውን ያሳቀው ይህ የአዛውንቷ የዋሕነት ነበር፡፡ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ስለተፈፀመ አንድ ሁኔታ ሰው ሲያጫውተኝ አዛውንቷ ፎርሙ የሚሞላበት ክፍል ውስጥ ብቻቸውን ከቆዩ በኋላ ከዚያ ወጥተው ሳጥኑ ወዳለበት ክፍል ይሄዳሉ፡፡ ዞር ዞር ብለው ሲመለከቱ አንድ ሳጥን ብቻ ነው የተቀመጠው፡፡ አንድ ሳጥን ብቻ ነው የተቀመጠው፡፡ አካባቢያቸውን ቢቀኙም ሌላ ሳጥን ሊያዩ አልቻሉም፡፡ ወደአስተባባሪዎቹ ዘወር ብለው ‹‹የቅንጅት ሳጥን የትኛው ነው?›› ይላሉ፡፡ ሰዎቹ ግራ ተጋብተው ዝም ብለው ‹‹እሱ ሳጥን ውስጥ ይጨምሩ›› ይሏቸዋል፤ ሴትየዋ ይናደዳሉ፡፡ ደግመው ‹‹የቅንጅትን ነው እኮ ያልኩህ!›› ይላሉ ወደአንደኛው ዘወር ብለው፣ ሰውዬው መልስ ቢሰጣቸውም ሊያምኑት አልቻሉም፤ ተቆጡ፡፡ ተናገሩት፡፡ ኋላ ላይ ሌሎች ባለሥልጣናት እና የተሰለፈው ሕዝብ ካረጋጋቸው በኋላ ካርዳቸውን ሳጥን ውስጥ ከትተው ሄዱ፡፡
ከላይ የዘረዘርኩት የእኔ ገጠመኝ እና በአንድ የምርጫ ቀጠና የታዘብኩት የሕዝቡ ተሳትፎ በመላ ሀገሪቱ ሁሉ ተፈፅሟል፡፡ የሕዝቡ ትዕግስት ድንበር አልነበረውም፡፡ በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ችግር ያልነበረ ሲሆን ችግር የተፈጠረባቸው አንዳንድ ቦታዎችም አልጠፉም፡፡ አቶ ኃይሉ ሻወል ‹‹የአዲስ አበባ ምርጫ እየተጭበረበረ ነው›› በማለት ሒደቱ ሳይጠናቀቅ መግለጫ ቢሰጡም ምርጫ ከሞላ ጎደል በጥሩ ሁኔታ ነበር የተጠናቀቀው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ‹‹ከበድ ያሉ ሕገወጥ አሠራሮች የታዩት በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ሲሆን መታወቂያ ያለማየትና ለምርጫ ያልደረሱ ወጣቶች ሲመርጡ ተስተውለዋል፡፡›› ይላል በታዛቢነት የተሳተፈው የካርተር ማዕከል፡፡ እንደካርተር ማዕከል በምርጫ ቀንም ሆነ ከዚያ በኋላ የማስፈራራት እና የማስደንገጥ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ የምርጫ ሳጥኖች ያለአግባቡ ከቦታቸው ተነስተዋል፤ ወይም ዋስትና ባለው መንገድ አልተቆለፉም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች በምርጫ ጣቢያዎች እንዳይገኙ ወይም በቆጠራው ላይ እንዳይኖሩ ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ የግንቦት 7/1997 ሕብረ-ብሔራዊ ምርጫ በኢሕአዴግ የ14 ዓመት አገዛዝ እና ይከተላቸው በነበራቸው ፖሊሲዎች ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ ያደረጉበት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያደረጉበት እውነተኛ ምርጫ ነበር፡፡

አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ኢትዮጵያና የአፍሪካ አንድነት/ኅብረት



Haile Selassie was known as a child as Lij Tafari Makonnen
‹‹ኢንሳክሎፒዲያ ብሪታኒካ›› ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ ባቀረበው አጠር ያለ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹Haile Selassie played a very important role in the establishment of the Organization of African Unity in 1963.››
ዕለታዊው የአዲስ ዘመን የወርኻ ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም ዕትሙ በፊት ለፊት ገጽ ላይ፣ ‹‹ሠላሳ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ጉባኤ በአፍሪካ አዳራሽ ተከፈተ፡፡ ግርማዊ ጃንሆይም የጉባኤው የክብር ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመረጡ፡፡›› በሚል ዐቢይ ርዕስ ዜናና ሰፊ ሐተታን ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡
የሰኞ ማለዳው የግንቦት 19 ቀን 1955 ዓ.ም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ደግሞ በርእሰ አንቀጹ፣ ‹‹የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ የሌሎችንም ብሎኮችና ቻርተሮች ሠርዞ የአፍሪካ አንድነትን የሚመሠርተው ‹የአፍሪካና የማላጋሲ አገሮች ድርጅት ቻርተር› ግንቦት 17 ቀን ለግንቦት 18 ቀን አጥቢያ 1955 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ በአፍሪካ አዳራሽ ውስጥ ተፈርሟል፡፡ በአራቱ ቀን ጉባኤ ፍጻሜ አዲስ የአፍሪካ ታሪክ፣ አዲስ የዓለም ታሪክ ተጽፏል፣ ተመዝግቧል፡፡›› ሲል የምስራቹን ዜና አስነብቧል፡፡
የትላንትናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት የ50ኛ ዓመቱን የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን በተለያዩ አገር አቀፍና አኅጉር አቀፍ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅቱን ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ግንባር ቀደም ሚና ባላትና ታላቅ አስተዋጽኦ ባደረገችው፣ የኅብረቱም ዋና መቀመጫ በሆነችው በአገራችን ኢትዮጵያ የበዓሉን ዝግጅት የደመቀና ልዩ ለማድረግ ሽር ጉድ እየተባለ ነው፡፡
ይህን በዓልም ባማረና በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ራሱን የቻለ የበዓል ዝግጅት ሴክረታሪያት ቢሮ ተቋቁሞ፣ የአፍሪካ ኅብረት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በዓሉን ዓመቱን ሙሉ ለማክበር፣ የተለያዩ ዝግጅቶችን ቀርጾ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ አይተናል፣ ሰምተናል፣ አውቀናልም፡፡
ከወራት በፊትም በመዲናችን በአዲስ አበባ ዋና ዋና ቦታዎችና አደባባዮች ላይ ‹‹I am African. I am the African Union›› የሚሉ የአፍሪካ ሕዝቦችን ማንነት፣ ታሪክ፣ ቅርስና ባህል የሚያንጸባርቁ፣ የአፍሪካዊነትን ስሜት፣ ኩራትና ወኔ የሚቀሰቅሱ ፖስተሮችን አይተናል፡፡ ከዑራኤል ወደ እስጢፋኖስ በሚወስደውም መንገድ ላይም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ያቋቋሙ የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ የሆኑ አባቶች ምስልም በትልቁ ተሰቅሎ አይቻለሁ፡፡ ይህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መልካም ሊባል የሚችል ነው፡፡
ለወደፊቱም በዓሉ በተለያዩ መጠን ሰፊ በሆኑ ዝግጅቶች እንደሚከበርና በበዓሉም ላይም የአፍሪካ አገራት ርዕሳነ ብሔራት፣ ተወካዮችና ባለ ሥልጣናት፣ ዓለም አቀፍ መሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለ ሙያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ደራሲያን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች … ወዘተ በሚሳተፉበት በደመቀ ሁኔታ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የበዓሉ ዝግጅት ኮሚቴ በተደጋጋሚ አሳውቋል፡፡
በዚህ ጽሑፌ ከሰሞኑ መላው አፍሪካና አፍሪካውያን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና እንዲሁም በአጠቃላይ የአፍሪካ ወዳጆች፣ የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የተለያዩ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ታዋቂ ሰዎች አብርውን በደስታ ሊያከብሩት እየተዘጋጁ ስላለው የአፍሪካ ኅብረት የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ስናወራ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ፡፡
ይኸውም በዚህ በዓል ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን ትልቅ መሥዋዕትነት የከፈሉትንና ስማቸውን በወርቅ ቀለም በታሪክ ማሕደር የጻፉትን አፍሪካውያን አባቶቻችንን ማስታወስ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ ይህ ጽሑፍም ለትላንትናው አፍሪካ አንድነት ድርጅት ለዛሬው የአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን የታገሉትን የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ አባቶቻችንን ታሪክ በተከታታይ በአጭሩ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡
ይህ ጹሑፍ የአፍሪካ ኅብረትን የ50ኛ ዓመት ወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ በቅድሚያ የአፍሪካ አባት፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማትና የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ዓርማ፣ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋምና በሂደትም ለኅብረቱ እውን መሆን ትልቁን የመሠረት ድንጋይ ስላስቀመጡት ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ ታሪክ፣ ፖለቲካዊ ሰብእና፣ በአፍሪካውያንም ሆነ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ስለነበራቸው መወደድ፣ ተቀባይነትና ታላቅ ክብር በአጭሩ በማዘከር የታሪክ ማስታወሻውን አሐዱ ብሎ ይጀምራል፡፡
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ መንግሥት ታሪክ በእሳቸው ዘመን ከነበሩ ከተራው የኅብረተስብ ክፍል ጀምሮ እስከ ታላላቅ ባለ ሥልጣናትና የሃይማኖት አባቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ የውጭ አገር መሪዎች፣ ታላላቅ ሰዎችና ፖለቲከኞች በቃል ከተናገሩት፣ በጽሑፍ ካስቀመጡት፣ በግል ማስታወሻዎቻቸው ከተዉልን፣ እንዲሁም የአጼ ኃ/ሥላሴንና የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጸሐፍት በመጻሕፍቶቻቸው ካሰፈሯቸው መረጃዎች በመነሣት ነው ይህን አጠር ያለ የታሪክ ማስታወሻ ጽሑፍ ያዘጋጀሁት፡፡
በአጭር ቃል የዚህ ተከታታይ ታሪክ አቅራቢ የአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመን ጣእሙንም ሽታውንም አልደረስበትም፡፡ በእሳርቸው ዘመንም አልታሰበም፣ አልተፈጠረምም፡፡
ይሁን እንጂ እንደ ታሪክ ተማሪነቴና ባለሙያነቴ የኢትዮጵያን ታሪክ በሰፊውና በሚገባ ማጥናት ከጀመርኩበት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንስቶ አሁን እስካለሁበት የትምህርት ሕይወቴና የሥራ ልምዴ እንዳስተዋልኩት፣ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ አፄ ኃ/ሥላሴ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የሚገለጹበት ታሪክ፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ዘንድም አንቱታን ያተረፉበትን ዝናና ክብር እንዲጎናጸፉ ያደረጋቸው በሳል የሆነ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሰብእና እንዳላቸው ነው የተረዳሁትና ያስተዋልኩት፡፡
በስድስት ዓመታት ውስጥ ለሁለት ጊዜ ‹‹Man of the Year›› የዓመቱ ምርጥ ሰው በማለት የለንዶኑ ታይምስ መጽሔት የመረጣቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ከፍ ያለ ሰብእና የነበራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ታላቅ መሪና አባት የሚታዩ የተዋጣላቸው ዲፕሎማቲክ፣ እንዲሁም በዓለማችን ከሚገኙ ታላላቅ መሪዎችና ፖለቲከኞች ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የነበራቸው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናትና ብዙዎች ሰዎች ይመሰክራሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ኃ/ሥላሴ ከሀያ በየሚበልጡ የክብር ዶክትሬት ድግሪዎችን ከተለያዩ አገራት መሪዎችና ዩኒቨርስቲዎች ተቀብለዋል፡፡ ምናልባትም አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምትታወቀበት ድርቅ፣ ራብና የእርስ በርስ ጦርነት ባሻገር በአንጻራዊ መልኩም ቢሆን በአዎንታዊነት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአገራችንን ስም በመልካም እንዲነሣ ምክንያት ከሆኑ የኢትዮጵያ መሪዎች መካከል አፄ ኃ/ሥላሴ አንዱ፣ ብቸኛውና ዋንኛው ናቸው ብል፣ ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
ይህን ኢትዮጵያን አዎንታዊ በሆነ መልኩ እንድትነሳ በማድረግ ረገድና ዓለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ የነበራቸውን ተቀባይነት፣ ክብርና ዝና እንዲሁም ለባለ ቃል ኪዳን አገሮችና በኋላም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሥረት፣ ለ50ኛ ዓመቱ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉ ዋዜማ ላይ ለሚገኘው ለአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን፣ ንጉሡ አፄ ኃ/ሥላሴ የነበራቸውን ትልቅ ሚና የሚያስታውስ አንድ ያጋጠመኘኝን ታሪክ እዚህ ጋር ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
እውቁ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላና በርካታ አፍሪካውያን የነጻነት ታጋዮች ለ27 ዓመታት በተጋዙበትና በመንግሥታቱ ድርጅት፣ ዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስ አድርጎ በመዘገበው በሮቢን ደሴት ሙዚየምና በደቡብ አፍሪካ የአርትና ካልቸር ደፓርትመንት የሚሰጠውን የስኮላር ሺፕ አሸንፌ፣ በተማርኩበት በኬፕታውኑ የዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቆይታዬ ከኢትዮጵያዊነት የነጻነት መንፈስና ከአፄ ኃ/ሥላሴ ጋር በተገናኘ አንድ በእጅጉ ያስደነቀኝ ነገር ገጥሞኝ ነበር፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በዋነኝነት በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲና በኬፕ ታውን ዩኒቨርስቲ በሚገኙ ደቡብ አፍሪካውያንና የሌሎች አፍሪካ አገሮች የተቋቋመ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ (የራስ ተፈሪያን) የተማሪዎች እንቅስቃሴ ኅብረት በሚል መጠሪያ የሚታወቅ በዩኒቨርስቲው ግቢ ቢሮ ተሰጥቶት የሚንቀሰቀስ ማኅበር ነበር፡፡
በነገራችን ላይ በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች እንደታዘብኩት በፖለቲካና በሃይማኖት፣ እንዲሁም ኪነ ጥበብን፣ ባህልንና ታሪክን መሠረት አድርጎ የተቋቋሙና በነጻነት በዩኒቨርስቲው ግቢ ቢሮ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ በተማሪዎች የተቋቋሙ የተለያዩ ድርጅቶችና ፓርቲዎች ይገኛሉ፡፡
ታዲያ እኔ በተማርኩበት በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲ በሚገኘው የግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የተማሪዎች ኅብረት እንቅስቃሴ ቢሮ ውስጥ የእንቅስቃሴው ደጋፊዎችና አባላት የሆኑት ተማሪዎች ለኢትዮጵውያን የስኮላር ሺፕ ተማሪዎች ባቀረቡላቸው ጥያቄ መሠረት የአማርኛ ቋንቋን የሚያስተምሯቸው ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ተማሪዎች ነበሩ፡፡
እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ከእኔ ቀደምው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለምርምር ሥራ፣ ለልምድ ልውውጥና ለተጨማሪ ጥናት ወደ አውሮፓ በሄዱበት አጋጣሚ ለእነዚህ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ከአንተ በተሻለ ስለ ኢትዮጵያችን የሺህ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ የነጻነት ተጋድሎና ቋንቋችንን ሊያስተምራቸው የሚችል የለም በማለት ከራስ ተፈራውያኑ የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ጋር አስተዋወቁኝ፡፡
ከዚሁ ማኅበር አባላት ተማሪዎቹ ጋር በተዋወኩበት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚገባ ለመግባባት ቻልን፡፡ ለጥቂት ወራት እነዚህ ወጣት ተማሪዎች የአማርኛ ቋንቋ ማስተማር ቆይታዬ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ሃይማኖት … ወዘተ ባደርግናቸው ውይይቶች በርካታ ቁም ነገሮችን አንስተን እንነጋገር ነበር፡፡
በአብዛኛው የውይይታችን ማእክል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ፣ ለአፍሪካ የፀረ-ባርነትና የፀረ-ቅኝ ግዛት የነፃነት ትግል፣  በደቡብ አፍሪካ ፀረ-አፓርታይድ ትግል ውስጥ ስለነበራቸው ጉልህ ሚናን በተመለከተ ነበር፡፡ በዚህ ውይይታችን ውስጥ ደግሞ ደጋግመው ከሚነሱት መካከል አፄ ኃ/ሥላሴ አንዱና ዋናው መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
እኔ እንደ ኢትዮጵያዊነቴና የታሪክ ባለሙያነቴ ስለ አገሬ ኢትዮጵያ ታሪክና ስለ መሪዎቻችን ካለኝ ግንዛቤና እውቀት ይልቅ እነዚህ አፍሪካውያን ተማሪዎች ስለ አኅጉራችን አፍሪካና ስለ አገሬ ታሪክ ያካፈሉኝ እውቀታቸውና ያላቸው መረዳት በጊዜው በእጅጉ ግርምትን አጭሮብኝ ነበር፡፡
እነዚህ ተማሪዎች ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህልና የነጻነት ተጋድሎ ውስጥ ያላቸውን ማእከላዊ ስፍራን በተመለከተ የሚያስረዱ በቢሮአቸው ያሰባሰቧቸው መጻሕፍቶችና መዛግብቶቻቸው፣ የምስልና የድምፅ መረጃ ክምችቶቻቸው በእጅጉ ነበር ያሰደነቀኝ፡፡
ከዚህም በላይ ደግሞ ሌላው በእጅጉ ያስደመመኝ ነገር ቢኖር በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ በሚገኘው የራስ ተፈሪያኑ ተከታዮች ማኅበር ቢሮ ግድግዳ አንድ ጎን በሁለት የታሪክ መስመር ተከፍሎ በተለያዩ ሰዎች ምስሎችና መረጃዎች አሸብርቆ ያየሁት Wall of Fame እና Wall of Shame የሚለው የቢሮው ግድግዳ ክፍል ነው፡፡
በዚሁ Wall of Fame እና Wall of Shame ወይም ‹‹የታሪክ ዕንቁዎችና የታሪክ አተላዎች›› ተብሎ በተከፈለው ግድግዳ ላይ ‹‹በዎል ኦፍ ፌም›› ምስላቸውና ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከተለጠፉት መካከል የአፄ ኃ/ሥላሴና የባለቤታቸው የእቴጌ መነን በመጀመሪያው ረድፍ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በዓድዋው ዘመቻ የኢጣሊያንን ወራሪ ኃይል አሸንፈው አዲስ የጥቁር ሕዝቦችን አዲስ ታሪክ የጻፉት የአፄ ምኒልክ፣ እንዲሁም ከእንግሊዞች ጋር ተዋግተው ራሳቸውን የሠዉት የአፄ ቴዎድሮስ ምስሎችና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በዚህ ‹‹የታሪክ ዕንቁዎች›› የክብር ግድግዳ ላይ አፄ ኃ/ሥላሴ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በገፍ በወረረች ጊዜ በሊግ ኦፍ ኔሽን፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያቀረቡት አቤቱታና ንግግራቸው በልዩ ንድፍና በአገራችን ሰንደቀ ዐላማ አሸብርቆ በግድግዳው ላይ ይታያል፡፡ ‹‹የዎል ኦፍ ፌምን›› ግድግዳ ካስዋቡ የታሪክ ሰዎች ፎቶግራፎች በአብዛኛው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሸቱት በዓይነትም በብዛትም እጅግ ልቀው ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ‹‹በዎል ኦፈ ፌም›› የታሪክ መስመር ውስጥ ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉ እንደ እነ ማርከስ ጋርቬይ፣ አፍሪካ አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር፣ የፓን አፍሪካ አባቶች የጋናው ንኩርማ፣ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ፣ ሴኔጋላዊው ሴዳር ሴንጎርና ሌሎችም የአፍሪካ የነጻነት ታጋዮችና መሪዎች በኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማና በኃ/ሥላሴ ግንባር ቀደም አዝማችነት የክብር ግርግዳውን ተጋርተውታል፡፡
ሌላው አስገራሚው ነገር የንጉሡን የአፄ ኃ/ሥላሴን ልደትና የነገሡበትን ዕለት የራስ ተፈራውያኑ ማኅበር ተከታይ ተማሪዎች እንግዶችን ከውጭ ሁሉ ሣይቀር በመጋበዝ ጭምር የዩኒቨርስቲውን የተማሪዎች ማእክልንና የግቢውን ሜዳ በኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ፣ በኃ/ሥላሴና በባለቤታቸው እቴጌ መነን ፎቶ ግራፍ አሸብርቀውና በአፍሪካ የሬጌ ሙዚቃ ስልት አጅበው በታላቅ በሆነ የኢትዮጵያዊነት የነጻነት መንፈስ ቀናቱን ያከበሩ እንደነበረ ትዝ ይለኛል፡፡
የማስታውሰው በዩኒቨርስቲው የምንገኘው በጣት የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በአፍሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም በድርቅ፣ በራብና በእርስ በርስ ጦርነት ስማችን እየተነሳ የምንሳቀቅበትን ምስላችንን፣ እነዚህ የዩኒቨርስቲው የራስ ተፈራውያን ተከታይ ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በግቢው ውስጥ የአገራችንን አረንዴ፣ ብጫና ቀይ ሰንደቀ ዓላማ ሰቅለው ሲያከብሩ ስናይ በአገር ፍቅር ናፍቆትና ትዝታ፣ በኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜትና ኩራት ውስጣችን የተናጠበትን አጋጣሚ አልረሳውም፡፡
በእርግጥ የእነዚህ ተማሪዎች እንቅስቃሴና አካሄድ በአብዛኛው ሃይማኖታዊ መልክ ያለውና ኃ/ሥላሴን መለኮታዊ ሰብእና እንዳላቸው አድርጎ የሚያቀርብ ቢሆንም የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ከሃይማኖታዊ መልኩ ይልቅ አፍሪካዊነቱና ፖለቲካዊ አንድምታው በእጅጉ የጎላ ነው፡፡
እነዚህ ደቡብ አፍሪካውያንም ሆነ የሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተማሪዎች ልብም ሆነ በአብዛኛው ጥቁር ሕዝቦች ልብ ውስጥ ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ሃይማኖት፣ ነጻነት ትልቅ ተምሳሌትና ማእክል ተደርጋ የምትወሰድ አገር ናት፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ባላት የሺህ ዘመናት የረጅም ዘመን ሥልጣኔ፣ ታሪክና ቅርስ የተነሣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ የሆነ የታሪክ እሴት ያላት አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ በተለይም ደግሞ መላው አፍሪካንና የጥቁር ዘርን ሁሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያነቃነቀው ኢትጵያውያን በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል ኢትዮጵያን ከጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ማማ ላይ እንድትወጣ አስችሏታል፡፡
ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያንና በጃማይካና በካረቢያ ላሉ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል መለኮስ ይኸው የአድዋው ድል ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ የእነ ማርከስ ጋርቬይና የትግል አጋሮቹ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነትና የመብት ጥያቄ ውሉ የሚመዘዘው ከኢትዮጵያዊነት የነጻነት መንፈስ፣ የአባቶቻችን የአይበገሬነትና ቆራጥ የተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ነው፡፡
የአፍሪካውያኑ የፓን አፍሪካ አቀንቃኞችና የፀረ ቅኝ ግዛት ታጋዮች የእነ ንኩርማ፣ የእነ ጆሞ ኬንያታ የአፍሪካዊነት ስሜትና ቆራጥ መንፈስ መፍለቂያ ምንጩም ይኸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከተሸከሙት ክቡር የነጻነት ተጋድሎ አኩሪ ታሪክና ቅርስ የሚመዘዝ ነው፡፡
ከአፄ ምኒልክ የዓድዋው ድል በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኃያላኑ አገሮች እኩል የተሠለፈችው ብቸኛው የጥቁር ሕዝብ አገር ኢትዮጵያ ይህ ገናና የነጻነት ተጋድሎ ታሪኳ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ ኤዥያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጃማይካና ካረቢያን ምድር ድረስ ዘልቆ ተሰምቶ ነበር፡፡
ይህ የኢትጵያዊነት የነጻነት መንፈስ ውሉ ሳይቋረጥ በአፍሪካውያንና በጥቁር ሕዝቦች ደም ውስጥ በሚገባ ተዋህዶ፣ በተባበረ ክንድ የጸናችና አንድ የሆነች አፍሪካ በዓለም መድረክ ከፍ ብላ እንድትታይ ደግሞ ትልቁን ሚና በመጫወት ረገድ አፄ ኃ/ሥላሴ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
ይህን ለአፍሪካ አንድነት እውን መሆን ኢትዮጵያና አፄ ኃ/ሥላሴ ያደረጉትን ታላቅ አስተዋጽኦና ተደናቂ ሥራ በተመለከተ በወቅቱ በአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት የናይጄሪያው ጠቅላይ ሚኒስቴር የሆኑት፣ ክቡር ሰር አል ሃጂ አቡበከር ታፌዋ ባሌዋ እንደሚከተለው ነበር ያሉት፡-
መላው የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎችና የመንግሥታት ባለ ሥልጣኖች በአዲስ አበባ ላይ ሊገኙ ለመቻላቸው በግርማዊነትዎ ጥረት ስለሆነ በተለይ ለግርማዊነትዎ እጅግ ከፍ ያለ ክብር የሚያሰጥ ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ አንድነት እንዲገኝ የምናደርገው ጥረት ወደፊት የኢትዮጵያን መናገሻ ከተማ የአዲስ አበባ ስም ደጋግሞ የሚያወሳ ስለሆነ የአዲሲቱ አፍሪካ ታሪክ የግርማዊነትዎን ስም በተቀዳሚው ገጹ ላይ አሳምሮ የሚያኖረው ለመሆኑ ጥርጥር የለበትም፡፡ 
አፄ ኃ/ሥላሴ በ1930ዎቹም ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል እንድትሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ኢትዮጵያንም ብቸኛዋ አፍሪካዊትና የጥቁር አገር ሊግ ኦፍ ኔሽን አባል በማድረግ ጥረታቸውን በሚገባ አሳክተዋል፡፡
በኋላም በተባበሩት መንግሥታት ምሥረታ ስብሰባ ወቅትም ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዜቬልት፣ ከብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችልና ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ስታሊን ጋር በያልታ ጥቁር ባሕር ልዩ ስብሳባ ላይ ተሣትፈዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋራ ስምምነት መሠረትም በኮሪያ ልሣነ ምድር የኢትዮጵያን የሰላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በዚህም አፄ ኃ/ሥላሴ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲታወቁ ትልቁን ሚና ተጫውተው አልፈዋል፡፡
ፍቅር፣ ወንድማማችነት፣ ሰላም፣ አንድነትና ኅብረት ለአፍሪካና ለአፍሪካውያንን ወሳኝና ተቀዳሚ ነገር መሆኑ የተረዱት አፄ ኃ/ሥላሴ አፍሪካውያን አባቶችን፣ ፖለቲከኞችንና መሪዎችን በማስተባበር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
በወቅቱ ድርጅቱ ሲቋቋም የነበሩ ሰዎች እንደመሠከሩት አፄ ኃ/ሥላሴ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የአፍሪካ መሪዎችን ጉባኤ ስብሰባ በመምራት፣ ይህ የአፍሪካውያን የወንድማማችነት፣ የአንድነትና የፍቅር ሰነድ ሳይፈረም ማንኛችንም ብንሆን ከዚህ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በጭራሽ አንወጣም በማለት የተኮራረፉና የተለያዩ ፖለቲካዊ ቁርሾ ውስጥ የገቡትን የአፍሪካ አገራት መሪዎችን በማግባባትና በማሸማገል ንጉሡ ኅብረቱ እውን እንዲሆን ታላቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡
የትላንትናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት በሁለት እግሩ እንዲቆም በማስቻል የኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔና ቅርስ፣ የቀደሙ አባቶቻችን ጽኑና አይበገሬ የሆነው የኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ኩራትና መንፈስ እንዲሁም ጥቁር ሕዝቦችን ሁሉ ያኮራውና አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲራመድ ያስቻለው የኢትዮጵያውያኑ የነፃነት ተጋድሎ፣ በባርነትና በቅኝ ግዛት ስር ይማቅቁ ለነበሩ ለአፍሪካ አገሮች ነፃነትና አንድነት እውን መሆን ትልቁን መሠረት ጥሏል፡፡
ይህን የኢትዮጵያንና የኢትጵያውያንን ታላቅ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ብሔራዊ ኩራትና የአባቶቻችንን አኩሪ የነፃነት ገድል ለዘመናዊው ዓለም በማስተዋወቅና ረገድ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ኃ/ሥላሴ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ክቡር ስምና ዝናና የፈተረላቸውን በርካታ አኩሪ ስራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዛሬ የ50ኛ ዓመቱን የወርቅ ኢዮቤልዩ ልደቱን ለማክበር ዋዜማ ላይ ያለውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/ኅብረት እንዲቋቋም ከሐሳብ ወይም ከጽንሱ አንስቶ እስከ ተግባራዊነቱ ድረስ የላቀ ተሣትፎ ነበራቸው ንጉሡ አፄ ኃ/ሥላሴ፡፡
ንጉሡ ቀዳማቂ አፄ ኃ/ሥላሴ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፡-
በዚህ በዛሬው ቀን በዚህች በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተካፋይ ለመሆን የመጣችሁትን የነፃ አፍሪካ አገር መሪዎች፣ ወንድሞቻችን በራሳችንና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ስንቀበል በጣም ደስ ይለናል፡፡ ይህ ዛሬ እኛ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች የምናደርገው ጉባኤ በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ የዚህን ታላቅ ጉባኤ መደረግና የመላው አፍሪካ አገሮች መሪዎች ተካፋይ በመሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችን በውስጧም ለሚገኙት ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነት ዓይነተኛ ምስክር ነው፡፡ ባጭሩ ይህ ቀን ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን በመላ ታሪካዊና ታላቅ ቀን ነው … ፡፡
የጊኒ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሴኮ ቱሬም በአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ለአፍሪካ አንድነት ምስረታ ኢትዮጵያና ንጉሡ አፄ ኃ/ሥላሴ ያደረጉትን ታላቅ አስተዋጽኦና ሥራ በተመለከተ ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉት፡-
… ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ስለ አፍሪካ ነፃነት በጀግንነት የተዋጋ፣ ነፃነትም ቋሚ እንዲሆን፣ ሕዝቦቻችን ያለ ምንም የውጭ መንግሥታት ተቆጣጣሪነትና ጣልቃ ገብነት በተገቢ ሥልጣናቸው እየተመሩ የገዛ ራሳቸውን ዕድል እንዲመሩ ያላቸው ሥልጣን እንዲጠበቅላቸው የደከመ አፍሪካዊ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ በንጉሠ በአፄ ኃ/ሥላሴ አስተባባሪነትና መሪነት፣ የአፍሪካውያኖችም ጉባኤ የተደረገው በኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ስለሆነ፣ አዲስ አበባና ኢትዮጵያ አሁንም የበለጠ ከአፍሪካ ታሪክ ጋር የተሳሰሩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት በአንድ አኅጉር ሕዝቦች ፈቃድ ተነሳስቶ በሚመራው የዕድገት ፍላጎትና ሥራ ሁሉ ሳይቋረጥ ስማቸው ተያይዞ የሚኖር ይሆናል … ፡፡
ለአፍሪካ አንድነት እውን መሆን ከአገራችን ኢትዮጵያና ከአፄ ኃ/ሥላሴ ጋር አብሮ ስማቸው የሚነሡ ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ድርጅቱንም በጸሐፊነት ያገለገሉ ባለ ታሪክ የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ እነርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ አቶ ከተማ ይፍሩና የድርጅቱ የመጀመሪያ ዋና ጸሐፊ ሆነው የተመረጡት አቶ ክፍሌ ወዳጆ ናቸው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አቶ ከተማ ይፍሩ በመላው አፍሪካ አገራት በመዞርና መሪዎቹን ወደ ጉባኤው እንዲመጡ በመጋበዝና በማግባባት ታላቅ የሆነ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አንዳንድ ጸሐፊዎችና ታሪክ አዋቂዎች እንደሚሉትም አቶ ከተማ ይፍሩ ከመሪዎቹ ማረጋገጫ እስከሚያገኙ ድረስ ወደ አገራቸው መሄድ እንደማይችሉ በመግለጽ አፍሪካውያን መሪዎች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ በማድረግ ትልቅ ጥረት ማድረጋቸውን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡
የዛሬውን መጣጥፌን ከማጠናቀቄ በፊት በቀጣይ ጽሑፌ ስለ ፓን አፍሪካ አመሠራረትና፣ በፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ውስጥ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውን ድርሻ ምን እንደነበር ከታሪክ ማሕደር በማጣቀስ ለመጻፍ እሞክራለሁ፡፡ በጽሑፌም ቀንደኛ ፓን አፍሪካኒስት ስለነበረው የጋናው ዶ/ር ንኩርማ በጥቂቱ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
የዛሬውን አጭር መጣጥፌን ኢትዮጵያ፣ ጀግና ልጆቿና ንጉሠ ነገሥቷ የነበሩት አፄ ኃ/ሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅትና መመሥረትና በኋላም ለኅብረቱ እውን መሆን ያበረከቱትን ትልቅ አስተዋጽኦ ያዘከርኩበትን አጭር የታሪክ ማስታወሻ፣ አፄ ኃ/ሥላሴ በአዲስ አበባ ላይ በተደረገው የግንቦት 15ቀን 1955 ዓ.ም. የአፍሪካ መሪዎች መክፈቻ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ታሪካዊ ንግግራቸው ጽሑፌን ልቋጭ፡፡
ዛሬ የገጠመን ዕድል በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ መቼም ያልተገኘ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ በፊታችን የተደቀኑት ችግሮች ያንኑ ያህል ከፍ ያሉና ከባድ ናቸው፡፡ ታሪክና ጊዜ የጣሉብን ከፍተኛ ኃላፊነት ሁላችንም ረጋ ብለን እንድናስብና እንድናመዛዝን ያስገድደናል፡፡ የተነሳንበትን ከፍተኛ ተግባር በመልካም አከናውነን ብንገኝ ስማችንና ተግባራችን በታሪክ መልካም ስም ይኖረዋል፡፡ ተግባራችንን ሳንፈጽም ብንቀር ግን ይታዘንብናል፡፡ ስለዚህ እምነታቸውን የጣሉብንን ሕዝቦቻችን በሚመጡት ጊዜያቶች ውስጥ ከእኛ የሚጠብቁትን ሁሉ ለመፈጸም እንዲያበቃን ሁሉን የሚችለውን ፈጣሪያችን ጥበብንና አስተዋይነትን እንዲሰጠን እናምነዋለን፣ እንለምንዋለን፡፡
ክብር ለአፍሪካ አንድነት ለደከሙ አፍሪካውያን አባቶቻችንና ጀግኖቻችን ሁሉ!