Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) :- ባለፈው እሁድ ህዳር 8 ሰማያዊ ፓርቲ በሳውዲ አረቢያ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ለመቃወም ያወጣውን መርሃ ግብር መዝጊያ ላይ እውቁ የዓለም አቀፍ ህግ ምሁር ዶክተር ያቆም ኃ/ማሪያም በታጋባዥ እንግዳነት ተገኝተው ነበር፡፡ በወቅቱ ዶ/ክተሩ ያደረጉትን ንግግርም በስነ ስርዓቱ ላልተገኙት ይደርስ ዘንድ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ ምንም እንኳ ያለፉት 20 አመታት የሰቆቃና የውርደት አመታት ቢሆኑም ሳውዲ ውስጥ በሚገኙት ወገኖቻቸን የደረሰው ግን በ1977 በኢትዮጵያውያን ላይ ከደረሰው ርሃብና ውርደት በኋላ የመጀመሪያው ነው፡፡(ምንሊክ ሳልሳዊ)በዚህ ችግር ሳውዲ አረቢያ ያሉት ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥም ሆነ በሌላው አለም ያለነው ኢትዮጵያውያን ተደፍረናል፡፡
አገራችንም ቢሆን ተደፍራለች፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ባሉት ዘመናት ከውርደት የታደጓት ትውልዶችን አይታለች፡፡ ይህ በተለይ ለዘመኑ የኢትዮጵያ ትውልድ አሳፋሪ ውርደት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሳውዲ ስላለው የምናወራው ግልጽ ሆኖ ስለወጣ እንጅ ውርደቱ እጅግ መጠነ ሰፊ ነው፡፡ ለአብነት ያህል 23 እስረኞች በዛምቢያ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ በታንዛኒያ 50፣ በማላዊ ደግሞ 25 ኢትዮጵያውያን ህዝብ፣ መሪና አገር እንደሌላቸው በእስራት እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ አገሪቱ በገጠማት ችግር ምክንያት በስደት ላይ እያለ በርሃብ የሞተውን፣ ውሃ ውስጥ የቀረውን፣ በአውሬ የተበላውንና በሌላም ችግር ነፍሱን ያጣውንና የተሰቃየውን ደግሞ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ በሌሎች አገራት እንዲህ አይነት ችግር ታይቶ ወይንም ተስምቶ አይታወቅም፡፡ ለምን የኬንያና የታንዛኒያ ህዝቦች እንዲህ አይነት ችግርና ውርደት አይገጥማቸውም? ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት የተሻለ ሀብትና ህዝብ አላት፡፡
ሰፋፊ መሬቶች አሉን፡፡ ወንዞች አሉን፡፡ እንዲያውም የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ተብላ ትጠራለች፡፡ የምስራቅ አፍሪካም ሆነ የአህጉሩ የውሃ ማማ ትባላለች፡፡ ህዝቡን ከሌላው አገር ህዝብ ጋር ሲነጻጸር ትሁት ቢሆን እንጅ ሰነፍ አይደለም፡፡ ከአፍሪካዋ ደቡብ አፍሪካ ጀምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰርተው የማይጠግቡ ናቸው፡፡ እንዲያውም በደቡብ አፍሪካና በእነዚህ አገራት ኢትዮጵያውያን የትላልቅ ህንጻዎች፣ የንግድ ድርጅቶችና የሌሎች ሀብቶች ባለቤቶች ናቸው፡፡ አገር ውስጥ ምቹ ስርዓት ባለመኖሩ ምክንያት ግን ህዝቦች አገራቸው ላይ ሰርተው ከመኖር ይልቅ ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያልተማሩት ብቻ ሳይሆኑ የተማሩትም በከፍተኛ ደረጃ እየተሰደዱ ነው፡፡ በምሁራን ፍልሰት ኢትዮጵያ ቀዳሚ አገር ሆናለች፡፡ ስለሆነም አገር ውስጥም አላሰራ ያለው፣ ለስደቱም ምክንያትና በስደተኞቻችንም ሆነ በአገራችን ላይ እየደረሰ ለሚገኘው ስቃይ ዋነኛው ምክንያት ስርዓቱ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው ‹‹የዚህ ብሄር አባል አይደለህም ውጣ›› ተብለው ከተባረሩ አገራችን ብለው ከመኖር ይልቅ ስደትን ይመርጣሉ፡፡ ለበርካታ አመታት ተምሮ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ወጣት የፓርቲ አባል ስላልሆነ ብቻ ስራ አታገኝም ከተባለ እጣ ፈንታው ስደት ነው የሚሆነው፡፡ እትብቱ የተቀበረበትን መሬት በሲጋራ ዋጋ አሁን ህዝቦቻችንን ለሚያሰቃዩት ሳውዲዎች አሳልፎ ሲሰጥበት ህዝብ ከስደት ውጭ ምን አማራጭ ይሆረዋል?
መንግስት የሌለው ህዝብ ሳውዲዎች በህዝቦቻችን ላይ የፈጸሙት በደል በተጎጅ ወገኖቻችን፣ በቀሪው ህዝብና በአገራችን ላይ የተቃጣ ብቻ አይደለም፡፡ የአገሬው ሰው ‹‹ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ›› እንዲሁ መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠውን አካልም እንደ መንግስት ስለማይቆጥሩትና ስለሚንቁት የፈጸሙት ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ኢህአዴግ እንደ መንግስት ለኢትዮጰያ ህዝብ እንደማይጨነቅም ህዝብ ሲበደል ምንም ደንታ እንደሌለው አሳምረው ያውቃሉ፡፡ የሌሎች አገራት መንግስታት ግን ለዜጎቻቸው ከፍተኛ ጥበቃና ለሚደርስባቸው ችግርም ተገቢውን ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት አንድ ፓኪስታናዊ ቦሌ አገር ማረፊያ ሲገባ ኢትዮጵያዊው ልጅ ስለያዝኩ ደብተር ያዝልኝ ይለዋል፡፡ ፓኪስታናዊውም ይተባበረዋል፡፡ ይሁንና ደብተሩ ውስር 90 የሚሆኑ ሲም ካርዶች ነበሩት፡፡ ፖሊሶቹም ይህን ፓኪስታናዊ ያስሩታል፡፡ ፓኪታናዊያንም ዜጋቸው መታሰሩን በመግለጽ እንዳስፈታላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ከፓኪስታን ኤምባሲ ጋርም መረጃ ተለዋውጠናል፡፡ ይህ ፓኪስታናውይ ተፈትቶ አገሩ ከገባ በኋላ ሳይቀር ኤምባሲው እየደወለ ጉዳዩ ምን ላይ እንደደረሰ ይጠይቀኝ ነበር፡፡ በቡሽ አስተደደር ዘመን ወደ ሰሜን ኮሪያ ዘመዶቿን ልትጠይቅ የሄደች አሜሪካውይት ሰላይ ነሽ ተብላ ትታሰራለች፡፡ ለዚህ አሜሪካው መፈታት እንዳለባት ፕሬዝደንት ክሊንተን ተነሳሽነቱን ይወስድና ለቡሽ አስተዳደር ያቀርብለታል፡፡ በስተመጨረሻ ፕሬዝደንት ክሊንተን ይችን አሜሪካውይንት ሰሜን ኮሪያ ድረስ ሄዶ አስፈትቷታል፡፡ በ1960ዎቹ ፍልስጤማውያን በርካታ አውሮፕላኖችን የሚጠፍፉበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚህ መካከል አንዱ ዩጋንዳ ውስጥ የተደረገው ጠለፋ ነው፡፡ የኢንተቤው ክስተት በሚባለው በዚህ ጠለፋ ፍልስጤማውያን ከጠለፉት አውሮፕላን ውስጥ አንዲት እስራኤላዊ አሮጊት ነበሩበት፡፡ ለዜጎቹ የሚጨነቀው የእስራኤል መንግስትም አስራ ሁለት አውሮፕላን ይህችን አሮጊት የሚያስለቅቅ ቡድን ላከ፡፡ ይህ ቡድን በስተመጨረሻ ጠላፊዎቹን ገድሎ አሮጊቷን አድኗል፡፡ ይህን ‹‹ኦፕሬሽን›› የመሩት የአሁኑ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሆ ናቸው፡፡ የጓትማላ ሁለት ዜጎች ወደ ችሊ ባቀኑበት ወቅት ይሞታሉ፡፡ እነዚህን ዜጎች የደረሰውን ችግር ተከትሎም የጓትማላው ፕሬዝደንት ችሊ ድረስ አቅንተው የሁለቱን ዜጎች አስከሬን ይዘው በመምጣት አገራቸው ውስጥ እንዲቀበሩ አድርገዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ ይህን ያህል ሰቆቃ ሲደርስ ግን ጠቅላይ ሚኒስተር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ምንም አላሉም፡፡ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ተደርጎ እንዲውለበለብ አልተደረገም፡፡ የሀዘን ቀን እንዲኖር አልተደረገም፡፡ ይልቁንስ በወገኖቻቸው ላይ የደረሰውን ችግር ለማጋለጥ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡትን ኢትዮጵያውያን በጨካኝነት ደብድበዋል፤ አስፈዋል፡፡ ኢህአዴግ ለምን ይህን አደረገ? አስራኤሎች አንዲት አዛውንት ላይ የደረሰን ችግር አስራ ሁለት አውሮፕላን በማሰለፍ ለህዝበባቸው ምን ያህል እንደሚጨነቁ አሳይተዋል፡፡ የጓትማላው ፕሬዝዳንት የሁለቱን ዜጎቹን አስክሬን እራሱ በማስመጣት አገራቸው ውስጥ እንዲቀበሩ አድርጓል፡፡ ቢል ክሊንተን ሰሜን ኮሪያ ድረስ በማቅናት እንድትፈታ አድርጓል፡፡ ሳውዲ አረቢያ የእኛዎቹን ዜጎች እየገደለችና፣ እያሰቃየች ግን ኢህአዴግ ምንም እርምጃ አልወሰደም፡፡ እንዲያውም በራሳቸው ተነሳሽነት ለዜጎቻቸው አለኝታ ለመሆን የተነሱት ላይ እርምጃ በመውሰድ ለኢትዮጵያውያን ያለውን ንቀትና ጥላቻ አሳይቷል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? በአገራችን ዴሞክራሲያዊና የህዝብ ምርጫ የለም፡፡ ይህም ማለት ህዝብ መንግስትን የማውረድና ስልጣን ላይ የማውጣት ስልጣን የለውም ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ኢህአዴግ ይህ የማይጨነቅለት ህዝብ በምንም መልኩ ከስልጣኑ ሊያወርደው እንደማይችል ስለሚያውቅ ምንም አይነት በደልና ሰቆቃ ቢደርስበትም ደንታ ቢስ መሆንን መርጧል፡፡ ከምርጫ ባሻገር ነጻ ፍርድ ቤትም አለመኖሩ ኢህአዴግ ራሱ በሚያስቀምጣቸው አካላትና በአባላቱ በሚመራው ፍርድ ቤት ምክንያት ምንም እንደማይደርስበት ያውቃል፡፡ ነጻ ፍርድ ቤት ቢኖር ኖሮ ኢህአዴግ ህዝብ በሚደርስበት ማንኛውም ጉዳይ በቀዳሚነት መቆም እየነበረበት ቸልተኛ በመሆኑ ሊያስቀጣው ይችል ነበር፡፡ ይህ ባለመኖሩ ምንም ችግር እንደማይደርስበት ያውቃል፡፡ በአገራችን ነጻ ሚዲያ አለመኖሩም ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ ነጻ ሚዲያ መንግስታት መንግስታት በህዝብ ላይ የሚፈጽሙትን በድል፣ መውሰድ ያለባቸውን እርምጃና ሌሎች መረጃዎችን በመስጠት ህዝብን ያነቃል፡፡ ኢህአዴግ ይህን ቸልተኝነቱን ለህዝብና ለዓለም ማህበረሰብ የሚያጋልጥ አማራጭ ሚዲያ ባለመኖሩ የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ ምንም ሊመስለው አይቻለም፡፡ ኢህአዴግ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያውያን ላይ ይህን ያህል ከፍተኛ በደልና ሰቆቃ እየደረሰ፣ አገራችን እየተዋረደች እንቅልፍ ሊወስደው አይችልም ነበር፡፡ በመሆኑም የአንድ አገር ህዝብ የሚቨነቅለትና የሚቆምለት መንግስት ሊያገኝ የሚችለው ዴሞክራሲን ከገነባና መንግስቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለስልጣን ካበቃ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ለኢትዮጵያውያን ሰቆቃ መሰረታዊ መፍትሄው ዴሞክራሲን ማስፈን ብቻ ነው፡፡ ሳውዲ ውስጥ እየተደረገ ያለውን ሰቆቃ በመቃወም የወጡት ኢትዮጵያውያን ላይ መንግስት የወሰደው እርምጃ አሳፋሪ ነው፡፡ ዜጎቹ ያነሱት ጥያቄ ኢህአዴግ ከሚፈራቸው ፖለቲካውይም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች የተለዩ ናቸው፡፡ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ አንግበው የወጡት የሀይማኖት ጥያቄ ይከበር የሚል አልነበረም፡፡ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱም አላሉም፡፡ ጋዜጠኞች ይፈቱ የሚል ጥያቄ ያነሳም አልነበረም፡፡ ይሁንና ከኢህአዴግ ስልጣን ጋር የማይገናኝና ጥያቄን ያነሱትን ዜጎች ሳውዲ ላይ እንደደረሰው የሰቆቃው ሰለባ ሆነዋል፡፡ ምን ይደረግ? ሳውዲ አረቢያ አባል ከሆነችባቸው ትቂት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል ዓለም አቀፍ የሰላተኞች ድርጅት (ILO) አባል ነች፡፡ በዚህ ድርጅት መርህ መሰረት ሰራተኞችመብት መከበር ይኖርበታል፡፡ በተለይ ለሴቶች፣ ለህጻናትና ከአገራቸው ርቀው ለሚገኙ ሰራተኞች ትልቅ ጥበቃ ይሰጣል፡፡ አንድ አባል አገር እነዚህን መብቶች ከጣሰና በሰራተኞች ላይ ችግር ከደረሰ በተቋሙ በኩል መክሰስ ይቻላል፡፡ ምንም እንኳ ሳውዲ አረቢያን ማስቀጣት ባይቻልም ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ማሳጣትና ማሳፈር እንዲሁም በሚቀጥሉት ጊዜያት ተመሳሳይ እርምጃ እንዳይወስዱ ማድረግ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን የፈረመችው እ.ኤ.አ በ1948 ነው፡፡ ከሀይቲ ውጭ ሌላ የጥቁር ህዝቦች መኖሪያ አገር ይህን ህግ በወቅቱ አልፈረመም፡፡ ሌሎች ህጎችን በመፈረምም ኢትዮጵያ ቀዳሚ አገር ነች፡፡ ባለፉት 20 አመታት ግን ህግን በመጣስና ከዓለም አቀፍ ተቋማት በመራቅ ከሚገኙት አገራት መካከል ቀዳሚዎቹ ጋር ተመድባለች፡፡ ዜጎቻችን እያሰቃየች የምትገኘው ሳውዲ በንጉሳዊ ስርዓት የምትመራ በህግ በኩል ኋላ ቀር አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ልክ እንደ ሳውዲ አረቢያ ሁሉ የጦር ወንጀለኞችን ፍርድ ቤት አባል ያካልሆኑ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ ሳውዲ አረቢያ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባል ባለመሆኗ ክሱ ሊቀርብ የሚችለው በአገሯ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በሳውዲ አረቢያ መንግስት ላይ የሚደረገው ክስ ጊዜ ከመፍጀት ውጭ ምንም ውጤት አይኖረውም፡፡ ከኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ባልተናነሰ ስርዓቱን ለማስጠበቅ የቆሙ ናቸው፡፡ ከሳውዲ አረቢያ በተጨማሪ ኢህአዴግ ላሳየው ነቀትና ቸለተኝነትም በአለም ወንጀለኞች ፍርድ ቤት መክሰስ ይቻል ነበር፡፡ ሆኖም የፍርድ ቤቱ አባል ባለመሆናችን እንክሰስ ካልን ክሱ የሚሆነው አገር ውስጥ ባለው ፍርድ ቤት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ከሳውዲ አረቢያ የተለየ ውጤት አይኖረውም፡፡ አኬልዳማ በሚል የተሰራው ዶክመንተሪና በሌሎች ጉዳዮች ክስ አቅርበናል፡፡ ሆኖም ምንም ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም፡፡ በአገራቸው እየተፈናቀሉ ያሉት ኢትዮጰያውያንን አስመልክተንም ክስ ብናቀርብም ፍርድ ቤቱ እንደማያስከስስ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን መክሰስ ክፋት የለውም፡፡ እንደ አንድ ትግል ስልትና ለህዝብ እንደማሳወቂያ መውሰድ ይቻላል፡፡ በደሉ የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ኢህአዴግ ላሳየው ቸልተኝነትና ንቀት ክስ ማቅረብ መብት አላቸው፡፡ ውጤቱ ግን በቀላሉ መገመት የሚቻል ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያውያን ተበታትነው ከመታገል ይልቅ ህብረት በመፍጠር በስርዓቱ ላይ ጫና ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን እራሳችን አጠናክረንና አደራጅተን ስለ መብታችን ካልታገልን በስተቀር ከውጭ አገራትና ድርጅቶች ብዙም ውጤት ባንጠብቅ መልካም ነው፡፡ አገራት ቅድሚያ የሚሰጡት ለብሄራዊ ጥቅማቸው ነው፡፡ የእኛ በደል ይህን ያህል ሊያስጨንቃቸው አይችልም፡፡ በመሆኑም ተባብረን መታገል ይኖርብናል፡፡ በአሁኑ ወቀት ዲያስፖራው እየተነቃቃ ነው፡፡ አገር ውስጥ ያለነው ጋር ትስስር በመፍጠር በዜጎቻችን ላይ በሚደርሱትና በሌሎች ችግሮች ላይ የጋራ እርምጃ መውሰድ አለብን፡፡Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar