በአበበ ገላው
የዛሬ ወር ገደማ የቪኦኤ አማርኛ ሪፖርተር የሆነውና አወዛጋቢና የተዛባ መረጃ በማቅረብ በስፋት የሚታወቀው ሄኖክ ሰማእግዜር ሙሉ በሙሉ ሃሰት የሆነ ዘገባ በአሜሪካን ሬድዎ አማካኝነት አሰራጨ። የዘገባው አላማ በካሊፎርኒያ የሚገኘው አዙሳ ፓስፊክ ዩኒቨርሲቲ ለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሰጥቶ የነበረውን የክብር ሽልማት መልሶ መንጠቁንና ዝግጅቱ መሰረዙን በማስመልከት የቀረበው ዘገባ ሃሰት ነው ብሎ ለማስተባበል እና እኔን፣ አለማቀፉን የኢትዮጵያዊያን መብት የጋራ ህብረት እንዲሁም ኢሳትን በሃሰተኝነት ለመወንጀል የታለመ ነበር።
ይሁንና ለእርምጃው ምክንያት የሆነው በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዩኒቨርሲቲው እንዲመረምርና ሽልማቱን መልሶ እንዲያጤን ስለተደረገ መሆኑ በግልጽ የተነገረ እውነታ ነበር። ዩኒቨርሲቲውም ለክብሩ ስነ ስርአት መሰረዝ የሰጠው ዋነኛ ምክንያት ይሄው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጉዳይ መሆኑን በይፋ ደጋግሞ ገልጿል።
አልተሳካም እንጂ ሄኖክ በተለይ በእኔ ላይ ያነጣጠረ በተንኮል የተሞላ ጎጂና የተዛባ ዘገባ ሲያቀርብ ይሄኛው ሶስተኛው ነው። በግንቦት 10, 2004 (May 18, 2012) በአቶ መለስ ዜናዊ ላይ የተቃውሞ ድሞጽ ሳሰማ ሄኖክ በአይኑ ያየው በጆሮው የሰማው ሃቅ ቢሆንም ድምጼን ሳንሱር አርጎ ዘገባውን አዛብቶ ለስርጭት አበቃው። በዚህም ምክንያት ቪኦኤ ከአድማጮቹ ከፍተኛ ተቃውሞ ስለቀረበበት በሳምንቱ ዘጋባውን እንደገና በሌላ ሰው አስተካክሎ ተቆርጦ የቀረውን ድምጼን አስገብቶ ሌላ ዘገባ ለማስተላለፍ ሞከረ። ይሄን በጋዜጠኝነት ስም የተሰራ እርካሽ የፖለቲካ ቁማር ታዝበን አለፍነው።
ከዛም ግኡሽ አበራ የሚባል አንድ የቦስተን ነዋሪ በእኔ ላይ የግድያ ወንጀል ለመፈጸም ሲዶልት ገና ከጥንስሱ በFBI ተደርሶበት ምርመራ እንደተደረገበት ተዘገበ። በዚህ ላይ ወያኔ የተቀናጀ ስራ በመስራት፣ አንዳንድ ድህረ ገጾችን፣ ፓልቶኮችን እና ቪኦኤን በመጠቀም እኔ ግኡሽ አበራን ልክ በሃሰት የወነጀልኩት ለማስመሰል ሌላ ያልተሳካ ጥረት ተደረገ። እንደተለመደው ሄኖክ አሳፋሪ የካድሬ ስራውን በመቀጠል ከፍተኛ መዛባት ለመፍጠር ሞከረ። ትንሽ ብዥታ ቢፈጥሩም ያሰቡትን ያህል ግን አልተሳካም። ፈጽሞ ያላናገረውን የFBI ቃል አቀባይ ጠቅሶ እንደለመደው ድምጽ ሳያስገባ “የጥቅሱ መጀመሪያ፣ የጥቅሱ መጨረሻ” በማለት አድማጭን ግራ የሚያጋባ ዘገባ ለቀቀ። እኔ እንደ ጋዜጠኛ ባይሆንም እንደ ጉዳዩ ባለቤት ከቦስተን FBI ቃል አቀባይ ግሬግ ኮምኮዊች ጋር ያደረኩት ንግግር የድምጽ መረጃ እስካሁን በእጄ ላይ አለ። በተጨማሪም እንደነ ግኡሽ ስራ ቦታው ድረስ ሄደው የFBI መርማሪዎች ካፋጠጡት ግን በሴራው አለመሳተፉ ከተረጋገጠው ቤዛ ጥላሁን ያገኘሁት ዝርዝር መረጃ ጭምር በእጄ ይገኛል።
http://youtu.be/Zv1LtuLEFIU
ዘፋኝና የግኡሽ ደባል የነበረችው አበራሽ የማነ በግዜው የቤዛ ወዳጅ የነበረች ሲሆን አሁን ትዳር መስርተዋል። በወቅቱ ለአበራሽ የማነ መርማሪዎቹ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምንም አይነት ውንጀላ ማንም ባያቀርብባትም ፓልቶክ ላይ ብቅ ብላ በሃሰት አበበ ገላው ወነጀለኝ እንድትል ተደረገ። እነ አውራምባ ታምስም ወገንተኛ የሆነና የሚያስተዛዝብ ስራ ሰሩ። ይህንንም በወቅቱ ታዝበን አለፍነው።
FBI በዋነኛነት ትኩረት ያደረገው ግኡሽ ላይ ነበር። ለዚህም ምክንያት ደግሞ እንዳወሩት በፌስቡክ ስለተሳደበ ወይንም ስለዛተ ሳይሆን በግድያ ወንጀል ዱለታ ሊያስጠይቅ የሚችል መረጃ መርማሪዎች እጅ በመግባቱ ነበር። በቀጣይነት በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ እርምጃ የመውሰድና ያለመውሰድ መብት የመርማሪዎቹ ሲሆን የዘገባው እውነታ ግን ከላይ የተጠቀሰው ነው።
በግልጽ አፍቃሪ ወያኔ የሆነው ሄኖክ ሰማእግዜር ግን ጥቅስ ብሎ ያነበበውን ብዥታ የሚፈጥርና ከዋናው ጭብጥ ውጭ የሆነና አዛብቶ ያቀረበውን ሃተታ በተውሶ የወሰደው ከሶስተኛ ወገን፣ እንደውም እንደሰማሁት ከሆነ፣ ከትግሪኛ ዝግጅት ክፍል ነበር። ይሁንና ጥረቱ እውነቱን አልቀየረውም። ግኡሽ አበራ እኔን በስም ማጥፋት በፍርድ ቤት እንደሚከስ ወያኔዎች ደጋግመው ከመናገር አልፈው ከፍትኛ ገንዘብ ቢያዋጡም እስካሁን የተሰማ ክስ የለም።
እኔ በወቅቱ ወንጀል ሲዶልት የተደረሰበት ሰው ማንንም በስም ማጥፋት መክሰስ አይቻለውም ያልኩት እውነትን በመተማመን ነበር። አሁንም ፍርድ ቤቶች ክፍት ስለሆኑ ግኡሽ ብቻ ሳይሆን የውሸት ዘገባ በማሰራጨት እጅ ከፍንጅ በመያዝ አደባባይ ያወጣሁት ሄኖክ ሰማእግዜር (እስከ እረዳቶቹ) ዶሴውን ጠርዞ ፍርድ ቤት መሄድ ይችላል። ይሁንና ውሸት ታጥቆ አየር ላይ መውጣትም ይሁን የውሸት ዶሴ ጠርዞ ፍርድ ቤት መሮጥ ፈጽሞ እንደማያዋጣ ከወዲሁ መጠቆም እወዳለሁ።
የአሁኑ ይባስ እንዲሉ ሄኖክ አቶ ሃይለማሪያም አሜሪካ ሳይደርሱ ላስቸኳይ ስራ ተመለሱ፣ ያልደወሉትን ስልክ ደውለው ክብሩ ይቅርብኝ አሉ፣ እኔ ያልጻፍኩትን ደብዳቤ እያነበበና እያጠቀሰ፣ ያልተናገርኩትን ተናገረ፣ ያልዘገብኩትን ዘገበ እያለ ፈጽሞ ያላናገራቸውን ቃል አቀባይ ያላሉትን አሉ እያለ፣ አደባባይ ወጣ። በሁዋላ ስናጠያይቅ እንደውም የተረዳነው አሳፋሪው የቪኦኤ የሃሰት ዘገባ የተሰራው በቡድን ለሶስት መሆኑን ነው።
ታዲያ ምነው ይሄ ሁሉ የቪኦኤ ሰራዊት አንዲት ቅንጣቢ መረጃ ማውጣት ተሰናው? ከሁሉ የሚገርመው ደግሙ ውሸታችን “ቢቢጂ” የተባለ ቦርድ አጸደቀልን ብለው አይናቸውን በጨው አጥበው አደባባይ መውጣታቸው ነው። በእውነቱ በጣም ያሳዝናል። ቢቢጂም ቢሆን በመረጃ የተደገፈ ማስተባበያ ይዞ እስካልመጣ ድረስ አድማጭም አክባሪም በቀላሉ ማግኘት ይችላል ብዬ አላምንም። የተራዳሁት አንድ ጉዳይ ቪኦኤ ውስጡን ለቄስ ነው። ማንንም የመውደድም ይሁን የመጥላት ግላዊ መብታቸውን ብናከብርም ውሸት ታጥቀው አየር ላይ ከወጡ ግን ችላ ሳንል ደግመን በእውነት ሚሳኤል አናወርዳቸዋለን።
እኛ ለህዝባችን ነጻነትና መብት ከመከራከርና ከመታገል አንቆጠብም። ለዚህም ደግሞ ከማንም ፍቃድ አንጠይቅም። አንዳንድ የቪኦኤ አማርኛ ክፍል ባልደረቦች የእነ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ክብር ተነካ ብለው እኛን ለማጥቃት መነሳታቸው ባያስገርምም ያሳዝናል። በከንቱ ይደክማሉ እንጂ አቶ ሃይለማርያምም ሆኑ አዙሳ ፓስፊክ ዩኒቨርሲቲ በዙ ተቀጣሪዎች አሏቸው። ሁለቱም ወገኖች ቪኦኤን በቃል አቀባይነትይሁን በጥብቅና አለመቅጠራቸውን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
እንኳን በሜድያ ስራ የተሰማራ ጋዜጠኛ ነኝ ባይ ይቅርና ማንም እንደሚያውቀው አንድ ሚድያ ስተት ሲሰራ ባግባቡ እርማት እንዲያደርግ ይጠየቃል። ስህትት ተሰርቶ ከተገኝም አግባብ ባለው መንገድ እርምት አድርጎ ይቅርታ ይጠይቃል።። ቪኦኤን የሚያህል ግዙፍ ተቋም የሌሎችን ስራ ከማኮሰስ አልፎ በውሸት ጭብጦ የእውነትን ተራራ ለመናድ ጥረት ማድረጉ በጣም ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ከመሆን አልፎ የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ የሚለውን አባባል ያስታውሰናል።
ሌላው አሳዛኝ ጉዳይ በዚህ የሀሰት ዘገባ ቁልፍ ሚና የተጫወተው ፒተር ሃይንላይን በአጠያያቂ መስፈርት ባለፈው ሳምንት ለሄኖክ ሰማ እግዜር “ሽልማት” ማቀበሉ ነው። ሄኖክም ይህንኑ ሽልማት ከአፍሪካ ክፍል ሃላፊው ከአቶ ንጉሴ መንገሻ እጅ ተቀብሏል። በርግጥ ሄኖክ ለማዛባትና ሃሰትን በይፋ በማሰራጨት ተወዳዳሪ ስላልተገኘለት ታላቅ ሽልማት ይገባው ይሆናል። ለጋዜጠኛነቱ ሽልማት መስጠት ግን ጋዜጠኝነትን መስደብ ነው።
በዚህ አይን ከፋች በሆነ አጋጣሚ ከእነ ሄኖክና ፒተር ሃይህላይን ይልቅ የአማርኛው እና የአፍሪካ ክፍል ሃላፊ የሆኑ ሁለት አንጋፋ ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞችን በጣም ታዘብኩ።። ክብር ወደ ትዝብት ያለ ምክንያት እንደማይቀየር ለማንም ግልጽ ነው። ለምን ታዘብከን ብለው ከጠየቁኝ ምላሹን በዝርዝር በአደባባይ ላስረዳቸው ዝግጁ ነኝ። እስከዛው ሆድ ይፍጀው በማለት ለዛሬው የኢሳቱ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን የቪኦኤን ከድጡ ወደ ማጡ የሆነውን የሰሞኑን ጉዞ አስመልክቶ ያዘጋጀውን ምርጥ ዝግጅት ካልሰሙት አያምልጥዎ።
መልካም አዲስ አመት ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!