fredag 22. august 2014

በባቲ ኦሮሞዎች እና የአጎራባች አፋር ክልል ነዋሪዎች ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉ ተሰማ

ነሃሴ ፲፮(አስራ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በባቲ ወረዳ ልዩ ስሙ ቡርቃ በተባለ ቀበሌ አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱ አጎራባች ክልሎች
ነዋሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በተኩስ እየተጋጩ በሁለቱም ወገን ሰዎች እየሞቱ ቢሆንም ፤የሁለቱ ክልል መሪዎች ጉዳዩን ለመፍታት ምንም ዓይነት
ጥረት አለማድረጋቸው እንዳሳዘናቸው የባቲ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
በቡርቃ  ቀበሌ  የተቀበረ ወርቅ አለ ተብሎ መነገሩ ለግጭቱ መባባስ ምክንያት መሆኑን የሚናገሩት የአይን እማኞች፣ የኦሮምያ ዞን መሬቱን
ለባላሀብቶች ሰጥቶ በማስቆፈርላይእያለበአካባቢውየሚኖሩትየአፋርተወላጆችድርጊቱንበመቃወምበቁፋሮበተሰማሩትሰራተኞችላይተኩስ ከፍተው
ጉዳት ማድረሳቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በተኩስልውውጡምቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ከመገደላቸውም በተጨማሪበንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አክለው ተናግረዋል።
አካባቢውን በግል የተደራጁ የአፋር ታጣቂዎች የተቆጣጠሩት ሲሆን የባቲ ወረዳ የፀጥታ ዘርፍ ሃላፊዎች ችግሩን ለመፍታት ቦታውን ከተቆጣጠሩ
ታጣቂዎች ጋር ቢነጋገሩም ታጣቂዎች ማንኛውንም ትእዛዝ ከአፋር መንግስት እስካልመጣ ድረስ  አንነጋገር ምበማለታቸው በአጎራባች ክልሎቹ
የጠረፍ ከተሞች መካከል ሊካሄድ የነበረው የሰላም ውይይት በተደጋጋሚከሽፏል።
የሁለቱ ክልል መንግስታት አመራሮች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ለመፍታት ባለመፈለጋቸው ነዋሪዎቹ ወቀሳ አቅርበዋል።
በሁለቱ ክልል ድንበር ያለው ውጥረት ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ እንደቀጠለ መሆኑን የአይን እማኞች ለዘጋቢችን ገልፀዋል፡                        esat

ከወያኔ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስልጠናዎች የተረዳነው:- ወጣቱ ለለውጥ ዝግጁ ነው፤ የቀረው ድርጅት ነው


የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመሠረቱበት ዓላማ የእውቀትና ጥበብ መበልፀጊያና ማስፋፊያ እና የምርምር ማዕከላት እንዲሆኑ ነው። እውቀትና ጥበብ እንዲበለፅጉ እና የምርምር ሥራዎች እንዲዳብሩ የአካዳሚ ነፃነት መኖሩ ቁልፍ ጉዳይ ነው። የአካዳሚ ነፃነት ሳይኖር መምህራኑም ተማሪዎቹም በነፃነት ማሰብ፣ አስቸጋሪ ጥያቄዎችን ማንሳት እና ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለመሻት መመራመር አይችሉም። የአካዳሚ ነፃነት ሳይኖር የተለያዩ እይታዎችንና ንድፈሀሳቦችን በገለልተኛነትና በሀቀኝነት መመርመር አይቻልም። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአካዳሚ ነፃነት እንዲኖር ተቋማቱ ከፓርቲ ፓለቲካ ገለልተኛ መሆን ይኖርባቸዋል። አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የአንድ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም አራማጅ ከሆነ ተቋሙ የፓርቲው ካድሬዎች ማሰልጠኛ ሆነ ማለት ነው። ዛሬ በአገራችን የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙበት ሁኔታ ይህ ነው። የአገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወያኔ ካድሬዎች ማሰልጠኛ ሆነዋል። ይህ አጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ህወሓት ካድሬ ማሰልጠኛነት መዝቀጥ አንድ ተጨባጭ ማስረጃ ሰሞኑን ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በፕላዝማ ቴሌቪዥን አማካይነት በመሰጠት ላይ ያለው ፕሮፖጋንዳ ነው። በዚህ ፕሮፖጋንዳ ያልተጠመቀ ተማሪ የሚቀጥለው ዓመት መደበኛ ትምህርት አይቀጥልም በማለት ተቋማቱ ለካድሬ ማሰልጠኛነታቸው እውቅና ሰጥተዋል።
በዚህ ብዙ የአገር ሀብትና ጊዜ በፈሰሰበት ቅስቀሳ፣ የወያኔ ካድሬዎች ዘረኛና ከፋፋይ ፓሊሲዎቻቸውን ማር ቀብተው ወጣቱን ለመጋት እየጣሩ ነው። ለፓርቲ ቅስቀሳ የመንግሥትን መዋቅር መጠቀም በራሱ ወንጀል ቢሆንም ከዚህ በላይ ጉዳት ያለው ደግሞ የፕሮፖጋንዳው ይዘትና ዓላማ ነው። ወያኔ/ኢሕአዴግ ሁሉንም ነገር የሚያውቅ፤ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችል ተደርጎ የተዘጋጀው ፕሮፖጋንዳ በትውልድ ላይ የሚያስከትለው የእውቀትና የሥነ ልቦና ኪሳራ ከፍተኛ ነው።
በዚህ “ስልጠና” ተብሎ በሚሞካሸው ርካሽ ፕሮፖጋንዳ አማካይነት አድርባይ የሆነው ወያኔ ወጣቱን ለአድርባይነት እያዘጋጀው ነው። የወያኔ ዓላማ የኢትዮጵያ ወጣት መስሎና ዋሽቶ አዳሪ እንዲሆን ማድረግ ነው። የስልጠናው ዓላማ ወጣቶች ለግል ሕወታቸው ምቾች ሲሉ የወያኔ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የስልጠናው ዓላማ “ወይን ለኑሮ” ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘይቤ ለማድረግ ነው። ይህ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርትን መሠረተ ሀሳብን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት ነፃነት-ወዳድ ባህልንም የሚፃረር ነው። በዚህም ምክንያት ወያኔ የወጣቱን ትውልድ ላይ አዕምሮ ለማላሸቅ የሚነዛውን ፕሮፖጋዳ መቃወም የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የዜግነት ግዴታ ነው።
ደግነቱ በአብዛኛዎቹ የስልጠና አዳራሾች እየሆነ ያለው ወያኔ ያሰበውና የተመኘውን አይደለም። የኢትዮጵያ ወጣት የወያኔን ዘረኛ ፕሮፖጋንዳ የሚጋት እንዳልሆነ እያስመሰከረ ነው። በብዙ አዳራሾች የወያኔ ካድሬዎች ሊመልሷቸው ከማይችሏቸው ጥያቄዎች ጋር ተፋጠው እንዲያፍሩ ተደርገዋል። ወጣቶች፣ “የታለ የምታወሩለት እድገት ?” “ቻይና በሠራው እናንተ የምትፎክሩት ለምንድነው?“ “ፍትህ የት አለ?” “የአንድ ብሔር የበላይነትን ነው እኩልነት የምትሉት?” እያለ ካድሬዎችን እያፋጠጠ ነው። ወጣቱ አፈና በበዛበት ሁኔታ ውስጥም ሆኖ መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ለማንሳት መድፈሩ፤ በአንዳንድ አዳራሾች ደግሞ በጩኸት የፕሮፖጋንዳውን ሥራ ማወኩ ወጣቱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ የሚያኮራ ተግባር ነው።
ወያኔ፣ ወጣቱን አድርባይነትን ለማስተማር ያዘጋጀው ስልጠና የወጣቱ ቆራጥነትና አርበኝነት ማሳያ ሲሆን፤ ፍርሃት ለማስፈን የተጠራ ስብሰባ ድፍረትን አደባባይ ሲያወጣ ማየት የሚያኮራ ነው። ወጣቱ በዚህ ስልጠና ላይ ባሳየው ድፍረት ለለውጥ ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ አሳይቷል። አሁን የጎደለው ድርጅት ነው። የወጣቱ ለለውጥ ዝግጁ መሆን አንድ ትልቅ የምሥራች ነው። ይህ ዝግጁነት በድርጅት መደገፍ ደግሞ ተከታትሎ መምጣት ያለበት ሥራ ነው። የወጣቱ የመንፈስ ዝግጅትና ድርጅት ከተቀናጁ የወያኔ ውድቀት ቅርብ ነው።
ወጣቱ ከተቃውሞ ባለፈ ሊሠራቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ከፊቱ ተደቅነዋል። ከሁሉ አስቀድሞ ድርጅት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ሊጤን ይገባዋል። ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በወያኔ አገዛዝ ሥር ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ምስጢራዊና ማዕከላዊነትን ያልጠበቁ ትናንሽ ስብስቦች ይበልጥ ውጤታማ ይሆናሉ ብሎ ያምናል። ስለሆነም ግንቦት 7፣ እያንዳንዱ ለሀገሩ፣ ለነፃነቱ፣ ለክብሩ፣ ለፍትህ ግድ ያለው ወጣት ከሚመስሉትና ከሚያምናቸው ጥቂት ወዳጆቹ ጋር በምስጢር እንዲደራጅ አጥብቆ ይመክራል። የተደራጁ ስብስቦች ግንቦት 7ን ማግኘት ወይም ግንቦት 7 እነዚህን ስብስቦች ማግኘት አስቸጋሪ አይሆንም። የኢትዮጵያ ወጣት ለለውጥ ዝግጁ ነው። የጎደለው ድርጅት ነው። የጎደለውን ማሟላት ደግሞ የሁላችንም ግዴታ ነው።
ግንቦት 7:የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በወያኔ ስልጠናዎች ላይ ተቃውሞ ለማሰማት በመድፈራቸው የተሰማውን ደስታ ይገልፃል። ይህ ክስተት ወጣቱ ለለውጥ የተዘጋጀ እንደሆነ በአመላካችነት ወስዶታል። ይህ የለውጥ ፍላጎት በድርጅት ካልታገዘ ውጤት ስለማያመጣ ወጣቱ በትናንሽ ሕዋሶች ራሱን እንዲያደራጅ ይመክራል። ይህንን ካደረግን የወያኔ ፋሺስታዊ አገዛዝን የምናስወግድበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

አብርሃ ደስታ ሃብታሙ አያሌዉና እና ኤርትራ ( ግርማ ካሳ)

Habtamu abrhayeshiwas danielራሱን ግንቦት 7 ብሎ ከሚጠራ ድርጅት ጋር እና ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች በመገናኘት ፤ እንዲሁም ከባንክ በትዕዛዝ ብር በመቀበል የግንቦት 7 ተልዕኮና አላማ ለመፈፀም፤ ቁጥራቸው ከ60 በላይ የሆኑ ግለሰቦችን ለዚህ ጥፋት እንዲሰማሩ በማድረግ» የሚል ክስ ነው በወዲ ሃዉዜን/ትግራይ በሆነው አንጋፋ ፖለቲከኛ እና ብሎገር ላይ ክስ የቀረበው። ሌላው አንጋፋና አንደበተ ርትኡ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ፣ ሃብታሙ አያሌውም፣ «የግንቦት ሰባት ተባባሪ ነው» በሚል ነው ለመክሰስ ነው ዝግጅት እየተደረገ ያለው።
አብርሃ ደስታ እና ሃብታሙ አያሌው ፣ «ግንቦት ሰባትን ይደግፋሉ» የሚል ክስ ከቀረበባቸው፣ በተዘዋዋሪ መንገድ «ከሻእቢያ ጋር ወዳጆች ናቸው» ማለት ነው። ታዲያ የሻእቢያ ወዳጅ የሆነ ሰው፣ የኤርትራን መገንጠል ተቃዉሞ፣ ወይንም የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት መከበር እንዳለበት በማስመር ይናገራል ወይ ? እስቲ የጸረ-ሽብርና የአገር ደህንነት ተብዬው ምላሽ ይስጠን !!!
ሁላችንም እንደምናውቀው፣ በኤርትራ በኩል ትግል እናደርጋለን የሚሉ ወገኖች፣ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ሊናገሩ አይችሉም። በሻእቢያ ሥር እስካሉ ድረስ ቀይ መስመር ተሰምሮላቸዋል። እነ ግንቦት ሰባቶች፣ ኦነጎች …፣ እርዳታ የሚያገኙጥ ከሻእቢያ ማእከላቼ ደግሞ አስመራ እስከሆነ ድረስ፣ «ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል» ብለው የመናገራቸው ነገር ጭራሽ የማይታሰብ ነው።
ዶር ብርሃኑ ነጋ ከቃሊት እሥር ቤት ሆነው የጻፉት አንድ መጽሃፍ ነበር። መጽሀፍ ላይ ባለው የ ኤርትራ ካርታ ፣ ኤርትራ ተቆርጣለች። ሃብታሙ አያሌው የጻፈው መጽሃፍ ላይ በሚታየው የ ኤርትር ካርታ ኤርትራ አልተቆረጠችም። ሃብታሙ አያሌው፣ ምንም እንኳን ሻእቢያና ሕወሃት/ኢሕአዴግ ከመረብ በስተሰሜን እና በስተደቡብ ያለዉን ሕዝብ ከፋፍለው፣ በደም ቢያቃቡትም፣ «ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ በሆኑበት መልኩ፣ ወንድማማቾችን አንድ ማድረግ ይቻላል» የሚል እምነት ስላለው ነው፣ ኤርትራ ከተቀረው የኢትዮጵያ አካል ጋር የቀላቀላት። ከ23 አመታት በፊት ያለው አስቦ ሳይሆን ፣ ወደፊት የሚሆነው ታይቶት ነው። ታዲያ ይህ አይነት ፖለቲከኛ ነው የሻእቢያ አሽከር ነው ተብሎ የሚከሰሰው ?
ወደ አብርሃ ደስታ ልውሰዳችሁ። በቅርብ ጊዜ ስለ አሰብ የጻፈው አስደናቂ ጽሁፍ ነበር። «ጦርነት ፈርተን ግን ሐገራችንን አሳልፈን አንሰጥም» በሚል ርእስ፣ በአደብ ጉዳይ ላይ፣ አብርሃ ደስታ ሲጸፍ « እኛ ጦርነት አንፈልግም። ሕጋዊ ንብረታችን (ወደባችን) በሰለማዊ መንገድ እንዲሰጠን ነው የምንጠይቀው። አዎ! ጦርነት አንፈልግም። ጦርነት አንፈልግም ማለት ግን ጦርነት ከፍተን በሃይል የሌላ ሀገርና ህዝብ ንብረት አንወርም ማለት እንጂ ጦርነት ፈርተን ልአላዊ ግዛታችን (ሃብታችን) ለሌሎች ሃይሎች አሳልፈን እንሰጣለን ማለት አይደለም። ጦርነት አንፈልግም ማለት ጦርነት እንፈራለን ማለት አይደለም። አዎ! ጦርነት ስለማንፈልግ ሌሎች ህዝቦችን አንወርም። ጦርነት ፈርተን ግን እናት ሀገራችን አናስደፍርም» ነበር ያለው።
ታዲያ በምን መሰፍርትና ሚዛን ነው አቶ ሃብታሙ አያሌው እና አቶ አብርሃ ደስታ የ«ሻእቢያ ተላላኪ» የሚሆኑት ? በምን መስፈርት ነው ግንቦት ሰባቶች ሊባሉ የቻሉት ?
«ህወሓት በራሱ ኮ የሻዕቢያ ተልእኮ ለማስፈፀም በሻዕቢያ የተቋቋመ ድርጅት ነው። ህወሓት የመሰረተው ማነው? ሻዕቢያ ነው። ሻዕቢያ መሓሪ ተኽለ (ሙሴ) የተባለ ኤርትራዊ የሻዕቢያ አባል በትግራይ ለሻዕቢያ ሊያግዝ የሚችል ድርጅት እንዲያቋቁም ወደ ኢትዮዽያ ላከ። እነዚህ ህወሓት የመሰረቱ የሚባሉ ሰባት ሰዎች አሰባስቦ እንዲደራጁ አደረገ» ብሎ አብርሃ ደስታ እንደጻፈው፣ ለሻእቢያ ዉስጥ ዉስጡን የሚቆረቀረዉስ ሕወሃት አይደለችንም ? ያ ባይሆን ኖሮ ተሽቀዳድሞ የአልጀርስ ስምምነት ይፈረም ነበርን? ያ ባይሆን ኖሮ አገር ቤት ካሉ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ጋር አልነጋገርም እያሉ፣ የሕወሃት/ኢሕአዴጉ ዳግማዊ መለስ ዜናዊ፣ ኃይለማሪያም ደሳለኝ «ካስፈለገም አስመራ ድረስ እሄዳለሁ» ይሉ ነበርን ?
እርግጥ ነው እነዚህ ሁለቱ አንጋፋ ወጣት ፖለቲከኞች፣ ኢሳት በተሰኘው ሜዲያ ቀርበው ቃለ ምልልስ አድርገዋል። አቦይ ስብሐት ነጋ፣ አምባሳደር ቪኪ ሃደልሰን፣ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን፣ ወንጌላዊ ዳንኤል ጣሰው ..የመሳሰሉትም በኢሳት ቀርበዋል። ታዲያ እነ አባይ ስብሐት ፣ «ኢሳት ላይ ቀረባችሁ» ተብለው ወደ ወህኒ የወረዱበት ሁኔታስ የታለ ?
በአንድ ሜዲያ መቅረብ አንድን ሰው ጥፋተኛ አያሰኘዉም። አንድ ሰው መከሰስ ካለበት፣ ሊከሰስ የሚገባው በቃለ መጠይቆቹ ዉስጥ ባለው ይዘት ነው። አቶ ሃብታሙና አቶ አብርሃ፣ ሲጽፉም ሲናገሩም በግልጽና በአደባባይ እንደመሆኑ «ይሄን ተናገረዋል.. » ተብለው የሚከሰሱበት ነጥብ ይኖራል ብዬ አላስብም። በመሆኑም አገዛዙ ፣ እነዚህ ሰላማዊ ዜጎችን ሽብርተኞች ናቸው ብሎ ማሰሩ የትም አያደርሰውም። ይህ አይነቱ ፍርድ ገምድልነትና ዜጎችን ያለ ከልካይ ማሰርና ማንገላታት መቆም አለበት።

torsdag 21. august 2014

የግንቦት 7 ሕዝባዊ ስብሰባዎች በዓለም ሃያ ስድስት ታላላቅ ከተሞች

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በመላው ዓለም ላይ ከሚገኙ አባላት፣ ደጋፊዎቹና በአጠቃላይ ከኢትዮጵያውያን  ጋር በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ለመመካከር ዝግጅቱን አጠናቋል።
በዚህም መሠረት ከዚህ በታች በተዘረዘሩት 26 የዓለም ታላላቅ ከተሞች ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ተጠርቷል።
  1. በላስቤጋስ                   ዩ ኤስ አሜሪካ              ረቡስ ኦገስት 27 ቀን
  2. በሂውስተውን               ዩ ኤስ አሜሪካ              ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
  3. በአትላንታ                   ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  4. በዋሺንግተን ዲሲ                     ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  5. በቦስተን                    ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  6. በሎስ አንጀለስ              ዩ ኤስ አሜሪካ              ቅዳሜ  ሴፕተምበር 6 ቀን
  7. በሳንቲያጎ                   ዩ ኤስ አሜሪካ              እሁድ ሴፕተምበር 7 ቀን
  8. በቶሮንቶ                    ካናዳ                        እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  9. በካልጋሪ                    ካናዳ                        ሴፕቴምበር 1 ቀን
  10. በደርባን                     ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  11. በጆሃንስበርግ                ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  12. ቬሪኒንፍ                    ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት  31 ቀን
  13. ሩስተምበርግ                ደቡብ አፍሪቃ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  14. ፍራክፈርት                  ጀርመን                     ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
  15. ሙኒክ                       ጀርመን                     እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  16. ሄልሲንኪ                   ፊንላንድ                    ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
  17. አምስተርዳም                ኒዘርላንድስ                   ቅዳሜ ሴፕተምበር 13 ቀን
  18. ኦስሎ                        ኖርዌይ                      እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  19. ለንደን                       እንግሊዝ                   ቅዳሜ ሴፕተምበር 6 ቀን
  20. ስቶክሆልም                 ስዊድን                      ቅዳሜ ሴፕተምበር 6 ቀን
  21. ፐርዝ                        አውስትራሊያ               እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  22. ሜልቦርን                             አውስትራሊያ               እሁድ ሴፕቴምበር 7 ቀን
  23. ቴላቪቭ                     እስራኤል                    ሐሙስ ሴፕቴምበር 11 ቀን
  24. ብራሰልስ                             ቤልጂየም                   እሁድ ሴፕቴምበር 14 ቀን
  25. ኦክላን                      ኒዩ ዚላንድ                 እሁድ ኦገስት 31 ቀን
  26. ሲኡል                      ደቡብ ኮርያ                 እሁድ ኦገስት 31 ቀን
በእነዚህ ስብሰባዎች ሁሉ የንቅናቄዓችን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሥራዎች ይወሳሉ። ወያኔን ማስወገድ በሚቻልበት ስልቶች ላይ ውይይት ይደረጋል። እስከዛሬ ድረስ ንቅናቄዓችንን ለመቀላቀል የተቸገራችሁ ወገኖች ይህንን አጋጣሚ እንድትጠቀሙበት ጥሪ እናደርጋለን።  በማናቸውም ምክንያት አባል ሳይሆን ደጋፊ መሆን ለምትፈልጉ ወገኖቻችንን የደጋፊዎች ምዝገባ ሥርዓት አዘጋጅተናል፤ እድሉን ተጠቀሙበት።
ኑ! ኢትዮጵያ አገራችንን፣ ኢትዮጵያዊ ወገናችንን እና ራሳችን ነፃ ለማውጣት እና በሀገራችን ፍትህ እንዲሰፍን ለማድረግ የሚደረገውን ትግል ይቀላቀሉ። ከዘወትር የህሊና ወቀሳ ይገላገሉ። ለዚህ ትግል ሁሉም የሚያበረክተው ነገር አለ። ስለሆነም በአቅራቢያዎ ወደሚደረገው የግንቦት 7 ስብሰባ ይምጡ፤ ጥያቄዎች ካልዎት ይጠይቁ።
አሁን ወሳኝ የትግል ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ትግላችን ሶስት የትግል ስልቶችን ያስተባበረ ነው – ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ሕዝባዊ አመጽ። ትግላችን በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ነው።
በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከድጋፍ ሰጪነት ወደ ተግባራዊ ተሳትፎ የተሸጋገሩበት ወቅት ነው። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል። የወያኔ ድርጅቶችና የወያኔ ሹማምንት በየትኛው አገር ተዝናንተው እንዲኖሩና እንዲነግዱ አንፈቅድላቸውም። በእነዚህ ስብሰባዎች ስለዚህ ጉዳይ ይመከራል።
ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት ሕይወታቸውን ለመሰዋት ተነስተዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች የአርበኛ ወጣቶቻችንን ጥረት እንዘክራለን። ሺዎች እንዲቀላቀሏቸው ጥሪ እናደርጋለን። በሁሉም ስብሰባዎች በአገር ውስጥም በውጭ አገርም የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ወጣት ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪ ይደረግለታል።
በሁሉም ስብሰባዎች ለኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥሪ  ይደረጋል። የሠራዊቱ መሪዎች የፋሽስት ወያኔ ባለሟሎች ቢሆኑም ሠራዊቱ ግን ከኢትዮጵያ አብራክ የወጣ ኢትዮጵያዊ ነው። ሠራዊቱ የወያኔ መጠቀሚያ ከመሆን የነፃነት ታጋዮችን እንዲቀላቀል፤ ያ ካልተቻለም ለወያኔ ሥልጣን እንዳይሞት፤ ወገኑን እንዳይገል ጥሪ ይደረግለታል።
መጥተው የእነዚህ ታሪካዊ ስብሰባዎች አካል ይሁኑ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ሰማያዊ ፓርቲ “ለተማሪዎች በግዳጅ የሚሰጠውን ካድሬያዊ ስልጠና እና ትውልድን የማኮላሸት ሴራ አጥብቀን እናወግዛለን!” አለ

ሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ ባወጣው መግለጫው ለተማሪዎች በግዳጅ እየተሰጠ ያለውን ካድሬያዊ ስልጠና በማውገዝ ኢሕአዴግ እየሰራ ያለውን ትውልድን የማኮላሸት ሴራ አጥብቀን እናወግዛለን አለ። መግለጫው እንደወረደ እነሆ፦
blue partyላለፉት 23 ዓመታት ህወሓት/ኢህአዴግ ስራዬ ብሎ ካዳከማቸውና ጉዳዬ ከማይላቸው ዘርፎች ውስጥ የሚመደበው የትምህርት ስርዓቱ ሲሆን ይህም ከኢህአዴግ ስህተቶች ሁሉ ዋነኛው እና አሳፋሪ ተግባሩ ነው፡፡ ለሁለት አስርት አመታት ትውልዱን በማምከን በሀገሩ ተስፋ እንዲቆርጥ ከገፉት ጉዳዮችም ግንባር ቀደሙ የህወሓት/ኢህአዴግ የተምታታበት የትምህርት ፖሊሲ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት የጀርባ አጥንት መሆኑ እየታመነ የትምህርት ስርዓቱ ሆን ተብሎ በንቀት እና በዝርክር አሰራር እንዳያድግና ጥራት እንዳይኖረው ኢህአዴግ እየተጋ አሁን ድረስ ዘልቋል፡፡
በዚህ አይነቱ አጥፊ አካሄድ ምክንያትም ሀገራችን በዓለም ደሃ ሀገራት ተርታ ቀዳሚዋ ሆናለች፡፡ የተማረ እየተገፋ በስራ አጥነት ሲንከራተት እና ለስደት ሲዳረግ በካድሬነት የስርዓቱ አገልጋይ መሆን ደግሞ በተቃራኒው ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው የገዢው ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ሲገደዱ መቆየታቸውና የኢህአዲግ አባል ካልሆኑም ስራ ሊያገኙ እንደማይችሉ እየተነገራቸው በፍራቻ ለአባልነት የተመዘገቡ ብዙዎች እንደሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በዚህ ሳያበቃ አሁን አሁን ደግሞ የገዢውን ፓርቲ ያረጀና ያፈጀ ኋላቀር አስተሳሰብና ርዕዮተ-ዓለም በተማሪዎች ላይ ለመጫን በየዓመቱ መጀመሪያ ‹ስልጠና› በሚል ፈሊጥ በጀት በጅቶ በግድ ሊግታቸው እየሞከረ ይገኛል፡፡
በዚሁ በያዝነው ወርም በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች እንዲሰበሰቡና ስልጠና እንዲወስዱ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን ስልጠናውን ያልተከታተለም መደበኛ ትምህርቱን እንደማይቀጥል ማስፈራሪያ አይሉት ማሳሰቢያ በገዢው ፓርቲ በኩል ተላልፏል፡፡ ሌላው አስገራሚ ዜና ደግሞ ተማሪዎቹ በግድ ስልጠናውን እንዲወስዱ መገደዳቸው ሳያንስ ወደ ግቢ ከገቡ በኋላ ተመልሰው መውጣት እንደማይችሉ መሰማቱ ነው፡፡ ይህም ኢህአዴግ ካድሬዎቹን የሚያሰለጥንበት ዝግ የስብሰባ ስልት መሆኑ ጉዳዩን የበለጠ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ይህንን ስልጠና ሲያካሂድም፡-
1. ህግን በጣሰ መልኩ የትምህርት ማዕከላትን የፖለቲካ ማራመጃ እና የአንድ ፓርቲ ርዕዮተ-ዓለም ማስፈፀሚያ አድርጓል፡፡
2. ይህን ፋይዳ ቢስ ስልጠና በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎችና ከ800.000 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በሚሰጥበት ወቅት ከፍተኛ የህዝብ ሀብት እያባከነ ይገኛል፡፡
3. ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በነፃነት ማሳለፍ ሳይችሉ በአስቸኳይ ወደ ዩኒቨርስቲዎች እንዲመለሱ ተገድደዋል፡፡
4. በሚሰጠው ስልጠናም ላይ በአክራሪነት በብሔርተኝነትና በመሳሰሉት ጉዳዩች ሽፋን በተማሪዎች ዘንድ መርዛማ ጥላቻን እየረጨ ይገኛል፡፡
5. በአጠቃላይ በስልጠናው ወቅት ርካሽ የፕሮፖጋንዳ ስልትን በመጠቀም መጪውን ምርጫ በማምታታት ለማለፍ እየሞከረ ሲሆን ይህም በአምባገነንነቱ ቀጥሎ ህብረተሰቡን አማራጭ ለማሳጣትና ሀገሪቷን ወዳልተፈለገ አለመረጋጋት ሊወስድ እየሞከረ መሆኑን ያሳያል፡፡
በመሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ ይህን የገዢው ፓርቲ ህገ ወጥ አድራጎት አጥብቆ እያወገዘ ጉዳዩን እየተከታተለም አቋሙን ይፋ የሚያደርግ መሆኑንን ይገልፃል፡፡ ተማሪዎችም በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ሳይደናገጡ ያለምንም ፍርሃት ህጋዊ በሆነ መንገድ ይህን ካድሬያዊ ስልጠና በማውገዝ፣ የገዢውን ፓርቲ ድብቅ ሴራ በማጋለጥ እና ለህወሓት/ኢህአዴግ የተለመደ አጥፊ ፕሮፖጋንዳ ባለመታለል ተማሪዎች በአንድነት እንዲቆሙ ሰማያዊ ፓርቲ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ነሀሴ 15/2006 ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

onsdag 20. august 2014

ዳኞች ካድሬ ሲሆኑ እንደማየት የመሰለ የአገር ዉድቀት የለም – ግርማ ካሳ

አገሩን እና ሕዝቡን የሚወድ ። እንደ ሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን፣ ኢትዮጵያ ከግፍ አገዛዝ ተላቃ ዜጎች መብታቸዉና ነጻነታቸው ተጠበቆ፣ ተከባብረዉ በስላም የሚኖሩባት አገር እንድትሆን፣ የሚያደርጉትን ትግል የተቀላቀለ ነው። ወጣት ነው። ጉልበትና አቅም አለው። እንደ አንዳንዶች በጥቅም ተታሎ አደርባይነትን መምረጥ ይችል ነበር። ነገር ግን አላደረገዉም። «ሰዉ ያለ ነጻነቱ ምንድን ነው ? » ብሎ ለነጻነቱ ቆመ። የባለ ራእዩ ወጣቶች ማህብርን ከዚያም የአንድነት ፓርቲን ተቀላቀለ። በአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ መዋቅር የቦሌ ወረዳ አመራር አባል ሆኖ ይሰራ ነበር። በሶሻል ሜዲያዉም ብዙ ጊዜ ድምጹን ያሰማል። አይፈራም። ወኔ አለው።
ጥላዬ
በቅርቡ በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ እየተደረገ በነበረዉ፣ ዉህዱን ፓርቲ ለመምራት በተደረገው የምርጫ ፉክክር «አዲስ አመራር ያስፈልጋል» በሚል ለአቶ በላይ ፍቃደ ይቀሰቅስ ነበር። ለዉጥ ፈላጊ ነው።
ነሐሴ 4 ቀን 2006 ዓ.ም ፣ ዜጎችን ማሰርና ማሰቃየት የለመደባቸው የአገዛዙ ታጣቂዎች ከየአቅጣጫው ተረባረቡበት። ምክንያቱ ለጊዘው ባልታወቀ ሁኔታ ወደ ወህኒ ወረወሩት። ይህ ወጣት ፣ ብዙዎች የማያወቁት፣ የማደንቀዉን የማከብረው ጥላዬ ታረቀኝ ይባላል።
ፖሊሲ ፍርድ ቤት ይዞት በቀረበ ጊዜ፣ «በሰው ላይ ጉዳት አድርሷል» የሚል ክስ ነበር ያቀረበበት። ፖሊሲ በሰው ላይ ጉዳት አደረሰ የሚል ክስ አቅርቦ ጉዳት ደረሰበትን የተባለው ግለሰብ ግን ለማቅረብ አልቻለም። «ጉዳይ ደረሰበት የተባለውን ሰው ማግኘት አልቻልኩም» ብሎ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ጊዜ እንዲሰጠው ጠየቀ። ወጣት ጥላዬ ግን ለፍርድ ቤቱ ፣ «የያዙኝ ደህንነቶች እየመጡ ከእኛ ጋር ለመስራት ፈቃደኛ እስካልሆንክና የምንሰጥህን ተልዕኮ እስካልፈፀምክ እዚህ ትበሰብሳለህ እንጂ አትወጣም» እያሉ እንደሚዝቱበት አስረዳ። ዳኛው ግን መረጃ ባልቀረበበት እና በወጣት ጥላዬ ላይ በፖሊሶች ዛቻና ማስፈራሪያ እየተሰጠ ባለበት ሁኔታ፣ በዋስ እንዲፈታ ሳይፈቅ ቀረ። ለነሐሴ 12 ፖሊሲ መረጃዎቹን አጠናቆ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሰጠ።
ጉዳት ደረሰ የተባለው ከሁለት ወራት በፊት፣ በሰኔ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ነው። በቀጠሮዉ ቀን፣ ፍርድ ቤቱ «ሁለት ወራት ሙሉ የት ነበራችሁ? ለምንስ ጉዳት የደረሰበት ሰው አላቀረባችሁም ? » ሲል ጠየቀ። ፖሊሶች «ጉዳይ የደረሰበትን ሰው ልናገኘው አልቻልንም። የሕክምና ማስረጃ እንድናቀርብ ይፈቀድልን» ብለው ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ወጣት ጥላዬ «የአንድነት ፓርቲ አባል በመሆኔ፣ ባለኝ የፖለቲካ አመለካከት ጫና ለማሳደር የተወጠነ ውጥን» ነው ሲል ከፍርድ ቤቱ ፍትህን ጠየቀ።ፍርድ ቤቱ ግን አሁን ለሰላማዊ ዜጎች ፍትህን ነፈገ። ወጣት ጥላዬ በወህኒ እንዲቆይ ተደርጎ ተለዋጭ ቀጠሮ ለነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም ተሰጠ።
አስቡት፣ የሕክምና መረጃ ያለ ባሌበቱ ሆስፒታሎች መስጠት የለባቸውም። (የአገር ደህንነትን የሚነካ ካልሆነ በቀር)። አሁን፣ ፖሊስ እያለ ያለው፣ ታከመ የተባለው ሰው ፍቃድ ሳይጠየቅ፣ የህክማን ማስረጃ ከሃኪም ቤቶች እንደሚያቀርብ ነው። ለነገሩማ የሆስፒታል አስተዳዳሪዎች ዉሸትን ጨማምረው፣ ያለዉን እንደሌለ፣ የሌለዉን እንዳለ አድርገው መረጃ መስጠታቸው አይቀርም። በተለያዩ ጊዜያት በሌሊት የሚገደሉ፣ በረሃብና በጠኔ የሚሞቱ ብዙ ናቸው። በአገር ቤት ችግር እንደሌለ የዉሸት ገጽታ ለማቅረብ የሚፈልገው አገዛዙ፣ ሆስፒታሎች የዉሸት አታብሲ (የሞት ይሕክምና ማረጋገጫ) እንዲጽፉ እንደሚያደርጓቸውም ያው አገር ሁሉ የሚያወቀው ሐቅ ነው።
እንግዲህ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው ሁለት ትላልቅ ነጥቦች አሉ።
1. ብዙዎቻችን በጣም የሚታወቁ ግለሰቦች ሲታሰሩ ነው የአገዛዙ ዜጎችን የማሸበርና የማወክ ተግባር የሚታየን። ነገር ግን በአገራችን እየተደረገ ላለው እልህ አስጨራሽ ትግል፣ ብዙ የማናውቃቸው ወገኖቻችን ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ነው። ከነዚህም አንዱ ወጣት ጥላዬ ታረቀኝ ነው።
2. በኢትዮጵያ አገራችን ባሉ ፍርድ ቤቶች እየታየ ያለው፣ ፍትህን የማስከበር ሥራ ሳይሆን፣ ፍጹም አሳፋሪ፣ ኋላ ቀርና አሳዛኝ የፍርድ መዛባት እንደሆነ ነው። ፖሊስ ዜጎችን እንደፈለገ ሲያስርና ሲያሸብር፣ በፈለገ ጊዜ ተጨማሪ ቀጠሮ ሲጠይቅ፣ ዳኞች ቅንጣት እንኳን የሕግ ባለሞያዎች የስነ-ምግባር ኮድ (ኤቲክስ) ሕሊናቸውን ወቅሷቸው፣ ትክክለኛ ነገር ሲሰሩ እንደማይታዩ ነው። ዳኞች ካድሬ ሲሆኑ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ለአገር ዉድቀት የለም።
ገዢዎች ይኸው ስልጣን ከያዙ ጀመሮ እንደገደሉና እንዳሰሩ ናቸው። ሕግን መቀለጃ እያደረጉ ናቸው። ነገር ግን በዱላ፣ በጠመንጃ፣ በማስፈራራት፣ በዛቻ ኢትዮጵያዉያን ለመብታቸው፣ ለነጻነታቸውና ለአንድነታቸው የሚያደርጉት ትግል ሊገቱ አይችሉም። እሳት የለበሱ፣ በወኔ የተሞሉ፣ የስለጠነ ፖለቲካ የሚያራምዱ፣ በአንድ ቦታ ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቷ የሚኖሩ፣ አገዛዙ ከዘረጋዉን የጎሳ ድንበር አልፈው በሰብእናና በኢትዮጵያዊነት የተሳሰሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንደ ጥላዬ ታረቀኝ ኢትዮጵያ አፍርታለች።

ጠብ-መንጃ አናነሳም! (ተመስገን ደሳለኝ)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
“ብሶት የወለደው” ኢህአዴግ ከሁለት አስርታት በፊት በሰሜን ተራሮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ጋር ያደረገውን የጎሬላ ውጊያ “አጃኢብ” በሚያሰኝ ቆራጥነት በድል መወጣቱ የማይታበል እውነትነው፤ ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላም ለሚሰነዘርበት ማንኛውም አይነት የኃይል ጥቃት፣ ያውም ማቸነፍ አለማሸነፉን ሳያሰላ በፍጥነት ዘሎ ለመዘፈቅ ሲያንገራግር የተስተዋለበት ጊዜም አልነበረም፤ አሀዱ ብሎ የአመፅ ትግል ከጀመረበት ዕለት አንስቶ ላለፉት አርባ ዓመታት ከጀብሃ እስከ ኢህአፓ፤ ከኦነግ እስከ ኦብነግ፤ ከትህዴን እስከ አርበኞች ግንባር፤ ከሻዕቢያ እስከ አልሸባብ… በስም ተዘርዝረው ከማያልቁ ብረት-ነካሽ ድርጅቶች ጋር ወደ ፍልሚያ ለመግባት ከመወሰኑ በፊት ሰላማዊ መፍትሄዎችን ግራና ቀኝ የመፈተሽ ትዕግስትም ሆነ ልባዊ ፍላጎት እንዳልነበረው የራሱ የታሪክ ድርሳናት ሳይቀሩ በግላጭ ይናገራሉ፡፡ በተለይም ሀገር በቀሎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች በእንዲህ አይነቱ አስገዳጅ ሁኔታ ነፍጥ አንግበው የመገኘታቸው ምስጢር በቀጥታም ሆነ በዘወርዋራው የሥርዓቱ እጅ ስላለበት መሆኑን የሚያስረዱ ማሳያዎች የበዙ ናቸው፡፡ ከነዚህ መሀል አንዱና ዋነኛው በርሱ አጋፋሪነት የፀደቀውን ሕገ-መንግስት፤ በፕሮፍ መስፍን ወልደማርያም አገላለፅ “በሕገ-አራዊት”ነት ቀይሮ በአደባባይ መብቶቻቸውን መጨፍለቁ ነው፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በነፃ ምርጫ ማሸነፍም ሆነ ሥልጣን መጋራትን ‹ግመል በመርፌ ቀዳዳ…›ን ያህል ማጥበቡ እና “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” የምትለዋ የከረምች እብሪት ድርጅቶቹ “ዱር ቤቴ” እንዲሉ ያስገደዷቸው ገፊ-ምክንያቶች ስለመሆናቸው ቅንጣት ያህል አያጠራጥርም፡፡
በግልባጩ በበርካታ ድርሳናት ስለጀብዱውና ተጋድሎው የተተረከለት አብዮታዊ-ግንባሩ፣ ለሕዝባዊ እምቢተኝነት ፈሪ እና ድንጉጥ የመሆኑ ነገር ተደጋግሞ መወሳቱ ሌላ እውነት ነው፡፡ ብረት ያነሱ ተቀናቃኞቹን በብረት ለመጋፈጥ ካለው ወኔ ይልቅ፣ ሰላማዊ ትግልን በተመሳሳይ ቋንቋ የማስተናገድ ፍርሃቱ እጥፍ ድርብ እንደሚልቅ በተጨባጭ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በተለያየ አጋጣሚ በድንጋጤ ሲርበተበት፣ እንቅልፍ ሲያጣ፣ ግብታዊ እርምጃ ሲወስድ… የተስተዋለውም በሕግ የደነገገውን መብት ተንተርሰው የተቀሰቀሱየተቃውሞ ትግሎች የተጠናከሩበት ጊዜያት ላይ ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የሰሞኑም ዘመቻ ነፃ-ፕሬስ ግባት ከዚሁ የሚመደብ ነው፡፡
በሰላማዊ የትግል ስልቶች ማዕቀፍ ስር የሚገኙ መብቶታቸውን የተጠቀሙ ቆራጦች ለተቃውሞ በወጡ ቁጥር፣ ቅጥ-ባጣ መልኩ መፍረክረኩን እና የእውር-ድንብር እርምጃ የመውሰዱን እውነታ ለማስረገጥ በተለያየ ጊዜ የተመለከትናቸው ማሳያዎችን እየጠቀሱ መሟገቱ አስቸጋሪ አይደለምና ጥቂቶቹን በአዲስ መስመር ላስታውስ፡-
በ1993 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተነሳውንና የአካዳሚያዊ ነፃነትን የጠየቀውን ሰላማዊ ተቃውሞ ተከትሎ በመዲናይቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ንቅናቄ ምን ያህል የሚይዝ የሚጨብጠውን አሳጥቶት እንደነበረ ለመረዳት፣ በሃያና ሰላሳ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማይቱን ኗሪዎች (አብዛኛዎቹ በተቃውሞ ያልተሳተፉ) ከየቤታቸው እንዴት አፋፍሶ ለግፍ እስር እንደዳረጋቸው ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በወቅቱ ክስተቱ አገሪቱን ለሁለት ቀናት መንግስት-አልባ አስመስሏት እንደነበረ በተሳታፊነትም በታዛቢነትም ሁኔታውን የተከታተልን ዜጎች ሁሉ አንዘነጋውም፡፡

በ1995 ዓ.ም የሲዳማ ተወላጆች፣ ክልላዊነትን እና የሀዋሳ ከተማ ዕጣ-ፈንታን በሚመለከት ጥያቄ አንስተው በደቡብ ክልል ርዕሰ- መዲና ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ጊዜም፣ አብዮታዊ-ግንባሩ ምን ያህል ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ እንደነበረ ማስታወሱ ለዛሬው ጠ/ሚንስትርም ሆነ ለብዙዎቻችን የሚከብድ አይሆንም፤ ሥርዓቱ ያዘመታቸው የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት አባላት ሕጋዊውን የሲዳማ ተወላጆች ጥያቄ ለመቀልበስ፣ ጎዳናዎቹን በደም-አባላ በማጥለቅለቅ የፈፀሙት አሳዛኝ ጅምላ ጭፍጨፋ (ዘር ማጥፋት) በታሪክ መዝገብ ጥቁር ገፅ ላይ በማይፋቅ መልኩ ተከትቦ አልፏል፡፡ ይህም ሆኖ የዚህ ሰላማዊ ተቃውሞ ውጤት፣ ለፌደራል መንግስቱ፣ ክልሉን በኃላፊነት ሲመራ የነበረውን ኃይለማርያም ደሳለኝን፣ በሽፈራው ሽጉጤ እንዲተካ ያስገደደ የሽንፈት ፅዋ ማስጎንጨቱ ይታወሳል፡፡

በምርጫ 97 ዋዜማ ሚያዝያ 30 ‹‹ዴሞክራሲን እናወድስ›› በሚል መሪሕ-ቃል ‹‹ቅንጅት›› በጠራው ስብሰባ ላይ ተገኝቶ መስቀል አደባባይን ያጥለቀለቀው የሕዝብ ‹‹ሱናሜ››፣ ሥርዓቱን ለከባድ ድንጋጤ አጋልጦ፣ በሀፍረት አኮራምቶ፣ ለከፋ ስቃይ ዳርጎት እንደነበረስ ከቶ ማን ሊዘነጋው ይቻለዋል? ያኔ የተመለከትነው ገዥው-ፓርቲን ከፍተኛ ፍርሃት ላይ የጣለ አስደንጋጭ ትዕይንት፣ ዛሬም ድረስ ለሚተገብረው የቅድመ-ምርጫ አደን መስዋዕት እየዳረገን እንደሆነ ሁላችንንም የሚያስማማ እውነታ ነው (በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹ምን አልባት ሕዝቡ በቁጣ የቤተ-መንግስቱን አጥር ገርስሶ ሊገባ ይችል ይሆናል› በሚል ፍርሃት ከእነ ቤተሰቡ ደብረዘይት አየር ኃይል ግቢ ተሸሽጎ አሳልፏል የሚለው ወሬ ከሹክሹክታም በዘለለ በከተማዋ በስፋት ተናፍሶ ነበር)፡፡

ሕዝበ-ሙስሊሙ ያቀጣጠለው ከሁለት ዓመት በላይ ያስቆጠረው የተቃውሞ ትግልም፣ አገዛዙን እንዴት በፍርሃት እንዳራደው ለመረዳት በጉዳዩ ዙሪያ በየጊዜው የሚወጡ እርስ-በርስ የተምታቱ መግለጫዎችን እና ረብ-የለሽ ‹‹ዘጋቢ›› ፊልሞቹን መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ይህንን ፍፁም ሰላማዊና ስልጡን የተቃውሞ ንቅናቄን ለማፈን የተወሰዱት የኃይል እርምጃዎችም፣ የእነ አባይ ፀሀዬን የይስሙላ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከማጋለጡ ባለፈ፣ ድርጅታቸው-ኢህአዴግን ለሳልሳዊ የውስጥ ክፍፍል መዳረጉን የመረጃ ምንጮች ያወሳሉ፡፡
በአናቱም ግንባሩ፣ በተቃውሞ ጎራ በተሰለፉ ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ነውረኝነቱን በግላጭ በሚያሳይ መልኩ የራሱን ሰዎች አስርጎ በማስገባት ለመከፋፈል ከሚሞክርበት ማኪያቬሊያዊ ሴራ በተጨማሪ፣ አመራሩን እና የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉ አባሎቻቸውን በጥቅማ ጥቅም በመደለል፣ ከሀገር በማሳደድ፣ ከፖለቲካ ተሳትፎ ራሳቸውን አግልለው በፍርሃት ‹‹ጎመን በጤና››ን እያጉረመረሙ የበይ-ተመልካች ሆነው አርፈው እንዲቀመጡ የብረት መዳፉን ለመጫን እና ለመሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶቹ ማስፈፀሚያነት በቢሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት አፍስሶ ጠንክሮ የመስራቱ (እየሰራም የመሆኑ) ጉዳይ አከራካሪ አይደለም፡፡ ይህንን ኩነት በምኩንያዊነት ለማስረገጥ በኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት የአቶ በረከት ስምዖን ምክትል የነበረውና ሀገር ጥሎ የተሰደደውን የቀድሞ ሚኒስቴር ዲኤታን የአቶ ኤርምያስ ለገሰን ምስክርነት መጥቀስ ተገቢ በመሆኑ፣ በቅርቡ ‹‹የመለስ ትሩፋቶች›› በሚል ርዕስ ለንባብ ካበቃው መጽሐፉ አንድ ማሳያ ላቅርብ፡-
‹‹በምርጫ 92 ኢህአዴግ መሸነፉን አስቀድሞ ካረጋገጠ በኋላ የተከተለው ስትራቴጂ የሕዝቡን ውሳኔ ባይቀይረውም ለማጭበርበር ጠቅሞታል፡፡ …የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት የሚያጠፉ ሶስት እርስ በእርስ የሚመጋገቡ ስትራቴጂዎችን ነደፈ፡፡ ስትራቴጂዎቹ እንደሚከተለው ነበሩ፤ በእጩ ምዝገባ ወቅት በተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ውስጥ ለኢህአዴግ የሚሰራ አስርጎ ማስገባት፤ በየወረዳው ምርጫ ቦርድ በሚፈቅደው መሰረት የተፎካካሪ እጩዎችን ከተቻለ በማሳመን ካልተቻለ በመደለልና በማስገደድ ራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረግ የሚሉ ነበሩ፡፡›› (ገጽ 58-59)
በነገራችን ላይ ኤርሚያስ ለገሰ በዚህ መጽሐፉ ለእንዲህ አይነቱ እኩይ ሴራ ስላልተበገረ አንድ ያልተዘመረለት ጀግና በዝርዝር አስፍሮልናል፡፡ ሰውየው በቅፅል ስሙ ‹‹አበበ ቀስቶ›› ተብሎ የሚታወቀው እና በምርጫ 92 በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ 24 ኢዴፓን ወክሎ ለውድድር የቀረበው ክንፈ ሚካኤል ደበበ ነው፡፡ የአገዛዙ ካድሬዎች ክንፈ በአካባቢው ጠንካራ ድጋፍ እንዳለው ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበረ ብርቱ ስጋት ላይ ይወድቃሉ፤ በዚህም ‹‹ምርጥ›› የሆነ አደናቃፊ ስልት ተነድፎ ለመተግበር መሞከሩን አቶ ኤርሚያስ እንደሚከተለው ይነግረናል፡-
‹‹(ክንፈ) ከምርጫው ፉክክር ገለል የሚልበት አማራጮች ታሰቡ፡፡ እሱን ማስፈራራቱ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ምድር ቢንቀጠቀጥም የሚፈራ ሰው አይደለም፡፡ በቁጥጥር ስር ለማዋል ደግሞ ወንጀል ሲሰራ እጅ ከፈንጅ መያዝ አለበት፡፡ ስለዚህ የቀረው የመጨረሻ አማራጭ በገንዘብ መደለል ሆነ፡፡›› (ገጽ 65)
ተራኪው ይቀጥላል፤ ለድለላው 50 ሺ ብር ወጪ ይደረጋል፤ በደላይነት ደግሞ ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም (ይህ ሰው የወቅቱ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ መሆኑን ልብ ይሏል) እና ኪሮስ የተባሉ የህወሓት አባላት ይመደባሉ፤ አቤም ሊያግባቡት ቤቱ ድረስ በመጡ ግለሰቦች ሃሳብ በመስማማቱ፣ ልዑልና ግብረ-አበሩ 35 ሺውን ለራሳቸው አስቀርተው 15ሺ ብር ይሰጡታል፤ የወረዳው የኢህአዴግ አመራርም በተከተለው ‹‹እፁብ-ድንቅ›› መፍትሔ ለጊዜው ከስጋት ነፃ ይሆናል፤ ግና፣ ይህ ሁኔታ ብዙ አልቆየም፡፡
ከሳምንታት በኋላ፣ ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ሸገር ተወልዶ፣ ሸገር ያደገው የአራዳ ልጅ አበበ ቀስቶም በታሪክ ሲዘከር የሚኖርበት ውሳኔውን እንዲህ ሲል አረዳቸው፡‹‹የተጋበዝኩትና ብራችሁን የተጠቀምኩት እናንተ ጋር የማይነጥፍ የብር ማምረቻ ስላለ ነው፡፡ ምርጫ የምወዳደረው ግን ለገንዘብ ሳይሆን ይህን አስከፊ ሥርዓት ለመጣልና ለነፃነቴ ነው፡፡ በዚህ ላይ ለመደራደር ህሊናዬ አይፈቅድም፡፡›› (ገጽ 65-66)
ዛሬ ‹‹አሸባሪ›› በሚል ክስ ተወንጅሎ፣ የሃያ አመት የእስር ቅጣት ተላልፎበት፣ በአሰቃቂው የቃሊቲ ወህኒ ተጥሎ የሚገኘው አበበ ቀስቶ እንዲህ ያለ ድፍረትና ቁርጠኝነት የነበረው ጀግና ስለመሆኑ አብዮታዊ ግንባሩን አደግድገው ያገለገሉት ካድሬዎች ጭምር እየመሰከሩለት ይገኛሉ፡፡
ከግል ገጠመኜ ደግሞ አንድ ልመርቅ፤
የ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኜ በምሰራበት ወቅት፣ አቤ በ‹‹አሸባሪ››ነት ተከሶ ፍርድ ቤት ይመላለስ ነበር፤ ከዕለታት በአንዱ ቀንም እጅግ የሚያሳዝንና የግፉአን እናቶችን የሀዘን እንባ የሚወክል ጽሑፍ ከወህኒ ቤት ይልክና በጋዜጣችን ላይ ይታተማል፡፡ ቀደም ብሎ እስክንድር ነጋ፣ አንዱአለም አራጌ እና ናትናኤል መኮንንም በተመሳሳይ መልኩ የላኳቸው ጽሑፎች ተስተናግደዋል፤ ይህ ከሆነ ሁለት ሳምንት በኋላ ‹‹የተከበረው›› ፍርድ ቤት እነዚህን ጽሑፎች እንዲታተሙ በመፍቀዴ ‹‹ችሎት መድፈር›› የሚል ክስ መስርቶብኝ ዳኞች ፊት ቀረብኩ፤ ከአራቱ ታሳሪዎች መካከልም አቤ ተለይቶ ተጠርቷል፤ የመሀል ዳኛውም አንድ ጥያቄ ጠየቀው፡-
‹‹ይህንን ጽሑፍ አንተ ነህ የጻፍከው?››
አበበ ቀስቶ መልስ ለመስጠት አልተቻኮለም፤ ዳኞቹ፣ ዓቃቢ-ሕግጋን እና የችሎቱ ታዳሚዎች በሙሉ ምን ሊል ይችላ ይሆናል? በሚል ጉጉት እየጠበቁት ነው፤ የእኔ አይደለም ቢልስ? ማን ያውቃል? …ጥቂት ሰከንዶች በአስጨናቂ ዝምታ ካለፉ በኋላም፣ ልበ-ሙሉ ፖለቲከኛ ፈገግ ብሎ መናገር ጀመረ፡-
‹‹አዎ፣ እኔነኝ የጻፍኩት! ፍላጎቴም እዚህ እናንተ ፊት ላነብላችሁ ነበር፤ ሆኖም ሰዓት የለንም ብላችሁ ስትከለክሉኝ ጊዜ ነው፣ ለተመስገን የላኩለት!››
(በቀጣዩ ሳምንት ስለመጽሐፉ በስፋት ለመወያየት ቀጠሮ ይዘን፣ ወደጀመርነው ርዕሰ-ጉዳይ እንመለስ)
ስለምን ነፍጥ አናነሳም?
በኢሕአዴግ ዘመነ-አገዛዝ ብረት የማንሳትን ተገቢነት የሚያቀነቅኑ ልሂቃን፣ ለትግሉ ስልት አግባብነት የሚያነሷቸውን መከራከሪያዎች በሁለት መልኩ ልናያቸው እንችላለን፡-
በቀዳሚነት ከገዥው-ፓርቲ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር አያይዘው፣ ለአቻቻይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያስፈልጉ ባህሪያት በፍፁም የማይስተዋሉበት፣ ይልቁንም ‹ሕገ-መንግስታዊነትን፣ የሕግ የበላይነትን፣ የተቋማት ነፃነት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን፣ የመሰሉ ዕሴቶችን በመጨፍለቅ የሚታወቅ ነው› የሚል ጥቅል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ እውነታው እነርሱ እንደሚሉት ቢሆንም እንኳ፣ ብረት የሚቀላቀልበት ትግል የሚያፈራርሳቸውን ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን እንደገና ከፍርስራሹ ዓመድ ላይ ለመጀመር የሚያስገድድ መሆኑን ግን የዘነጉት ይመስለኛል፡፡
ሁለተኛው ጭብጥ፣ የማሕበረሰቡን የፖለቲካ ባህል እና የአንድ ወቅት የሰላማዊ ትግልን ሙከራ ክሽፈት በማውሳት የሚቀነቀነው ነው፡፡ የፖለቲካ ባህላችን ለጦረኛነት፣ ተዋስኦን ለሚጨፈለቅ የመጠፋፋት መንገድ የቀረበ የመሆኑን መሞገቻ ለክርክር በመግፋት የሃሳባቸው ማጠንጠኛ ያደርጉታል፡፡ ይሁንና የመድበለ-ፓርቲ ሥርዓትን እና ነፃ የአደባባይ ክርክርን ያልተላመደ ማሕበረሰብን አሁንም ለትጥቅ ትግል መጥራት ይህንኑ አሉታዊ ሕዝባዊ ባህርይ ከማጠናከር የዘለለ አንዳች ፋይዳ እንደሌለው ለመሟገት የሚያስችሉ በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡ ‹ማሕበረሰቡ ለተራዘመ ሰላማዊ ትግል አይሆንም› ብለው የሚከራከሩ ጸሐፍት የሚጠቅሱት፣ 97 ላይ የተጨናገፈውን እንቅስቃሴና መሰል ሕዝባዊ ተቃውሞን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በተለይም የቅንጅት ጉምቱ ፖለቲከኞች እስኪበቃን እንደነገሩን፣ ስህተቱን ሁላችንም የምንጋራው ይሆናል (የኢሕአዴግ ቢልቅም ቅሉ!)፡፡ ግና፣ የወቅቱ ክስተት ከሰላማዊ ትግል አማራጮች አነስተኛ ሚና የሚሰጠውን የምርጫ ፖለቲካን ብቻ ግብ ያደረገ መሆኑ ‹ትግሉን ሞክረነዋል› የሚለውን መከራከሪያ ያጎደለው ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ይልቅ፣ ሰላማዊ ሕዝባዊ አብዮትን አንድም ጊዜ በቅጡ ሳንሞክር (በቀቢፀ-ተስፋ ተሞልተው የሥልጣን ጥማት ካሰከራቸው ቀልባሾች ሳንታደገው) ጠብ-መንጃ ወደማንገብ መመለስ ቢያንስ በቂ መከራከሪያዎችን ያሳጣል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከላይ በጥቅሉ ከጠቀስኳቸው ጭብጦች ባለፈ፣ እነዚህ ኢህአዴግ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ማግስት አንስቶ ነፍጥ የነከሱ ቡድኖች፣ንፁሃን ዜጎችን እንዳሻው እንዲያስር እና እንዲያሰድድ ፖለቲካዊ ሰበባ-ሰበቦች ከመስጠት ባሻገር ያዋጡት በጎ አበርክቶ (ተጨባጭውጤት) አለመኖሩን ልብ ማለት ያሻል፡፡
የሆነው ሆኖ የዚህ ጽሑፍ ተጠየቅ ከተለመዱት ሁለቱ የትግል ስልቶች አንዱን መባረክ እና ሌላኛውን ማውገዝ አይደለም፡፡ ይልቁንም በህወሓት ጠቅላይነት የሚመራው ገዥው-ግንባር፣ ከብረት ትግል ይልቅ፣ በሕገ-መንግስቱ ማዕቀፍ ስር ለሚጠቃለሉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ብርክ የሚይዘው መሆኑን በማውሳት፤ ባለፉት እትሞች በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› የጠቀስኳቸውን አተገባበሮች በበቂ ሕዝባዊ ጉልበት መግፋት እንደሚያዋጣ ዳግም አፅንኦት ለመስጠት ነው፡፡ ርግጥ ነው ሁላችንንም ግራ-ገቡ ኢህአዴግ ፍርሃት በናጠው ቁጥር ሲያሻው በገፍ ወህኒ እያጎረ፤ ሲፈልግ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንኳን ያልጨረሱ ብላቴኖችን ግንባር በጥይት እያፈረሰ፣ በል ሲለው ደግሞ ይህንን መከራ እና ስቃያችንን የምንተነፍስበት ሚዲያ እያሳጣን በምሬት እንደሞላን አንክድም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም ግን ድርጅቱ የተካነበትንና ለፍልሚያ የሚመርጠውን ጠብ-መንጃ አናነሳም፡፡ ጠብ-መንጃ የማናነሳው ልበ-ሙሉነታችን ከህወሓት-ኢህዴን መስራቾች የጉብዝና ዘመን ያነሰ ሆኖ በመገኘቱ አይደለም፤ ሚሊዮናት ዘመን ተጋሪዎቼ ለሀገር ጉዳይ፣ ለሕዝብ ጥቅም ግንባራቸውን እንደማያጥፉ አውቃለሁና፡፡ የደኑ መመንጠር ምሽግ ስላሳጣን ወይም የምናፈገፍግበት መሬት ስለጠፋንም አይደለም፡፡ ብረት-ጠል የሆንነው፣ በሰላማዊ ሕዝባዊ ዓመፅ ይህን ሥርዓት አስቁሞ፣ ኢትዮጵያን ማደስ እንደሚቻል ካለን የፀና እምነት ባሻገር፣ ነባራዊውም ሁነት ጮኾ የሚያስረግጥልን ይሄንን በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ የመጨረሻ ሙከራ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ዳግም ነፍጥ እንዳይነሳ አስተማማኝ ዋስትናን ሰጥቶ እንደሚጠናቀቅም አልጠራጠርም፡፡ በረዥሙ የጭቆና አገዛዝ በተለይም በእርስ በርስ ጦርነት ለተጎዳና ለደኸየ ሕዝብ፣ የወጣቶቹን ደም ለሚያስገብር ትግል አሳልፎ መስጠት፣ የነገይቱን ኢትዮጵያ ባድማነት ማወጅ ነውም ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ‹ብረት ያዋጣል› የሚሉ ኃይሎች በመረጡት መንገድ ሥርዓቱን አስገድደው ወደ ብሔራዊ እርቅና አገራዊ ሕዳሴ ሊያመጡልን ከቻሉ፣ የትግላቸው ታላቅ አበርክቶ እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡ ወደምናልመው ሁለንተናዊ ሕዳሴ ለመድረስም የሚኖራቸውን ሚና በምንም አይነት መነሾ ላሳንሰው አይቻለኝም፡፡
ከዚህ በላቀ በተከታታይ የተወያየንበት የ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ማዕቀፍ፣ በሕዝባዊ የአደባባይ ዓመፅ ሥርዓቱን ከማውረዱ በዘለለ፣ በደም-እልባት ያጣነውን አንድ ዋነኛ እሴት አውሶን የሚያልፍ ይመስለኛል፡፡ በሰላማዊ አብዮት የሚሳተፍ ዜጋ አገራዊ ሕዳሴን በማምጣት፤ ሁላችንንም በእኩልነትና በነጻነት የሚያኖር ፖለቲካዊ ሥርዓት ማዋለዱ አይቀሬ ነው፡፡ በመጪው አስተዳደር የሚከወኑትን ሀገራዊ ጉዳዮች በያገባኛል የሚከታተል፣ እያንዳንዱን የዜግነት መብቱን አጠንክሮ የሚጠይቅ እና በውይይት (በሃሳብ ብዙሃነት) የሚያምን ትውልድ በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ሂደት እንደሚፈጠር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የንቅናቄው አድማስ ሁሉን አቀፍ መሆኑ ከተሳካለት ደግሞ በድህረ-ለውጡ የሚነብረውን የፖለቲካ ባህል በእጅጉ የዘመነ ያደርገዋል፡፡ ‹የአብዮተኞች አባት› ተብሎ የሚወደሰው ካርል ማርክስ ከጓዱ ፍሬዴሬክ ኤንግለስ ጋር በጻፈው መድብል ላይ ይህን እውነት አስረግጦ አልፏል፡፡ ‹‹German Ideology›› በሚለው ያሰላሳዮቹ የጋራ ስራ ላይ የአብዮት ሂደት ዋና ፋይዳ ከለውጡ በኋላ የሚፈጠር ማሕበረሰብ የነቃ እንደመሆኑ፣
መጪዎቹ የሥልጣን ተረካቢዎች በቁመቱ ልክ ካልሆኑ (ካልመጠኑት) ለእነርሱም አስቸጋሪ እንደሚሆን የማስረገጡ እውነታ ነው፡፡
ለዚህም የቅርቡን የአረቡ መነቃቃት ማየት ያዋጣል፡፡ የግብፅ ሕዝብ ከአብዮቱ በፊትና በኋላ ያለውን የንቃት ልዩነት ማንም የሚያስተውለው ነው፤ ዛሬ ላይ የምናየው ማሕበረሰብ የሆስኒ ሙባረክ አገዛዝ ከነበረበት አንፃር ሲታይ ፍፁም ፖለቲካዊ ስለመሆኑ በብዙዎች ተወስቷል፡፡ ለእያንዳንዱ አገራዊ ጉዳይ ያገባኛል በማለት መሟገትን የዕለት ተዕለት ስራው አድርጎታል፡፡ ከዚህ አብዮታዊ ሃሳብ ትይዩ በብረት የሚመጣ ለውጥ፣ ተመልሶ ማሕበረሰባዊ ፍዝነት ውስጥ እንደሚጥለን መረዳታችንም፣ መጪውን የአብዮት አማራጭ ብቸኛው ትውልዳዊ ዕዳ ወደማድረጉ ገፍቶታል፡፡ ከሞት ይልቅ ህይወት፣ ከድቀት ይልቅ ጥንካሬ፣ ከመበታተን ይልቅ አንድነት የሚሰጠንን ሰላማዊ የለውጥ ንቅናቄ በቀጣዩ ዓመት ስለመከወን ደግመን ደጋግመን ማሰላሰል ደግሞ የዘመኑ አስገዳጅ ኃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!